የዓለማችን ሞቃታማው ቀን ተመዘገበ

ሞቃት ቀን

የፎቶው ባለመብት, STR

የዓለም ሙቀት መጠን መመዝገብ ከተጀመረበት በኋላ ከፍተኛው ሙቀት ተመዘገበ።

የዓለማችን ከፍተኛው አማካይ ሞቃት ቀን ለመጀመሪያ ጊዜ የተመዘገበው ሰኔ 26 ቀን 2015 ዓ. ም. ነው።

አሜሪካውያን አጥኚዎች እንዳሉት ይህ ሞቃት ቀን ምዝገባው ከተጀመረበት የ19ኛው ክፍለ ዘመን ማገባደጃ ወዲህ ከፍተኛው ነው።

ሳይንቲስቶች እንደሚሉት ለሞቃቱ ቀን መንስኤው ኤል ኒኖ የሚባለው ሞቃት የአየር ሁኔታና የሰው ልጆች የካርቦን ዳይኦክሳይድ ልቀት መብዛት ነው።

ባለፈው ወርም የዓለም ሞቃቱ ቀን ተመዝግቧል።

በአሜሪካ ብሔራዊ የከባቢ አየር ትንበያ ማዕከል የሚሠሩ ሳይንቲስቶች እንደሚሉት፣ ያሳለፍነው ሰኞ የዓለም አማካይ ሙቀት 17.01 ሴልሸስ ሆኗል።

ከዚህ ቀደም ከፍተኛው ተብሎ የተመዘገው እአአ በ2016 ነሐሴ ላይ 16.92 ሴልሸስ ነበር።

ይህ ዓመት ከገባ አንስቶ ተመራማሪዎች በመሬትና በባሕር ያለውም የሙቀት መጠን መጨመር አስግቷቸዋል።

የፀደይ ከፍተኛው ሙቀት በስፔንና በሌሎችም በርካታ የእስያ አገራት ተመዝግቧል። ከዚህ ቀደም ከፍተኛ ሙቀት ባልታየባቸው አካባቢዎችም የሙቀት ወጀቦች ተነስተዋል።

ቻይና በዚህ ሳምንት ከፍተኛ ሙቀት የገጠማት ሲሆን እስከ 35 ሴልሸስ የደረሰባቸው አካባቢዎች አሉ። አሜሪካ ውስጥም ተመሳሳይ ነገር ገጥሟል።

በሳተላይት የዓለምን ሙቀት መመዝገብ የተጀመረው እአአ በ1979 ሲሆን ሳይንቲስቶች እንደሚሉት፣ ያለፈው ሰኞ ሙቀት በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ከታዩት እጅግ የከፋው ነው።

ለዚህ አንድ መንስኤ የተባለው ኤል ኒኖ ሙቀት፣ ቀዝቃዛና አማካይ ደረጃዎች አሉት። በምድር ከፍተኛ የአየር ሁኔታ መዋዠቅ ከሚታይባቸው አንዱ እንደሆነም ይገለጻል።

የአየር ንብረት አጥኚው ሊዮን ሳይመንስ እንደሚለው፣ የዓለም አማካይ ሙቀት 17 ሴልሸስ መድረሱ እየሞቀ ለመጣው ዓለም አዲስ ከፍተኛ ጣሪያ ሆኖ ይወሰዳል።

“ኤል ኒኖ ሙቀት ደረጃ ላይ ደርሷል። ስለዚህ በቀጣዩ ዓመት ተኩል በየቀኑ፣ በየወሩና በየዓመቱ ሙቀት እንደሚጨምር መጠበቅ አለብን” ብሏል።

ይሄኛው ሰኔ በዓለም ሞቃቱ ወር ተብሎ ተመዝግቧል።

ከ1850 እስከ 1900 ድረስ የዓለም አማካይ ሙቀት 1.46 ሴልሸስ ነበር።

ኤል ኒኖ እየጠነከረ ሲሄድ ተጨማሪ ሞቃት ቀናት እየተመዘገቡ እንደሚሄዱ ሳይንቲስቶች ይናገራሉ።

በሊፕዚግ ዩኒቨርስቲ የምትሠራው ካርስተን ሃውስተን “ሐምሌ ከፍተኛው ሙቀት የሚመዘገብበት ወር የሚሆንበት ዕድል ሰፊ ነው። ይህም ከ120 ሺህ ዓመታት በፊት ከነበረው የከፋ የሙቀት ዘመን ኤምሪን የከፋ ነው” ትላለች።