“የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል” በሚል 12ኛ ክልል ተመሠረተ

የደቡብ ኦሞ ዞን ሕዝቦችም በአዲስ በተመሠረተው ክልል ውስጥ የሚካተቱ ይሆናል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የደቡብ ኦሞ ዞን ሕዝቦችም በአዲስ በተመሠረተው ክልል ውስጥ የሚካተቱ ይሆናል

በኢትዮጵያ 12ኛው አዲስ ክልል “የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል” በሚል ስያሜ ተመስርቶ የፌዴሬሽኑ አባል በመሆን ተቀላቀለ።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ዛሬ ሰኔ 28/2015 ዓ.ም. ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ አዲሱ ክልል “የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል” ሆኖ እንዲደራጅ ውሳኔ አስተላልፏል።

በዚህ ክልል ውስጥ የሚካተቱት ከዚህ ቀደም በደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ውስጥ ተካተው የነበሩ ስድስት ዞኖች እና አምስት ልዩ ወረዳዎች ናቸው።

ምክር ቤቱ እንዳስታወቀው የጌዴኦ፣ የወላይታ፣ የጋሞ፣ የጎፋ፣ የኮንሶ እና የደቡብ ኦሞ ዞኖች እንዲሁም የቡርጂ፣ የአማሮ፣ የዲራሼ፣ የባስኬቶ እና የአሌ ልዩ ወረዳዎች ናቸው የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በሚል ስያሜ እንዲዳራጅ የተወሰነው።

እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ስድስት ዞኖች እና አምስት ልዩ ወረዳዎች ከዚህ ቀደም በአንድ ክልል የመደራጀት ፍላጎት ነበራቸው ተብሏል።

በቅርቡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የወላይታ ዞንን ጨምሮ ሌሎች 6 ዞኖች እና 5 ልዩ ወረዳዎች በጋራ በአንድ ክልል ለመመሥረት የቀረበው ሕዝበ ውሳኔ በወላይታ ሕዝባዊ ይሁታን ስለማግኘቱ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

ዛሬ መመሥረቱ በይፋ የተገለጸው “የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል” ከደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ወጥቶ ራሱን የቻለ ሦስተኛው ክልል ሆኗል።

ሲዳማ እና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች ከዚህ ቀደም ከደቡብ ብሔር፣ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ተነጥለው ራሳቸውን የቻሉ ክልሎች መሆናቸው ይታወሳል።

ከ25 ዓመታት በፊት በአገሪቱ ቋንቋን እና ማንነትን መሠረት ያደረገው ፌደራላዊ አወቃቀር ተግባራዊ ሲደረግ አምስት እራሳቸውን የቻሉ ክልሎች የነበሩት አካባቢዎች እንዲዋሃዱ እና የደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል በሚል እንዲዋቀሩ ተደርገዋል።

ነገር ግን በአገሪቱ ካሉት ከ80 ከሚበልጡ ብሔር ብሔረሰቦች መካከል አብዛኞቹ ይገኙበታል በሚባለው ክልል ውስጥ ያሉ ማኅበረሰቦች የራሳቸውን ክልሎች ለመመስረት ሲጠይቁ መቆየታቸው ይታወሳል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ በክልሉ ውስጥ ካሉት ሁሉም ዞኖች በሚያስብል ሁኔታ ከደቡብ ክልል በመውጣት የተናጠል ክልል ለመመሥረት በምክር ቤቶቻቸው አማካይነት ውሳኔ አሳልፈው ነበር።

ከ50 በላይ ብሔር፣ ብሔረሰቦችን የያዘው የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ከአገሪቱ ትልቅ ከሚባሉት ክልሎች መካከል አንዱ ሆኖ የቆየ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ወደ አራት ተከፍሏል።

የሲዳማ ክልል ከደቡብ ክልል በወጣውት ቀዳሚ ሲሆን ተከትሎም የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ተመስርቷል። አሁን የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል እንዲመሠረት የተወሰነ ሲሆን ነባሩ ክልል የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ተብሎ ይቀጥላል።

በዚህም ሳቢያ ዘጠኝ የነበሩት የአገሪቱ ፌደራል ክልሎች ቁጥራቸው ወደ 12 ከፍ ብሏል።

ነገር ግን አዲስ በተዋቀሩት ክልሎች ውስጥ ያሉ ነዋሪዎች እና ፖለቲከኞች አሁንም የራሳቸውን ክልላዊ መስተዳደር ለመመሥረት ጥያቄ እያረቡ ነው።