ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ ግሪንላንድን "እንደምትቆጣጠር" ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የዴንማርክ ግዛት የሆነችውን ግሪንላንድ በቁጥጥራቸው ሥር እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
ፕሬዝደንቱ ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ግሪንላንድን መጠቅለል እንደሚፈልግ ሲናገሩ ቆይተዋል።
ባለፈው ሳምንት የዴንማርክ ጠቅላይ ሚኒስትር ሜቴ ፍሬድሪክሰን ከዶናልድ ትራምፕ ጋር ባደረጉት የተካረረ የስልክ ልውውጥ ግሪንላንድ ለገበያ አትቀርብም ማለታቸውን ዘገባዎች ጠቁመዋል።
ትራምፕ ግሪንላንድ ገዝተው የአሜሪካ ግዛት ለማድረግ እንደሚሹ ለመጀመሪያ ጊዜ የተናገሩት በአውሮፓውያኑ 2019 ነበር። ፕሬዝደንቱ አሜሪካ ግሪንላንድን መግዛቷ ለዓለም አቀፍ ደኅንነት "እጅግ አስፈላጊ ነው" ይላሉ።
ትራምፕ የአሜሪካ ፕሬዝደንቶች ከሚጠቀሙበት አውሮፕላን ውስጥ ሆነው በሰጡት አስተያየት "እኔ እንደማምነው ሕዝቡ ከኛ ጋር መሆን ይፈልጋል" ብለዋል።
"ዴንማርክ ምን ዓይነት ምክንያት እንዳላት አላውቅም። ነገር ግን ለዓለም ጥበቃ ሲሉ ይህን የማያደርጉ ከሆነ ድርጊቱን እንደ ወዳጅ ሀገር ተግባር አናየውም" ሲሉ አክለዋል።
"ግሪንላንድ እንደምንቆጣጠር አምናለሁ። ምክንያቱም ጉዳይ የዓለም ነፃነት ጉዳይ ነው" ያሉት ትራምፕ አሜሪካ ለግሪላንድ "ነፃነት ለማጎናፀፍ" ቆርጣ እንደተነሳች ተናግረዋል።
ዶናልድ ትራምፕ በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት በተደጋጋሚ በአርክቲክ ውቅያኖስ የሚገኘውን እና በዓለማችን ትልቁን የግሪንላንድ ደሴት 'ለመጠቅለል' ፍላጎት እንዳላቸው ሲያንፀባርቁ ቆይተዋል።
የዴንማርክ እና የአውሮፓ ባለሥልጣናት በበኩላቸው ግሪንላንድ ለሽያጭ አትቀርብም፤ የግዛት አንድነቷም መጠበቅ አለበት ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
ዶናልድ ትራምፕ የዴንማርክን የራስ ገዝ ግዛት ለመጠቅለል ወታደራዊ ሃይል ጭምር ሊጠቀሙ እንደሚችሉ መግለጻቸውን ተከትሎ ግሪንላንድን ማስፈራራታቸውን እንዲያቆሙ ጀርመን እና ፈረንሳይ ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል።
የግሪንላንድ ጠቅላይ ሚንስትር ሙቴ ኤጌዴ ከዴንማርክ ነፃ ለመሆን እየሠሩ ቢሆንም ግዛቷ እንደማትሸጥ በግልጽ ተናግረዋል።
ራስ ገዟ ግሪንላንድ የሕዝብ ቁጥሯ 57 ሺህ ገደማ ነው። ኢኮኖሚዋ በአብዛኛው ከኮፐንሃገን በሚደረግ ድጎማ ላይ የተመሰረተ ሲሆን የዴንማርክ ግዛት አካል ናት።
ባትሪዎችን እና ከፍተኛ የቴክኖሎጂ መሳሪያዎችን ለማምረት አስፈላጊ የሆኑ ማዕድናት ክምችት አሏት።
ወርቅ እና ፕላቲኒየም፤ ሊቲየም፣ ቲታኒየም እና ሌሎች ተፈላጊ ማዕድናትን ጨምሮ እንደ ድንጋይ ከሰል እና ዩራኒየም ያሉ የኃይል ማዕድናት እንዲሁም አልማዝ እና ሩቢን የመሳሰሉ የከበሩ ድንጋዮችም በደሴቲቱ ይገኛሉ።
ትራምፕ ከግሪንላንድ በተጨማሪ የፓናማ 'ካናል' እና ካናዳን በቁጥጥራቸው ሥር ለማድረግ እንደሚሹ ተናግረዋል።












