“የልጄን ሕይወት በአንድ ሚሊዮን ብር ገዛሁ” ልጃቸውን ከእገታ ያስለቀቁ አባት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
መምህር አንለይ መኩሪያ ለአርባ ዓመታት በመምህርነት ሲያገለግሉ በሕይወት ዘመናቸው አንድ ሚሊዮን ብር የሚጠይቅ ፈተና ገጥሟቸው አያውቅም።
በመቶዎች ብር ክፍያ ከጀመሩት የመምህርነት ሙያቸውም በአራት አስርት ዓመታት አገልግሎታቸው ውስጥ በደሞዝ በቀጥታ እጃቸው የገባው ገንዘብ ቢታሰብ አንድ ሚሊዮን ሊደርስ ስለመቻሉም እርግጠኛ አይደሉም።
በዚህ ዓመት ሰኔ ወር መጀመሪያ ላይ ግን ባለሰቡት እና ባልጠበቁት ሁኔታ የበኩር ልጃቸውን ሕይወት ለመታደግ አንድ ሚሊዮን ብር ተጠይቀው በጡረታ ዘመናቸው ከማይወጡት ዕዳ ውስጥ ገብተዋል።
በአማራ ክልል፣ ምሥራቅ ጎጃም ዞን የአማኑኤል ከተማ ነዋሪ የሆኑት መምህር አንለይ “የልጄን ሕይወት በአንድ ሚሊዮን ብር ከአጋቾች ላይ ገዝቻለሁ” ሲሉ ይናገራሉ።
እገታው
በአሁኑ ወቅት የሰዎች በታጣቂዎች የመታገት ዜና እንግዳ መሆኑ ከቀረ ሰነባብቷል። ክስተቱም በተወሰኑ መጥፎ ዕጣ በገጠማቸው ሰዎች ላይ የሚከሰት ሳይሆን፣ በተለያዩ አካባቢዎች በተደጋጋሚ እና በብዛት የሚያጋጥም ስጋት ሆኗል።
ታጣቂዎች በዋና ከተማዋ አዲስ አበባ ዙሪያ በጥቂት መቶ ኪሎ ሜትሮች ውስጥ እገታዎችን እየፈጸሙ ማስለቀቂያ ከመቶ ሺዎች አስከ አንድ ሚሊዮን ብር እየጠየቁ አየተከፈላቸው ነው።
የመምህር አንለይ የበኩር ልጅ የሆነው አብርሃም አንለይም፣ ይህ ክፉ አጋጣሚ ከደረሰባቸው ግለሰቦች መካከል አንዱ ነው።
ባለትዳር እና በሹፌርነት ሥራ የሚተዳደረው አብርሃም፣ የራሱን እና የጡረተኛ ቤተሰቦቹን ኑሮ የሚደጉመው ከዚሁ ሙያው ከሚያገኘው ገቢ ነው።
የተለያዩ ጭነቶችን በመያዝ ከጎጃም አዲስ አበባ የሚመላለስበት መንገድ ዋነኛው የእንቅስቃሴው መስመር ነው። ከ10 ዓመታት በላይም በዚህ መስመር ተመላልሶ ሥራውን አከናውኗል። ሰኔ 10/2015 ዓ.ም. ግን እንደከዚህ ቀደሞቹ አልነበረም። በታጣቂዎች ታግቶ መንገድ ላይ ቀረ።
በዕለተ ቅዳሜ ሰኔ 10/2015 ዓ.ም. አብርሃም ከትውልድ ቦታው ምሥራቅ ጎጃም አማኑኤል ከተማ ተነስቶ ፍቼ ካደረ በኋላ፣ የማለዳ ጉዞውን የጀመረው ከንጋቱ 12፡00 ሰዓት አካባቢ ነበር።
በኦሮሚያ ክልል ከፍቼ ከተማ የተወሰነ ርቀት እንደተጓዙ አሊዴሮ ከተባለ ቦታ ላይ ግን እርሱ እና ጓደኞቹ ያልጠበቁት ነገር ገጠማቸው። ታጣቂዎች ከ30 በላይ ተሽከርካሪዎችን አስቁመው ፍተሻ ያደርጋሉ።
