በአቶ ክርስቲያን ላይ ከመጋረጃ ጀርባ ሊሰማ የነበረው የዐቃቤ ህግ ምስክር በጠቅላይ ፍርድ ቤት ታገደ

አቶ ክርስቲያን ታደለ

የፎቶው ባለመብት, HOPR/FB

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በአቶ ክርስቲያን ታደለ ላይ ከመጋረጃ ጀርባ ሊደረግ የነበረው የምስክር አሰማም ሂደት እንዲታገድ ትዕዛዝ አስተላለፈ።

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሁለተኛ ወንጀል ይግባኝ ሰሚ ችሎት የዕግድ ትዕዛዙን ያስተላለፈው አቶ ክርስቲያን በጠበቆቻቸው በኩል የይግባኝ አቤቱታ ከቀረበለት በኋላ ነው።

ጠበቆች የስር ፍርድ ቤት በሰጠው ብይን ቅር በመሰኘት የይግባኝ አቤቱታውን ያቀረቡት ከአንድ ሳምንት በፊት ሐምሌ 8/ 2017 ዓ.ም ነው።

ቢቢሲ የተመለከተው አራት ገጽ የይግባኝ አቤቱታ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ የጸረ ሽብር እና ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ችሎት ከዐቃቤ ህግ ምስክር ጋር በተያያዘ በሰጠው ብይን ቅር መሰኘታቸውን ያትታል።

ይግባኝ የተባለባቸው ሁለት ብይኖች ሰኔ 18 እና ሐምሌ 1/ 2017 በስር ፍርድ ቤት የተላለፉ ናቸው።

ይግባኝ የተባለበት ምስክር በአማራ ክልል ምክር ቤት አባሉ አቶ ዮሐንስ ቧያለው መዝገብ በተከፈተው የክስ መዝገብ ሁለተኛ ተከሳሽ አቶ ክርስቲያን ላይ የሚመሰክር ነበር።

ዐቃቤ ህግ አቶ ዮሐንስን እና የፓርላማ አባሉን አቶ ክርስቲያንን ጨምሮ በሌሎች ፖለቲከኞች ላይ ክስ የመሰረተው ከአንድ ዓመት ከአራት ወር በፊት መጋቢት 2016 ዓ.ም. ነበር።

በ68 ገጾች ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቀረበው የዐቃቤ ህግ የክስ ሰነድ በተከሳሾች ላይ አራት ክሶችን አቅርቧል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የወንጀል ሕጉን እና የሽብር ወንጀልን ለመቆጣጣር እና ለመከላከል የወጣውን አዋጅ በመተላለፍ የተፈጸመ "ወንጀልን" የሚመለከተው የመጀመሪያ ክስ የቀረበው በሁሉም ተከሳሾች ላይ ነው።

አቶ ክርስቲያን ከመጀመሪያው ክስ በተጨማሪ የጦር መሳሪያ አስተዳደር እና ቁጥጥር አዋጅን በመተላለፍ ሁለተኛ ክስ ተመስርቶባቸዋል።

አቶ ክርስቲያን የጦር መሳሪያን ለመያዝ ፈቃድ ሳይኖራቸው አንድ ታጣፊ ክላሽ ከነ ካርታው እና 30 የክላሽ ጥይት በቤታቸው ይዘው መገኘታቸውን ዐቃቤ ሕግ በክስ ሰነዱ ላይ አስፍሯል።

ዐቃቤ ህግ በክስ ሰነዱ ላይ 21 የሰው ምስክሮች እና 28 የሰነድ ማስረጃዎችን አቅርቧል።ከ21ዱ የዐቃቤ ህግ ምስክሮች ውስጥ 15ቱ ፍርድ ቤት ቀርበው በግልጽ ችሎት ተሰምተዋል።

ሆኖም ግን ዐቃቤ ህግ በክስ መዝገቡ ላይ ተጨማሪ የማስረጃ አቤቱታ ማቅረቡን ተከትሎ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ሰኔ 18 ማስረጃው ቀርቦ እንዲሰማ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር።

ከዚህ ትዕዛዝ አንድ ቀን በኋላ ዐቃቤ ህግ "አንድ ምስክር ከመጋረጃ ጀርባ ለማሰማት" እንዲፈቀድለት ሌላ አቤቱታ አቅርቧል።

ዐቃቤ ህግ ምስክሩ ከመጋረጃ ጀርባ እንዲሰማ የጠየቀው "ምስክሩ የሚያስረዳው ጭብጥ በሌላ ማናቸውም ማስረጃ ሊረጋገጥ የማይችል በመሆኑ እና በምስክሩ ህይወት፣ አካላዊ ደህንነት፣ ነጻነት እና ንብረት ላይ ከባድ አደጋ ሊደርስ እንደሚችል" በመጥቀስ ነው።

ዐቃቤ ህግ አክሎም "በግልጽ ችሎት ቀርቦ የሚያውቀውን ነገር ነጻ ሆኖ ማስረዳት ስለማይችል ከስጋት ነጻ ሆኖ የሚያውቀውን እንዲመሰክር የምስክርነት ቃሉን ከመጋረጃ ጀርባ ሆኖ እንዲሰጥ" ጠይቋል።

