ዴንማርክ የትራምፕን ግሪላንድን "እቆጣጠራለሁ" ንግግር ተከትሎ የግዛቲቷን መከላከያ በጀት አሳደገች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ትራምፕ የዴንማርክ ራስገዟን ግሪላንድ ለመቆጣጠር ያላቸውን ፍላጎት በተደጋጋሚ መናገራቸውን ተከትሎ መንግሥት የግዛቲቷን የመከላከያ በጀት በከፍተኛ ሁኔታ ማሳደጉን አስታወቀ።
ዶናልድ ትራምፕ የአርክቲኳን ግዛት ለመቆጣጠር እፈልጋለሁ ባሉ በሰዓታት ውስጥ ነው የዴንማርክ መንግሥት የበጀት ጭማሬ አደርጋለሁ ያለው።
የዴንማርክ መከላከያ ሚኒስትር ትሮልስ ሉንድ ፖልሰን የታቀደው የመከላከያ በጀት ጭማሬ "ባለሁለት አሃዝ ቢሊዮን" ክሮን [በአገሪቱ መገበያያ ገንዘብ] ወይም 1.5 ቢሊዮን ዶላር መሆኑን ገልጸዋል።
ተመራጩ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ግዙፏን ግሪንላንድ ደሴት ባለቤት መሆን እና መቆጣጠር ለአሜሪካ "ፍጹም አስፈላጊ ነው" ብለዋል።
ግሪላንድ ራስ ገዝ የዴንማርክ ግዛት ስትሆን ትልቅ የአሜሪካ ጠፈር ተቋም ይገኝባታል። ለአሜሪካ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ከመሆኗም በተጨማሪ ከፍተኛ የማዕድን ክምችት አላት።
የመከላከያ ሚኒስትሩ እንደተናገሩት የታቀደው የበጀት ፓኬጅ አዳዲስ ሁለት የፍተሻ መርከቦችን፣ ሁለት የረጅም ርቀት ድሮኖችን እና ሌሎች መሳሪያዎችን ለመግዛት ያስችላል ብለዋል።
በተጨማሪም በዋና ከተማዋ ኑኡክ የሚገኘውን የአርክቲክ እዝ ላይ የሰው ኃይል መጨመር እንዲሁም ከግሪንላንድ ሶስት ዋና ዋና የሲቪል አውሮፕላን ማረፊያዎች ለአንዱ ኤፍሱፐርሶኒክ ተዋጊ አውሮፕላኖችን እንዲያስተናግድ የሚያደርግ የማጠናከሪያ ድጋፍን ይጨምራል።
"ለበርካታ ዓመታት በአርክቲክ ውስጥ በበቂ ኢንቨስት አላደረግንም። አሁን በበበለጠ ይዞታችንን እናጠናክራለን" ብለዋል። የመከላከያ ሚኒስትሩ የበጀቱን ፓኬጅ ትክክለኛ አኃዝ ባይጠቅሱም የዴንማርክ መገናኛ ብዙኃን ከ12-15 ቢሊዮን ክሮን አካባቢ እንደሚሆን ገምተዋል።
ትራምፕ ትሩዝ ሶሻል በተሰኘው የማህበራዊ ሚዲያቸው ላይ "ለብሄራዊ ደህንነት እና በአለም ዙሪያ ነጻነት እንዲሰፍን አሜሪካ ግሪንላንድን በባለቤትነት መያዝ እና መቆጣጠር ፍጹም አስፈላጊ እርምጃ እንደሆነ ይሰማናል" ብለው ነበር።
የግሪላንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሙቴ ኤጌዴ ለትራምፕ አስተያየት በሰጡት ምላሽ "ለሽያጭ አልቀረብንም" ብለዋል።
ነገር ግን ግሪላንድስ በተለይም ከጎረቤቶቿ ጋር ለትብብር እና ለንግድ ክፍት መሆኗን መቀጠል አለበት ብለዋል።
ግሪንላንድሰ ያቀደችው በጀት ለረጅም ጊዜ ውይይት ላይ የነበረ መሆኑን የሚጠቅሱት ተንታኞች በበኩላቸው ለትራምፕ አስተያየት ቀጥተኛ ምላሽ ተደርጎ ሊወሰድ አይገባም ይላሉ።
እስካሁን ድረስ ዴንማርክ በግሪላንድ ወታደራዊ አቅሟን ለማስፋፋት የዘገየ አካሄድ እንደነበር ይገልጻሉ። አገሪቱ በግዛቲቱ ዙሪያ ያለውን ውሃ ከቻይና እና ሩሲያ ወረራ መከላከል ካልቻለች የአሜሪካ ልቆጣጠር የሚለው ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ አይቀርም ተብሏል።
ሆኖም ትራምፕ ዴንማርክ ወደዚህ አይነት እርምጃ እንድትገባ ግፊት ለማድረግ አስበውበት ሊሆን እንደሚችል የዴንማርክ መከላከያ አካዳሚ ባልደረባ የሆኑት ሜጀር ስቲን ክጃርጋርድ ይናገራሉ።