በኪሳቸው የያዙትን ገንዘብ እና የእጅ ስልክ ቀሟቸው። የብዙዎቹ ተስፋ ሁኔታው በዝርፊያ የሚቋጭ መስሏቸው ነበር። ታጣቂዎቹ ግን በቀሙት ነገር አልረኩም። ሹፌሮቹን እና ረዳቶቻቸውን አግተው ወደ ጫካ ይዘዋቸው ሄዱ።
ገንዘብ ማፈላለግ
ከአዲስ አበባ 160 ኪሎ ሜትሮች አካባቢ ርቆ በሚገኘው አካባቢ ለተፈጸመው የበርካታ አሽከርካሪዎች እና ረዳቶቻቸው እገታ ኃላፊነትን የወሰደም ሆነ ማንነቱ የታወቀ ቡድን አስካሁን የለም።
ለሥራ ከቤቱ የወጣው አብረሃም እና ሌሎችም ሲታገቱ የሚያሽከረክሯቸው መኪኖቻቸውን መንገድ ዳር ትተው ነው በጠመንጃ አፈሙዝ ተገደው ወደ ጫካ የተወሰዱት።
አብረሃም እንደታገተ ባገኘው ስልክ የመደወል ዕድል መጀመሪያ የደወለው ቀጥሮ ለሚያሰራው ለመኪናው ባለቤት ነበር። እርሱም በታጣቂዎች መታገቱን፣ ለመለቀቅም 1 ሚሊዮን ብር ታጠቂዎቹ እንደሚፈልጉ እና ተሽከርካሪውን ከቆመበት እንዲወስድ ነገረው።
የአብርሃም ቤተሰቦች በተለይም አባቱ መምህር አንለይ የልጃቸውን መታገት የሰሙት በሦስተኛ ወገን በኩል ነበር። የበኩር ልጃቸው የታገተባቸው አባት፣ ለልጃቸው ስልክ ደውለው ራሱን ለማግኘት ቢጥሩም የሚሳካ አልሆነም።
ከእገታው ለማስለቀቅ የተጠየቁት ገንዘብ 1 ሚሊዮን ብር መሆኑን መስማታቸው ደግሞ ሰማይ በላያቸው ላይ የተደፋባቸው ያህል ስሜትን በእሳቸው እና በቤተሰባቸው ላይ ፈጠረ።
በዚህ ዓመት ለረጅም ጊዜ ካገለገሉበት የመምህርነት ሙያ ጡረታ የወጡት መምህር አንለይ፣ አንድ ሚሊዮን ብር ሊኖራቸው ይቅር እና ለራሳቸው ኑሮም ተጨማሪ ድጎማ የሚያገኙት ከዚሁ ከታጋች ልጃቸው ነበር።
ከእገታው ሁለት ቀን በኋላ ሰኞ ሰኔ 12/2015 ዓ.ም. ጠዋት ላይ በተደወለ ስልክ ለመጀመሪያ ጊዜ ከልጃቸው ጋር እንደተገናኙ ይናገራሉ መምህር አንለይ።
“ምንም የማደርገው ስላልነበረኝ ወደ ሰማይ እያንጋጠጥኩ እስከ ማክሰኞ ስብሰለሰል ቆየሁ” የሚሉት መምህር አንለይ፣ ማክሰኞ ግን ጎረቤት እነርሱን በማረጋጋት የቻለ ገንዘብ በመርዳት፣ ያልቻለ ደግሞ አበዳሪ በማፈላለግ ርብርብ ማድረግ ጀመረ።
የአንድ ልጅ አባት የሆነው ባለትዳሩ የጧሪ ልጃቸው ሕይወት በአንድ ሚሊዮን ብር አይተመንም ያሉት መምህር አንለይ፣ ልጃቸውን ካጋቾቹ ለመታደግ አይገቡበት ዕዳ ውስጥ ለመግባት ቆረጡ።
የማይወጡት ዕዳ