ምስክሩ ከመጋረጃ ጀርባ ሆኖ ቃሉን እንዲሰጥ "በቂ እና አሳማኝ በሆነ መልኩ አልቀረበም" ያሉት የተከሳሹ ጠበቃ "ምስክሩ ከመጋረጃ ጀርባ ሆኖ ይመስክር ቢባል ማንነቱን መለየት ስለማንችል መስቀለኛ ጥያቄ የመጠየቅ መብታችንን በፅኑ የሚጎዳ ነው" በሚል የዐቃቤ ህግን አቤቱታ ተቃውመው ነበር።

ከዚህ በተጨማሪም ከዚህ በፊት የተሰሙ የዐቃቤ ህግ ምስክሮች በግልጽ ሲመሰክሩ "አንዳችም ጉዳት ደርሶባቸው እንደነበር የቀረበ ነገር ሳይኖር" ምስክሩ ከመጋረጃ ጀርባ ይሰማ መባሉን ተቃውመው ተከራክረዋል።

ጠበቆች ዐቃቤ ህግ "ከቅን ልቦና ውጪ የመዝገቡን አቅጣጫ በመመልከት ከዚህ ቀደም በማስረጃ ዝርዝር ያልጠቀሰውን ምስክር" ተጨማሪ ምስክር ሆኖ እንዲሰማ አቤቱታ አቅርቧል የሚል መከራከሪያ አሰምተዋል።

ለጠቅላይ ፍርድ ቤት የቀረበው የአቶ ክርስቲያን አቤቱታ በአቶ ክርስቲያን ላይ ከመጋረጃ ጀርባ እንዲመሰክር የቀረበው ምስክር ከዚህ በፊት በተቆጠሩ ምስክር ምትክ ሆነው መቅረባቸውን ጠቁሟል።

ይህን ተከትሎም "በወንጀል ጉዳይ አንድ ምስክር በሌላ ምስክር በምትክነት እንዲመሰክር የሚደረግበት የስነ ስርዓት ህግ በሌለበት የስር ፍርድ ቤት ይህን መቀበሉ ተገቢነት የሌለው ነው" ሲሉ ጠበቆች በአቤቱታቸው ተቃውመውታል።

ሆኖም የስር ፍርድ ቤት የዐቃቤ ህግን አቤቱታ በመቀበል ምስክሩ "ተጨማሪ ማስረጃ ሆኖ የምስክርነት ቃሉን ይስጥ ብሎ ብይን መስጠቱ ተገቢነት የሌለው ነው" ብለዋል።

"ዐቃቤ ህግ ተጨማሪ ማስረጃውን ጉዳዩን ለማጓተት እና ትክክለኛ ፍትህን ለማዛባት አስቦ ያቀረበው መሆኑን መረዳት ይቻላል" ያሉት ጠበቆች፤ "በተጨማሪ ማስረጃነት ቀርቦ የምስክርነት ቃሉን እንዲሰጥ የተፈቀደበት አግባብ ኢ-ስነስርዓታዊና መሰረታዊ የህግ ስህተት በመፈጸም የተፈቀደ በመሆኑ" በይግባኝ ሰሚ ችሎቱ እንዲታረም ጠይቀዋል።

የአቶ ክርስቲያን ታደለ ጠበቆች የዐቃቤ ህግ ምስክር በፍርድ ቤት እንዲመሰክሩ የተሰጠው ብይን እንዲቀለበስ ብቻ ሳይሆን የምስክር አሰማም አካሄዱ ላይም ተቃውሞ አላቸው።

ምስክሩ "ከመጋረጃ ጀርባ ሆኖ የምስክርነት ቃሉን ይስጥ ቢባል የተከሳሾች መብት የሚጎዳ" መሆኑን የጠቆሙት ጠበቆቹ፤ ምስክሩን በአካል የማይመለከቱ ከሆነ ማንነቱን መለየት እንደማይችሉ እንዲሁም "የምስክሩን ማንነት ሳንለይ የምንጠይቀው መስቀለኛ ጥያቄ ዋጋ አልባ ያደርገዋል" ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪም "በመሆኑ ከመጋረጃ ጀርባ መሰማቱ መስቀለኛ ጥያቄ የመጠየቅ መብታችን ላይ ከፍተኛ የሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ አለው" ሲሉ ተቃውሟቸውን በአቤቱታቸው አስፍረዋል።

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሁለተኛ ወንጀል ይግባኝ ሰሚ ችሎትም የስር ፍርድ ቤት የሰጣቸውን ብይኖች እንዲሽር ጠይቀዋል።

ይህን ተከትሎ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት፤ "ጉዳዩ ታይቶ ዕልባት እስኪሰጥ ወይም ተለዋጭ ቀጠሮ እስኪሰጥ ድረስ" የስር ፍርድ ቤት ትዕዛዝ እንዲታገድ ትዐዕዛዝ ሰጥቷል።

የዐቃቤ ህግን ምስክር ከመጋረጃ ጀርባ ለመስማት የስር ፍርድ ቤት ዛሬ ረዑዕ ሐምሌ 16/2017 ዓ.ም ቀጠሮ ቢኖርም የዕግድ ትዕዛዙን ተከትሎ ለሚቀጥለው ዓመት ጥቅምት 10/ 2018 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።