በአማራ ክልል በሁለት ቀናት በተለያዩ ቦታዎች ሦስት የአካባቢ ባለሥልጣናት ተገደሉ

የፎቶው ባለመብት, SM
ባለፉት ሁለት ቀናት በአማራ ክልል ውስጥ በሚገኙ ሁለት አካባቢዎች በታጣቂዎች በተፈጸሙ ጥቃቶች ሦስት የፀጥታ ባለሥልጣናት ተገደሉ።
ሰኞ እና ማክሰኞ በአማራ ክልል ውስጥ በሚገኙት በምሥራቅ ጎጃም ዞን ደጀን ወረዳ እና በሰሜን ሸዋ ዞን ሸዋ ሮቢት ከተማ ውስጥ ባሉ የአካባቢ የፀጥታ ኃላፊዎች ላይ ነው ግድያው የተፈጸመው።
የሸዋ ሮቢት ከተማ ፀጥታ ዘርፍ ኃላፊ የሆኑት የአቶ አብዱ ሁሴን ግድያን ተከትሎ የከተማዋ አስተዳደር አሉ ያላቸውን የፀጥታ ችግሮች ለመቆጣጠር በከተማዋ ውስጥ የሰዓት ዕላፊ እና የእንቅስቃሴ ገደብ ጥሏል።
በተለያዩ ሁለት ጥቃቶች ሁለት የፖሊስ ኃላፊዎች እና አንድ የፀጥታ ኃላፊ በተፈጸመባቸው ጥቃት መገደላቸውን ቢቢሲ ከዞኖቹ ባለሥልጣንት አረጋግጧል።
የደጀን ወረዳ አስተዳደር እንዳስታወቀው ሰኞ ሰኔ 26/2015 ዓ.ም. የወረዳው ፖሊስ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ዘውዱ ታደለ እና የወረዳው ፖሊስ ጽ/ቤት የወንጀል መከላከል ክፍል ኃላፊ ምክትል ኢንስፔክተር ወርቁ ሽመልስ በተፈጸመባቸው ጥቃት ተገድለዋል።
የወረዳው ምክር ቤት ባወጣው መግለጫ ከሁለቱ የፖሊስ ኃላፊዎች ላይ ከተፈጸማው ግድያ በተጨማሪ አብሯቸው የነበረ የፖሊስ አባል የሆነ ሹፌር የመቁሰል ጉዳት ደርሶበታል።
የደጀን ወረዳ ሰላም እና ፀጥታ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ካሳው አስፋው፣ ለቢቢሲ እንደተናገሩት በሁለቱ የፖሊስ ኃላፊዎች ላይ ግድያውን የፈጸመው የቀድሞ የልዩ ኃይል አባል ነው።
በተመሳሳይ ማክሰኞ ሰኔ 27/2015 ዓ.ም. በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ውስጥ በምትገኘው የሸዋ ሮቢት ከተማ ከፍተኛ ባለሥልጣን የሆኑት አቶ አብዱ ሁሴን ላይ በተፈጸመ ጥቃት መገደላቸው ተገልጿል።
የከተማው አስተዳደር ፀጥታ ዘርፍ ኃላፊ የሆኑት አቶ አብዱ ሁሴን የተገደሉት ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች መሆኑን የሸዋ ሮቢት ከተማ አስተዳደር በማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ ላይ አስፍሯል።
የሸዋ ሮቢት ከተማ አስተዳደር በአቶ አብዱ ላይ ግድያ ከመፈጸሙ ውጪ ምንም አይነት ዝርዝር መረጃ አልሰጠም።
ይህንን ግድያ ተከትሎ የሸዋ ሮቢት ከተማ ጊዜያዊ የፀጥታ ኮማንድ ፓስት ባሰራጨው አስቸኳይ መግለጫ በከተማዋ “ከፍተኛ የፀጥታ ችግር እንዲከሰት ጥረቶች እየተደረጉ ስለመሆኑ ማሳያዎች እየተስተዋሉ” በመሆናቸው ያለውን የፀጥታ ለማጠናከር የተለያዩ ክልከላዎች መጣላቸውን አሳውቋል።