በአማኑኤል ከተማ ነዋሪ የሆኑ እና የማስለቀቂያ ገንዘብ የተጠየቀባቸው የመምህር አንለይ ልጅን ጨምሮ ወደ ሰባት የሚደርሱ ሰዎች በአጋቾቹ እጅ በመውደቃቸው ከተማዋ በሐዘን ድባብ ውስጥ ሰንብታለች።
አጋቾቹ ለአንዳንዶቹ ማስለቀቂያ 500 ሺህ ብር ሲጠይቁ፣ ለሌሎቹ ደግሞ አንድ ሚሊዮን ብር በመጠየቃቸው የቤተሰባቸው አባል በታጣቂዎች የተያዘባቸው ሰዎች ጎዳና ላይ ነጠላ ዘርግተው መዋጮ አስከመሰብሰብ ደርሰዋል።
የሕግ አካላት ጣልቃ ከመግባታቸው በፊት ታጣቂዎች የጠየቁትን ገንዘብ በመስጠት የተለቀቁ ሰዎች እንዳሉ መስማታቸው እና ቀናት እየተቆጠሩ ሲሄዱ ልጃቸውን ሊያጡት እንደሚችሉ የሰጉት መምህር አንለይ፣ የወዳጅ ዘመዶቻውን ደጅ ጠኑ።
ከተጠየቀው የማስለቀቂያ ገንዘብ ውስጥ እዚህ ግባ የሚባል ብር እጃቸው ላይ የሌላቸው መምህር አንለይ፣ በእርዳታ ያገኙት ገንዘብ አንድ መቶ ሺህ ብር ብቻ ነበር። ቀሪው 900 ሺህ ብር ግን የልጃቸውን ሕይወት ለመታደግ የገቡበት ዕዳ ነው።
“ጎረቤቶቼ ከልጅ የሚበልጥ ነገር የለም ብለው ‘ቤትህንም ቢሆን ሽጠህ ትከፍላለህ’ በማለት እስከ ሐሙስ 1 ሚሊዮን ብር አሰባስበው ሞሉልኝ” ይላሉ መምህር አንለይ።
ለመምህር አንለይ ቀጣዩ ፈተና ደግሞ ይህንን ገንዘብ “ለአጋቾቹ እንዴት ነው የማደርሰው” የሚለው ነው። ከአጋቾቹ ጋር መጠኑን እንዲቀንሱላቸው ብዙ ጊዜ ለምነው አልተሳካም። ብሩን እስኪሰበስቡ ጊዜ እንዲሰጧቸውም ጠይቀዋቸው አልሆነም።
አሁን የመጨረሻ ልመናቸው ገንዘቡን በባንክ እንዲቀበሏቸው ነበር። ጠየቁ። በዚህ በኩል አጋቾቹ በፍጹም የሚለመኑ አልሆኑም።
ገንዘቡን በአካል እጅ በእጅ መቀበል እንደሚፈልጉ አስረግጠው ነገሯቸው። የመቀባበያ ቦታም አብርሃም ከታገተበት ቦታ አቅራቢያ ገርበ ጉራቻ አካባቢ መሆኑን ነገሯቸው።
አንድ ሚሊዮን ብር በዘንቢል
አማራጭ ያልነበራቸው መምህር አንለይ፣ የበኩር ልጃቸውን ከእገታ ለማስለቀቅ በጎረቤቶቻቸው መልካም ትብብር እና በብድር የተሰበሰበውን 1 ሚሊዮን ብር ተሸክመው ወደ ገርበ ጉራቻ ተጓዙ።
“ልክ ልጄ በታገተ በሳምንቱ ቅዳሜ፣ 1 ሚሊዮን ብሩን ዘንቢል ውስጥ ካደረግኩ በኋላ በማደበሪያ ተሸክሜ ወደማላውቀው ቦታ ሄድኩ።”
ገርበ ጉራቻ ከደረሱ በኋላ አስተርጓሚ ቀጥረው ከከተማው 7 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደሚገኝ ቦታ ብሩን ተሸክመው ሄዱ። ከዚያች ቦታ እንደደረሱ አንድ ግለሰብ ሲጠብቃቸው አገኙ። ለአጋች ነኝ ላለው ሰው ሲደውሉ ብሩን የሚቀበለው ይህ ግለሰብ መሆኑን ነገራቸው።
