በአሜሪካ ማዕቀብ ተጥሎባት የነበረች የሩስያ መርከብ ሞተሯ ላይ ካጋጠመ ፍንዳታ በኋላ ሰጠመች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የሩስያ ዕቃ ጫኝ መርከብ ሆነችው ኡርሳ ሜጀር በሞተር ክፍል ውስጥ በደረሰ ፍንዳታ ምክንያት በስፔን እና በአልጄሪያ መካከል በሚገኘው የሜዲትራኒያን ባህር ውስጥ መስጠሟን የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የመርከቧን 14 አባላት በመታደግ ወደ ስፔን ካርቴጋና ወደብ መውሰድ ቢቻልም ግን ሁለቱ ጠፍተዋል ብሏል።
የሩስያ የዜና ወኪል ኢንተርፋክስ እንደዘገበው ከሆነ ኡርሳ ሜጀር ከ12 ቀናት በፊት ነበር ከሴንት ፒተርስበርግ ወደብ ጉዞ የጀመረችው።
የመርከቧ ባለቤት በሩቅ ምሥራቅ ሩሲያ ወደምትገኘው ቭላዲቮስቶክ በመጓዝ ላይ እንደነበረች እና እያንዳንዳቸው 380 ቶን የሚመዝኑ ሁለት ክሬኖችን (የእቃ ማንሻ መሳሪያ) ጭና እንደነበር የመርከቧ ባለቤት ገልጿል። የመርከቧን መዳረሻ በገለልተኛ ወገን ማረጋገጥ አልተቻለም።
ኡርሳ ሜጀር ከመስጠሟ በፊት ሳልቫሜንቶ ማሪቲሞ የተባለው የስፔን የባህር ላይ የአደጋ ጊዜ ኤጀንሲ እንዳስታወቀው 14 ሰዎች በአደጋ ጊዜ ጀልባ ላይ ተገኝተው በሰላም ወደ ስፔን የተጓጓዙ ሲሆን በኋላ ላይ የደረሰው የሩሲያ የጦር መርከብ የነፍስ አድን ሥራውን መረከቡን አክለዋል።
ኡርሳ ማጀር በሜድ አካባቢ ሌላኛዋ ማዕቀብ ከተጣለበት ስፓርታ ከምትባል ከሩሲያ መርከብ ጋር በነበረችበት ወቅት ችግር ውስጥ ገብታ ሁለቱ መርከቦችም በእንግሊዝ ቻናል በኩል ታጅበው ሲያመሩ ታይተዋል።
የዩክሬን ወታደራዊ መረጃ (ኤችዩአር) በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ እንደዘገበው ስፓርታ ከበሻር አል አሳድ ውድቀት በኋላ ወታደራዊ መሳሪያዎችን ከሶሪያ ለማውጣት መቀመጫውን ታርቱስ ወዳደረገው እና በሶሪያ የባህር ጠረፍ ወደሚገኘው የሩስያ የባህር ሃይል ጣቢያ እያመራች ነበር።
የክሬምሊን ባለስልጣን ሰኞ ዕለት እንደተናገሩት ከሆነ ሩስያ በዲፕሎማሲያዊ እና በወታደራዊ ደረጃ ስለ ሁለቱ ወታደራዊ ተቋማት የወደፊት ዕጣ ፈንታ ከአዲሶቹ የሶሪያ አስተዳዳሪዎች ጋር እየተጋገረች ነው።
የኡርሳ ሜጀር ባለቤት የሆነው ኦቦሮንሎጂስቲካ ጭነቶችን ወደ ታርቱስ በማጓጓዝ ከፍተኛ ተሳትፎ አድርጓል። የስፓርታ መድረሻ ደግሞ የግብጿ ፖርት ሰዒድ ነበር ተብሏል።
የባህር ላይ ትራንስፖርት መከታተያ ድረ-ገጹ ኤልኤስኢጂ ለቢቢሲ እንደገለጸው ከሆነ የኡርሳ ሜጀር አውቶማቲክ መከታተያ ስርዓት (ኤአይኤስ) ከታህሳስ 2 ጀምሮ መድረሻው ቭላዲቮስቶክ እንደነበረ እና በታርቱስ ወደብ የመጨረሻ ጥሪ የተደረገው በሰኔ ወር ነው ብሏል።

የፎቶው ባለመብት, Rosmorport
ኤችዩአር ሰኞ ዕለት እንደገለጸው ከሆነ ስፓርታ ፖርቹጋልን ካለፈች በኋላ ችግሩ ገጥሟት ተስተካክሏል። ኡርሳ ሜጀር መጀመሪያ ላይ ስፓርታ 3 ትባል ስለነበር ዩክሬናውያን ስለየትኛውን መርከብ መግለጽ እንደፈለጉ ግልጽ አልነበረም።
ስፓርታ ከሳምንት በፊትም ሰሜናዊ ፈረንሳይ ችግር ገጥሟት ነበር። ራዲዮ ፍራንስ ኢንተር እንደዘገበው ከሆነ የሩስያዋ ጭነት መርከብ ከሳምንት በፊት ለፈረንሳይ የግንኙነት ጥያቄዎች ምላሽ አልሰጠችም ነበር። በኋላ ላይ ይህ የተከሰተው በችግር ምክንያት መሆኑን አሳውቃለች።
"ችግር ውስጥ ነን። ሞተሮቼ ሥራ አቁመዋል። በሚቀጥሉት ደቂቃዎች ውስጥ ለመጠገን እንሞክራለን" ሲል የመርከቧ ሬዲዮ መልዕክት ማስተላለፉን አርኤፍአይ ዘግቧል።
ለ 61 ደቂቃዎች ከተንሸራተቱ በኋላ ስፓርታ ወደ ጉዞ መስመር መመለሳቸውንም አስታውቀዋል።
ሰኞ ከሰዓት በኋላ ኡርሳ ሜጀር በአልጄሪያ ኦራን እና በስፔን አጊላስ ከተማ መካከል ስታልፍ የተፈጠረው ፍንዳታው በምን ምክንያት እንደሆነ እስካሁን አልታወቀም።
ነገር ግን በታህሳስ 14 ከቀኑ 6፡00 እስከ 7፡00 የግሪኒዊች ሚን ታይም ሰዓት አቆጣጠር መካከል የተቀረጸው እና በቢቢሲ የተረጋገጠው ቪዲዮ መርከቧ መጥፎ ሁኔታ ውስጥ እንደነበረች ያሳያል።
በመጨረሻ 7፡20 ሰዓት ገደማ ሰመጠች።
ኡርሳ ሜጀር እአአ በ2009 የተገነባች ሲሆን በ2022 ሩስያ ዩክሬን ላይ ወረራ መፈጸሟን ተከትሎ የመርከቧ ባለቤት ጭነቶችን ለሩስያ ጦር ለማድረስ በተጫወተው ሚና ምክንያት ማዕቀብ ተጥሎባታል።
ኦቦሮንሎጂስቲካ እንደገለፀው ከሆነ የዕቃ መጫኛ መርከቧ 45 ቶን የሚመዝን የበረዶ መሸፈኛ እና ለቭላዲቮስቶክ ወደብ የሚያገለግሉ ትላልቅ ክሬኖች ጭና ነበር።