በዚህም ላልተወሰነ ጊዜ ከምሽቱ 12 ሰዓት ጀምሮ ማንኛውም የተሽከርካሪም ሆነ የሰው እንቅስቃሴዎች የተገደቡ ሲሆን፣ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትም ከምሽት 12 ሰዓት በኋላ ምንም አይነት አገልግሎት እንዳይሰጡ በከተማዋ ውስጥ ክልከላ ተጥሏ።

አስካሁን በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች በፀጥታ ባለሥልጣናት ላይ ስለተፈጸሙት ግድያዎችም ሆነ እየተወሰዱ ስላሉት እርምጃዎች ያለው ነገር የለም።
ሰኞ ዕለት ከተሰጠው የስምንተኛ ክፍል ፈተና ጋር በተያያዘ በሥራ ላይ የነበሩት ሁለቱ የፖሊስ ኃላፊዎች በመንገዳቸው ላይ ባገኙት ሕገወጥ የጦር መሳሪያ በታጠቀ የቀድሞ የልዩ ኃይል አባል መገደላቸውን የደጀን ወረዳ ሰላም እና ፀጥታ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ካሳው አስፋው ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ጥቃት ፈጻሚው ማንነቱ መለየቱ የታወቀ ሲሆን አስካሁን ግን በቁጥጥር ስር አልዋለም። የአካባቢው የፀጥታ አካላትም ግለሰቡን ይዘው ለፍርድ ለማቅረብ ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን ኃላፊው ተናግረዋል።
በሸዋ ሮቢት ከተማ ውስጥ እንዲህ አይነቱ የባለሥልጣናት ግድያ ሲፈጸም ይህ የመጀመሪያው አይደለም። ባለፈው ዓመት ማብቂያ ላይ በከተማዋ የፀጥታ እና የደኅንነት መመሪያ መውጣቱን ተከትሎ የከተማዋ ከንቲባዋ መገደላቸው ይታወሳል።
ከንቲባው አቶ ውብሸት አያሌው ሐሙስ ነሐሴ 26/2014 ዓ.ም. ምሽት ሦስት ሰዓት ገደማ ነበር ከቤታቸው አቅራቢያ ባላታወቁ ሰዎች በተተኮሰባቸው ጥይት የተገደሉት።
ከሁለት ወራት በፊት ደግሞ የአገሪቱ ገዢ ፓርቲ ብልጽግና ሥራ አስፈጻሚ አባል እና የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ ግርማ የሺጥላ በታጣቂዎች መገደላቸው ይታወሳል።
ከፍተኛ ባለሥልጣኑ አቶ ግርማ ማንነታቸው ባልታወቁ ታጣቂዎች የተገደሉት ከዋና ከተማዋ አዲስ አበባ 250 ኪሎ ሜትር በስተሰሜን በሚገኝ ስፍራ ሚያዚያ 19/2023 ዓ.ም. ነበር።
ከአቶ ግርማ እና አብረዋቸው በነበሩ ሰዎች ላይ በተፈጸመው ጥቃት ቢያንስ አምስት ሰዎች መገደላቸው መዘገቡ አይዘነጋም።
የአቶ ግርማ የሺጥላን ግድያ ጨምሮ ባለፉት ሁለት ቀናት የበተለያዩ የአማራ ክልሎች ውስጥ ከተፈጸሙት የባለሥልጣንት ግድያ ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር የዋለም ሆነ በይፋ ኃላፊነቱን የወሰደ ወገን የለም።
በአገሪቱ ክልሎች ውስጥ የሚገኙ ልዩ ኃይሎች ወደ መደበኛ የፀጥታ ኃይል እንዲካተቱ እና ሌሎች የታጠቁ አካላትን ለመቆጣጠር እየተወሰዱ ካሉ እርምጃዎች ጋር በተያያዘ በክልሉ ውስጥ ግጭቶች መከሰታቸው ሲዘገብ ቆይቷል።