ይህ ሲሆን ግን አሁንም ልጃቸው የት እንዳለ አያውቁም። ተስፋ ያደረጉት ብሩን እንደሰጡት ልጃቸው በዚያው አቅራቢያ እንደሚለቀቅላቸው ነበር። ሰውዬው የሰጣቸው መልስ ግን የበለጠ ስጋት የሚያጭር ነበር።
“ገንዘቡን ፈትተን አሳይተን አስረከብነው። ብሩ ከሰባት ሰዓት ጉዞ በኋላ ዋናዎቹ አጋቾች ጋር ይደርሳል። ከዚያ በኋላ ብሩ ተቆጥሮ አድሮ ሙሉ መሆኑ ከተረጋገጠ በኋላ ይነገርሃል ብለው ሸኙኝ” ይላሉ መምህር አንለይ።
“ሲሞላላችሁ ደውሉ”
የአጋቾቹ ዋነኛ ግብ በቁጥጥራቸው ስር ባሉት ሰዎች መያዣነት ከቤተሰቦቻቸው ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ መሰብሰብ ነው። በእገታው መጀመሪያ ላይ በቶሎ ገንዘቡን ካላገኙ በእጃቸው ባሉት ታጋቾች ላይ “እርምጃ” እንደሚወስዱ በስልክ ሲያስጠነቅቁ ቆይተዋል።
መምህር አንለይ እንደሚሉትም በየዕለቱ ልጃቸውን እንዲደውል እያደረጉ በቶሎ ገንዘቡን እንዲያመጡ ይወተውቷቸው የነበረ ሲሆን፣ በጠየቁት ገንዘቡ ከፍተኛነት እና ሌሎች ከዚያም ከዚህም ብለው ሲከፍሉ “ሲሞላላችሁ ደውሉ” ይሏቸው ነበር።
መምህር አንለይ እና የሌሎች ታጋች ቤተሰቦች በዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥ ከአጋቾቹ ጋር ስለሚያደርጉት ግንኙነትም ሆነ ስለተጠየቁት ገንዘብ ለማሳወቅ ከፀጥታ አካላት ጋር ምንም አይነት ግንኙነት አላደረጉም።
ለዚህም አንደኛው ምክንያት ፖሊስ በጉዳዩ ውስጥ ከገባ ታጋቾቹ በታጣቂዎቹ ሊገደሉ ይችላሉ የሚል ሲሆን፣ ሌላኛው ጉዳዩ አገር ያወቀው፣ ፀሐይ የሞቀው በመሆኑ ከመንግሥት ኃይሎች የተሰወረ ነው ብለው ባለማመናቸው ነው።
አልነጋ ያለው ሌሊት
መምህር አንለይ ሌሎች ታጋቾች ገንዘብ ከፍለው በሰላም ከቤተሰባቸው ጋር መቀላቀላቸውን ሲሰሙ፣ ከመምህርነት ጡረታቸው በሚያገኙት ገንዘብ ቀርቶ መኖሪያ ቤታቸውን እንኳን ቢሸጡ ከማይመልሱት ዕዳ ውስጥ ገብተው የልጃቸውን ሕይወት ለማትረፍ ወስነዋል።
የሰበሰቡትን አንድ ሚሊዮን ብሩም ቅዳሜ ዕለት ከአንድ ጫካ ውስጥ የታጣቂዎቹ ወኪል ነው ለተባለ የማያውቁት ሰው አስረክበው፤ ብሩ ሙሉ ከሆነ በነጋታው ልጃቸውን እንደሚያገኙት ተነግሯቸው በአቅራቢያ ወደ ምትገኘው ፍቼ ከተማ ተመልሱ።
