በኬንያ የወሊድ መጠን ቀነሰ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ባለፉት 10 ዓመታት ኬንያውያን ሴቶች የሚወልዱትን የልጆች ቁጥር እየቀነሱ መሆኑን ጥናት አሳየ።
እአአ 2014 ላይ አንድ ኬንያዊት ሴት በአማካይ 3.9 ልጆቸን ትወልድ ነበር። የኬንያ የሥነ ሕዝብ ጤና የዳሰሳ ጥናት እንዳሳየው ግን በ2022 አንዲት ሴት በአማካይ የምትወልደው የልጆች ቁጥር ወደ 3.4 ዝቅ ብሏል።
ይህ ማለት በአሁኑ ወቅት ዕድሜያቸው በ15 እና 49 መካከል ያሉ ኬንያውያን ሴቶች ከአራት ልጆች ይልቅ ሦስት ልጆች የመውለድ ፍላጎት አላቸው።
እአአ 1989 ላይ የነበረው አሃዝ አንዲት ኬንያዊት ሴት በአማካይ 7 ልጆች ገደማ ትወልዳለች የሚል ምጣኔን ነበር የሚያሳየው።
የጤና ባለሙያዎች ሰዎች የእርግዝና መከላከያ ዘዴዎችን በቅርባቸው ማግኘታቸው የመውለድ መጠኑ እንዲቀንስ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል ይላሉ።
ከዚህ በተጨማሪም ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ሴቶች ከፍተኛ ትምህርት ፍለጋ ልጆች የሚወልዱበትን ጊዜ ያራዝማሉ።
በሪፖርቱ ላይ ለውልደት መጠን መቀነስ የተቀመጠው ሌላኛው ምክንያት የኑሮ ውድነት መጨመር ሰዎች ተጨማሪ ልጅ እንዳይወልዱ አያበረታታም የሚል ነው።
የኬንያ መንግሥት ግን ምንም እንኳን የውልደት መጠን መቀነስ ቢያሳይም፤ የሕዝብ ቁጥር መጨመሩ ይቀጥላል ይላል።
የውልደት ምጣኔ በአገር ምጣኔ ሃብታዊ እድገት ላይ ቀጥተኛ ሚና አለው።
የጥናት ውጤቶች እንደሚያሳዩት ገና በማደግ ላይ ያሉ አገራት ከበለጸጉት አገራት ጋር ሲነጻጸሩ ከፍተኛ የውልደት መጠን አላቸው።
እንደ የዓለም ባንክ አሃዝ ከሆነ አንጎላ፣ ናይጄሪያ እና ኡጋንዳ በአፍሪካ ከፍተኛ የውልደት መጠን ያላቸው አገራት ናቸው።












