የኮሎምቢያው ሽምቅ ተዋጊ ቡድን ከ60 ዓመታት ጦርነት በኋላ ለተኩስ አቁም ተስማማ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኮሎምቢያ መንግሥት እና ሽምቅ ተዋጊው ቡድን ከስልሳ ዓመታት ጦርነት በኋላ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ደረሱ።
ይህም ሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች ወደ እርቅ ለመምጣት ያደረጉት የመጀመሪያው እርምጃም ነው ተብሏል።
የኮሎምቢያው ብሔራዊ ነጻ አውጪ ጦር (ኢኤልኤን) ከዛሬ ረቡዕ ጀምሮ ውጊያ እንደሚያቆም አስታውቋል።
ከነሐሴ ጀምሮም ግጭትን በዘላቂነት ለማቆም ስምምነት ላይ መድረሳቸውም ተገልጿል።
የኮሎምቢያ መከላከያ ሚኒስቴር የታጣቂ ኃይሉ አባላት ከዚያን ወቅት ጀምሮ ውጊያ እንዲያቆሙ እንደሚነገራቸው አረጋግጠዋል።
ሆኖም ኢኤልኤን ከኮሎምቢያ ጦርም ሆነ ከሌሎች ታጣቂ ቡድኖች ጥቃት የሚሰነዘርበት ከሆነ ራሱን እንደሚከላከል አቋሙን ገልጿል።
ሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች ባለፈው ሳምንት ለስድስት ወራት የሚቆይ የተኩስ አቁም ስምምነትም ላይ መድረሳቸው የተገለጸ ሲሆን፣ ይህም ነሐሴ መጀመሪያ ላይ ተግባራዊ ይሆናል።
በሁለቱ ኃይሎች መካከል የተደረገው ይህ ስምምነት ከጸናም ለስድስት አስርት ዓመታት የቆየው ረጅሙ ጦርነት ማክተሚያ ይሆናል።
ኢኤልኤን ነፍጥ አንስቶ መታገል የጀመረው ከአውሮፓውያኑ 1964 ጀምሮ ነው።
ነገር ግን ይህ ተኩስ አቁም ስምምነት ስለመጽናቱ ጥርጣሬዎች መነሳታቸው አልቀረም። የኢኤልኤን አባላት የተኩስ አቁም በታወጀበት ዕለት በሰሜን ምሥራቅ ኮሎምቢያ ሦስት ፖሊሶችን ገድለዋል።
በተጨማሪም ከሳምንት በፊት የመንግሥት ኃይሎች በአገሪቱ ምሥራቃዊ ክፍል ስድስት የታጣቂውን ወታደሮች ገድለዋል።
የኮሎምቢያው ፕሬዝዳንት ጉስታቮ ፔትሮ የቀድሞ አማጺ ቡድን የነበረው ኤም 19 አባል የነበሩ ሲሆን፣ ባለፈው ዓመትም ወደ ሥልጣን ሲመጡ በፕሬዚዳንትነት ዘመናቸው ለአገሪቱ “ፍጹም ሰላም” ለማምጣት ቃል ገብተዋል።
ፕሬዚዳንቱ የተኩስ አቁም አዋጁን ከሰሞኑ እንደሚፈርሙም የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
የሽምቅ ተዋጊው ቡድን እና የኮሎምቢያ መንግሥት ከነሐሴ ወር ጀምሮ በቬንዙዌላ የሰላም ድርድር ለማድረግም አቅደዋል።