ለመምህር አንለይ ከቀናት ሁሉ አስጨናቂዋ ቀን ይህች ዕለት ነበረች። አንደኛ ሰውዬውን ሙሉ በሙሉ ማመን ከበዳቸው፣ በሌላ በኩል ደግሞ በመንገድ ላይ ሌላ አጋች ይህንን ሰው ብሩን ቢቀማውስ? በተጨማሪ ደግሞ ታጣቂዎቹ ብሩን ካገኙ በኋላ ልጄን ያልሆነ ነገር ቢያደርጉትስ? የሚሉ ጥያቄዎች እረፍት ነስቷቸው ነበር።
“ደውለው እስከሚነግሩኝ ድረስ ቤርጎ ውስጥ ቁጭ ብዬ እያለቀስኩ፣ ምግብ ሳልበላ እስከ ሌሊቱ 8 ሰዓት ድረስ ቆይቻለሁ” በማለት አስጨናቂ ነበረች ያሏትን ሌሊት ያስታውሳሉ።
በማግስቱ ልጃቸው የሚለቀቅበት ቀን ነው። በጠዋት ይለቀቃል ተብለዋል። ነገር ግን የታገተበት ቦታ ደግሞ የሰባት ሰዓት የእግር መንገድ ያስኬዳል። በመሆኑም ቢያንስ እስከ ቀኑ 7 ሰዓት ድረስ መጠበቅ ነበረባቸው። ቀኑ በጣም ቢረዝምም እንደምንም ያቺ ተጠባቂ ቅጽበት ደረሰች። በመጨረሻም ልጃቸው ከእገታው ተለቆ በአካል ሊያገኙት በቁ።
“በአንድ ሚሊዮን ብር ነፍሱን የገዛሁት ልጄ፣ ረጅም ርቀት የተጓዘበት ጫማው ተቀዶ እና እግሮቹ አባብጠው ሳገኘው እንደገና እንባዬን መቆጣጠር አቃተኝ። የአገሩ ሰው እስኪገረም ድረስ ተንሰቅስቄ አለቀስኩ” ይላሉ።
የወደፊቱ ስጋት
በምሥራቅ ጎጃም ዞን ውስጥ በምትገኘው የአማኑኤል ከተማ ውስጥ ብቻ ከእርሳቸው ልጅ ጋር ሰባት ሰዎች ታግተው ነበር። እንደመምህር አንለይ ከሆነ አጋቾቹ የተለያዩ ቡድኖች ናቸው።
በመሆኑም እነዚህ ቡድኖች ታጋቾቹን ለማስለቀቅ የሚጥሉት የገንዘብ መጠን ከቡድን ቡድን ይለያያል። ለምሳሌ ከእርሳቸው ልጆች ውጪ የታገቱት ስድስቱ ከተማዋ ነዋሪዎች የተጣለባቸው ተመን 500 ሺህ ብር ነው።
የእርሳቸውን ልጅ እና ሌሎች 21 ሰዎችን ያገቱት ታጣቂዎች ግን ከእያንዳንዳቸው 1 ሚሊዮን ብር ነበር ለማስለቀቂያነት የጠየቁት።
መምህር አንለይ ቀጣይ መኖሪያ ቤታቸውን ሸጠው ለመክፈል 100 ሺህ በእርዳታ፣ 900 ሺህ ብር ደግሞ በብድር አሰባስበው በ1 ሚሊዮን ብር ልጃቸውን አስፈትተዋል። ነገር ግን ያልተመለሰ ጥያቄ አላቸው።
መንግሥት እና ሕግ ባለበት አገር “የአሁኑን በእዚህ ሁኔታ ፈታነው። ቀጣይስ? ልጄ ድጋሚ ላለመታገቱ ምን ዋስትና አለኝ? ሥራ አቁም እንዳልለው አቅም የለኝም። እንዲያውም ከፍተኛው ስጋቴ የወደፊቱ ነው” ይላሉ።
የመምህር አንለይ ልጅን ጨምሮ በርካታ አሽከርካሪዎች እና ረዳቶች ስለታገቱበት እንዲሁም ብዙዎቹም የተጠየቁትን ገንዘብ ከፍለው የተለቀቁባቸውን እና እየተደጋገሙ ስለመጡት የእገታ ድርጊቶች፣ አስካሁን ከመንግሥት በኩል የተባለ ነገር የለም።












