በጦርነት እየታመሰች ያለችው ሱዳን ወደ ከፋ ረሃብ እየገባች መሆኑ ተገለጸ

የሱዳን ታዳጊ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በጦርነት እየታመሰች ያለችው ሱዳን ወደ ከፋ የረሃብ ቀውስ እየገባች መሆኑን የምግብ ዋስትና ባለሙያዎች ቡድን ገለጸ።

ረሃብ ወደ አምስት አካባቢዎች የተዛመተ ሲሆን 24.6 ሚሊዮን ወይም ግማሽ ያህሉ ህዝብ አስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልገው ቡድኑ ገልጿል።

አገሪቷን ለረሃብ እና ለውድመት የዳረጋት የእርስ በርስ ጦርነት ለሁለት ዓመት ያህል ዘልቋል።

በጦሩ እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መካከል እየተደረገ ያለውን ጦርነት ለማስቆም የተደረጉ የሽምግልና ጥረቶች ፍሬ ሳያፈሩ ቀርተዋል።

ጦሩ እና ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ከሶስት ዓመታት በፊት በጋራ መፈንቅለ መንግሥት ቢያደርጉም ነገር ግን በመሪዎቹ መካከል በተፈጠረ የስልጣን ሽኩቻ አገሪቱ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ገብታለች።

ይህ ደም አፋሳሽ ጦርነት በዓለማችን ላይ ካሉት አስከፊ ሰብዓዊ ቀውሶችን አንዱን አስከትሏል። በተባበሩት መንግሥታት የሚደገፈው የረሃብ ገምጋሚ ኮሚቴ (ኤፍአርሲ) ጦርነቱ ካልተገታ "የከፋ ጥፋት" ሊፈጠር እንደሚችል አስጠንቅቋል።

ኮሚቴው የተባበሩት መንግሥታት ኤጀንሲዎች፣ የእርዳታ ቡድኖች እና መንግሥታት የረሃብ ሁኔታዎችን ለመለየት ያዋቀሩት ዓለም አቀፍ ተነሳሽነት የሆነው አይፒሲ የተሰኘው ተቋም ጋር ግንኙነት አለው።

የኮሚቴውን ሪፖርት ተከትሎ "የሱዳን ሉዓላዊነት እና ክብር የሚጎዱ አሳማኝ ያልሆኑ ዘገባዎችን አውጥቷል" ሲል በሱዳን ጦር የሚደገፈው መንግሥት ከኮሚቴው ጋር ያለውን ትብብር ማቋረጡን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

አይፒሲ ለመጀመሪያ ጊዜ በነሐሴ ወር ላይ በሱዳን ዳርፉር ግዛት ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ባስጠለለው ዛምዛም ካምፕ ውስጥ ረሃብ እንዳለ አስታውቆ ነበር።

ኮሚቴው በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት ደግሞ በከበባ ውስጥ ባለችው የዳርፉሯ ኤል ፋሸር ከተማ በሚገኙት አቤ ሹክ እና አል ሳላም ካምፖች እንዲሁም በደቡብ ኮርዶፋን ግዛት ውስጥ በሚገኙ ሁለት አካባቢዎች ረሃብ ተከስቷል ብሏል።

"ረሃብ ለህልውና አስፈላጊ የሆኑ ስርዓቶች እና ሃብቶችን አስከፊ ውድቀትን የሚወክል እጅግ የከፋ የሰው ልጅ ስቃይ መገለጫ ነው" ሲል ኮሚቴው አስታውቋል።

"የምግብ እጦት ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ የጤና፣ ኑሮ እና ማህበራዊ መዋቅሮች መፈራረስ በመሆኑ መላውን ማህበረሰብ የተስፋ መቁረጥ ስሜት ውስጥ ጥሎታል" ሲል አክሏል።

ኮሚቴው በዳርፉር አምስት ተጨማሪ አካካቢዎች በግንቦት ወር ለረሃብ እንደሚጋለጡ እና ወደ ሌሎች 17 አካባቢዎች የመዛመት ስጋት እንዳለ ተንብዮ ነበር።

"ግጭት በተፋፋመባቸው አካባቢዎች ጦርነቱ የግብርና ስራውን በእጅጉ በማስተጓጎል አርሶ አደሮች እርሻቸውን ትተዋል። በተጨማሪም ዘረፋዎች እና ውድመቶች ተከስተዋል" ብሏል።

የዳርፉር እና የደቡብ ኮርዶፋን ግዛቶች እጅግ አስከፊ የሆነ ጦርነት እየተካሄደባቸው ሲሆን በዚህም በርካታ ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል፣ ተደፍረዋል እንዲሁም በታጣቂዎች ታፍነው ተወስደዋል።

በሱዳን የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ቶም ፔሪየሎ በጦርነቱ እስከ 150 ሺህ ሰዎች ሳይገደሉ እንዳልቀሩ በግንቦት ወር ተናግረው ነበር።