ትራምፕ በርካታ የመንግሥት መሥሪያ ቤት መርማሪዎችን ማባረራቸው ቁጣ ቀሰቀሰ

ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ዲሞክራቶች ለትራምፕ በላኩት ደብዳቤ "ስጋት እንደገባቸው" ተናግረዋል

የትራምፕ አስተዳደር ባለፈው አርብ በርካታ የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤት መርማሪዎችን ማባረሩ ተዘገበ።

ይህ የትራምፕ አስተዳደር ውሳኔ ከፍርድ ቤት ፈተና ሊገጥመው እንደሚችል ተገምቷል።

የአሜሪካ ሴኔት የአናሳዎች መሪ የሆኑት ቻክ ሹመር መርማሪዎቹ መባረራቸው "ዶናልድ ትራምፕ ተጠያቂነት እንደሚፈሩ የሚያመለክት እና ግልፀኝነትን የሚፈታተን ነው" ብለዋል።

ዋይት ሐውስ እስካሁን ስለመርማሪዎቹ መባረር አስተያየት አልሰጠም። ከቢቢሲ ለቀረበለት ጥያቄም ምላሽ ከመስጠት ተቆጥቧል።

ከሥራቸው የተባረሩ የፌዴራል መሥሪያ ቤቶች መርማሪዎች በኢሜል "ቅድሚያ የምንሰጠው ነገር በመቀየሩ ከአሁን ሰዓት ጀምሮ ከኃላፊነትዎ ተነስተዋል" የሚል መልዕክት እንደደረሳቸው በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር የሆነው ሲቢኤስ ዘግቧል።

የጤና ሚኒስቴር እንዲሁም የአነስተኛ ቢዝነሶች አስተዳደር መርማሪዎች ከሥራቸው ከታገዱት መካከል ናቸው።

ኒው ዮርክ ታይምስ በዘገባው የግብርና ሚኒስቴር፣ የንግድ፣ የጤና፣ መከላከያ፣ ትምህርት፣ ቤቶችና ከተማ ልማት፣ የትራንስፖርትና የሀገር ውስጥ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች መርማሪዎች ከሥራቸው ሊታገዱ ይችላሉ ብሏል።

የትራምፕ አስተዳደር ከሥራቸው ባገዳቸው ሰዎች ምትክ ማንን ሊሾም እንደሚችል ግልፅ አይደለም።

ኢንስፔክተር ጄኔራል ተብለው የሚጠሩት እኒህ የመንግሥት መሥሪያ ቤት መርማሪዎች ገለልተኛ ሲሆኑ የአስተዳደር ብልሹነት እና ሥልጣን ያለአግባብ መጠቀምን ለመቆጣጠር የሚሾሙ ናቸው።

ምንም እንኳ መርማሪዎቹ በፕሬዝደንቱ ታጭተው በሴኔቱ የሚሾሙ ቢሆንም ከማንኛውም አካል ተፅዕኖ ነፃ መሆን ይጠበቅባቸዋል።

ተንታኞች የትራምፕ አስተዳደር መርማሪዎቹን ማባረሩ ሕጋዊ አይደለም ምክንያቱም ለኮንግረሱ የ30 ቀን ማሳሰቢያ እና የማባረሪያ ምክንያተ ማቅረብ ይጠበቅበታል ይላሉ።

የአነስተኛ ቢዝነሶች አስተዳደር መርማሪ እና የፌዴራል መሥሪያ ቤት መርማሪዎች ምክር ቤት ኃላፊ የሆኑት ሃኒባል ከሥራቸው መታገዳቸውን ተከትሎ በፃፉት ደብዳቤ "ድርጊቱ ሕጋዊ አይደለም" ብለዋል።

ዲሞክራቶች መርማሪዎቹ ከሥራቸው መታገዳቸውን ተከትሎ ፕሬዝደንቱን ተችተዋል።

ቻክ ሹመር እንዳሉት ይህን እርምጃ ትራምፕ እና አስተዳደራቸው ሊያራምዱ ያሰቡትን "ሕግ የጣሰ አካሔድ" የሚያሳይ ነው።

የቨርጂኒያ ግዛት የሕዝብ ተወካይ የሆኑት ዲሞክራቱ ጌሪ ኮኖሊ ይህ "ግልፀኝነት እና ተጠያቂነት ላይ የተከፈተ ጥቃት ነው" ብለዋል።

እሳቸውን ጨምሮ 20 የኮንግረስ አባል የሆኑ ዲሞክራቶች ለትራምፕ በላኩት ደብዳቤ በእርምጃው "ስጋት" እንደገባቸው ጠቅሰው ፕሬዝደንቱ ውሳኔያቸውን እንዲያጤኑት አሳስበዋል።

"ድርጊትዎ ሕግ የጣሰ፣ ዲሞክራሲያችን ላይ ጥቃት የሰነዘረ እና የአሜሪካዊያንን ደኅንነት አደጋ ላይ የጣለ ነው" ይላል ደብዳቤው።

የተወሰኑ የሪፐብሊካን ፓርቲ አባላትም የፕሬዝደንቱን ድርጊት ኮንነዋል።