ኔዘርላንድስ በመማሪያ ክፍሎች ውስጥ የሞባይል ስልኮችን መጠቀም አገደች

ስልክ የያዘ ተማሪ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የሞባይል ስልኮችን ጨምሮ የመማር ማስተማር ተግባርን ሊያስተጓጉሉ ይችላሉ የተባሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶች በኔዘርላንድስ ትምህርት ቤቶች ታገዱ።

በመማሪያ ክፍሎች ውስጥ የሞባይል ስልኮችን መጠቀም እንደታገደም የኔዘርላንድ መንግሥት አስታውቋል።

ዕቅዱ ከትምህርት ቤቶች ጋር በመተባበር ተግባራዊ እንደሚሆን የተገለጸ ሲሆን፣ ይህም በአውሮፓውያኑ አዲስ ዓመት ተግባራዊ መሂን ይጀምራል ተብሏል።

ሆኖም ልዩ የህክምና ፍላጎት ወይም አካል ጉዳተኛ የሆኑ ተማሪዎች ይህ እዳው እንደማይመለከታቸው ተገልጿል።

በተጨማሪ በዲጂታል ክህሎቶች ላይ በሚያተኩሩ የትምህርት ክፍለ ጊዜያት ላይ እነዚህ የቴክኖሎጂ ውጤቶች እንደሚፈቀዱም ተጠቁሟል።

ይህ እግድ በሕግ ባለመስፈሩ በሕጋዊ መንገድ ተፈጻሚ ባይሆንም፣ ወደፊት ግን ሊካተት ይችላል ተብሏል።

“የሞባይል ስልኮች ከሕይወታችን ጋር ከሞላ ጎደል የተሳሰሩ ቢሆኑም፣ በመማሪያ ክፍሎች ውስጥ ግን መገኘት የለባቸውም” በማለት የትምህርት ሚኒስትሩ ሮበርት ዲጅግራፍ ተናግረዋል።

“ተማሪዎች ትኩረታቸውን በደንብ ሰብስበው በጥሩ ሁኔታ እንዲማሩ ዕድል ሊሰጣቸው ይገባል። ሞባይል ስልኮች የመማር ማስተማሩን ተግባር እንደሚያስተጓጉሉ ከሳይንሳዊ ምርምር ውጤቶች እናውቃለን” ብለዋል።

የተለያዩ ጥናቶች የልጆችን የስክሪን ቆይታ ጊዜ መገደብ ከግንዛቤ እና ትኩረት መሻሻል ጋር እንደሚያያዝ አረጋግጠዋል።

ታብሌቶች እና ዘመናዊ ሰዓቶችን ጨምሮ ሌሎች የቴክኖሎጂ ውጤቶች በዚህ እገዳ ውስጥ ተካትተዋል።

መንግሥት እነዚህን የቴክኖሎጂ ውጤቶች ሙሉ በሙሉ ማገድን በተመለከተ ትምህርት ቤቶች ከመምህራን፣ ከወላጆች እና ከተማሪዎች ጋር በመምከር ተግባራዊ ሊያደርጉ እንደሚችሉም አስታውቋል።

ይህ ዕቅድ በሚኒስቴሩ፣ በትምህርት ቤቶች እና በባለድርሻ ተቋማት መካከል የተደረሰ ስምምነት መሆኑም ተገልጿል።

ዕቅዱ ተግባራዊ ከሆነ በኋላም በአውሮፓውያኑ 2024/2025 የትምህርት ዘመን መጨረሻ ምን ያህል ውጤታማ እንደሆነ ተገምግሞም በሕግ ይስፈር የሚለውም ውሳኔ ይደረስበታል።

ፊንላንድ በተመሳሳይ መልኩ የሞባይል ስልኮችን በመማሪያ ክፍሎች ውስጥ የሚያግድ ውሳኔ ባለፈው ሳምንት አስተላልፋለች።

የፊንላንድ መንግሥት በትምህርት ቤቶች ውስጥ ስልኮችን የማገዱን ሁኔታ ወጥ ለማድረግ ሕጉን እንደሚያሻሽል አስታውቋል።

ዩናይትድ ኪንግደም እና ፈረንሳይን ጨምሮ ሌሎች አገራትም የመማር ማስተማር ሁኔታውን ለማሻሻል የሞባይል ስልኮችን በመማሪያ ክፍሎች የማገድ ሃሳብ አቅርበዋል።