እነ አቶ ዮሐንስ ቧያለው አቤቱታቸው ምላሽ ካላገኘ ጉዳያቸውን ለመከታተል ችሎት እንደማይቀርቡ አስታወቁ

ከግራ ወደ ቀኝ አቶ ዮሐንስ ቧያሌው፣ ዶ/ር ካሳ ተሻገር እና አቶ ክርስቲያን ታደለ
የምስሉ መግለጫ, ከግራ ወደ ቀኝ አቶ ዮሐንስ ቧያሌው፣ ዶ/ር ካሳ ተሻገር እና አቶ ክርስቲያን ታደለ

በእነ አቶ ዮሐንስ ቧያለው መዝገብ ክስ የተመሠረተባቸው ተከሳሾች ለፍርድ ቤት ያቀረቧቸው ቅሬታዎች መፍትሔ ካላገኙ ችሎት እንደማይቀርቡ አስታወቁ።

ተከሳሾቹ ይህን ያስታወቁት በዚህ ሳምንት አጋማሽ ጉዳያቸው ለሚታይበት ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ለሕገ መንግሥት እና ሽብር ወንጀል ጉዳዮች ችሎት በጽሁፍ ባቀረቡት አቤቱታ ነው።

ባለፈው ረቡዕ ሐምሌ 9/ 2017 ዓ.ም. ለችሎት የቀረበውን አቤቱታ የፈረሙት በመዝገቡ የተካተቱ ሁሉም ተከሳሾች ናቸው።

ከአንድ ዓመት ከዘጠኝ ወራት በፊት በዐቃቤ ሕግ በተመሠረተው ክስ ውስጥ 52 ተከሳሾች ያሉ ሲሆን፣ ጉዳያቸውን በማረሚያ ቤት ሆነው እየተከታተሉ የሚገኙት ግን 16ቱ ተከሳሾች ብቻ ናቸው።

ችሎቱ ባለፈው ረቡዕ የተቀጠረው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ክርስቲያን ታደለ የሚገኙበት የክስ መዝገብ ላይ የዐቃቤ ሕግን ምስክር ለመስማት ነበር።

ረፋድ ላይ ከመጋረጃ ጀርባ ሊሰማ የነበረው የዐቃቤ ሕግ የመጨረሻ ምስክር የቀረበው በሁለተኛ ተከሳሹ አቶ ክርስቲያን ታደለ ላይ እንደነበር የተከሳሾቹ ጠበቃ አቶ ሰለሞን ገዛኸኝ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"ከመጋረጃ ጀርባ ያለ የምስክር አሰማም ሂደት ሊጀመር ሲል፤ አቶ ክርስቲያን ታደለ [በችሎት ውስጥ] አልነበረም" የሚሉት ጠበቃው፤ ከአዳራሽ ውጪ የነበሩትን ደንበኛውን ሲያናግሯቸው "አሞኛል ተገድጄ ነው የመጣኹት" ማለታቸውን ገልጸዋል።

ጠበቃ ሰለሞን ከአቶ ክርስቲያን በተጨማሪ ሌሎች ሦስት ተከሳሾችም "ተገድደን ነው የመጣነው ብለው ለችሎት ተናግረዋል" ብለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ጠበቃው የአቶ ክርስቲያንን መታመም ለችሎት ተናግረው ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰጥ የጠየቁ ሲሆን፤ ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ "ተከሳሹ እና ጠበቃቸው እዚሁ ስላሉ ምስክር ይሰማ" የሚል ተቃውሞ አሰምቶ ነበር።

ለዚህ የዐቃቤ ሕግ ተቃውሞ በጠበቃው በኩል "ተከሳሽ አቶ ክርስቲያን ታደለ በአግባቡ የቀረበባቸውን ክስ የመከላከል መብት ስላላቸው ሕመማቸው ደግሞ ይህንን የመከላከል መብት የሚያጣብብ [ነው]" የሚል መከራከሪያ መቅረቡን ጠበቃው ገልጸዋል።

ችሎቱም የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ የመጨረሻውን ምስክር ለመስማት ለሚቀጥለው ሳምንት ረቡዕ ሐምሌ 16/ 2017 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

ተለዋጭ ቀጠሮው ከተሰጠ በኋላ አንደኛ ተከሳሽ የሆኑት አቶ ዮሐንስ ቧያለው "አቤቱታ አለን" ብለው በጽሁፍ የተዘጋጀ አቤቱታቸውን ለፍርድ ቤት ማቅረባቸውን ጠበቃቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ቢቢሲ በተመለከተው አቤቱታ ተከሳሾቹ "ከነገ ዛሬ የፍትሕ ሂደቱ ይሻሻል ይሆናል ብለን ብንጠብቅም . . . በተከሳሾች ላይ ሰፊ የመብት ጥሰት እና በደል እየተፈፀመብን ይገኛል" ብለዋል።

"በችሎቱ ላይ ያለንን ቅሬታ ስለመግለጽ" በሚል ጉዳይ የቀረበው አቤተታ ተከሳሾቹ ከአያያዛቸው ጀምሮ እስከ ምስክር አሰማም ድረስ አሉ ያሏቸውን "ችግሮች" ዘርዝረዋል።

"ችሎቱ ሙሉ በሙሉ ለመንግሥት እና ለገዥው ፓርቲ" ወግኗል የሚል ክስ ያቀረቡት ተከሳሾቹ "በእኛ በተከሳሾች ላይ ያልተቋረጠ ጫና እና ይሉኝታ ቢስ ውሳኔዎችን በተደጋጋሚ ፈጽሞብናል" የሚል ክስ በችሎቱ ላይ አቅርበዋል።

አቤቱታ አቅራቢዎቹ በፍርድ ቤቱ ተፈጸሙ ያሏቸውን አስር "ኢፍትሐዊ ውሳኔዎች" በዝርዝር በአቤቱታቸው ላይ አስፍረዋል።

ክስ ከመመሥረቱ በፊት ለወራት በወታደራዊ ካምፕ መቆየታቸውን ያስታወሱት ተከሳሾቹ ፍርድ ቤት ከቀረቡ በኋላ ፍርድ ቤቱ "አጋቾችን" በሕግ ተጠያቂ እንዲያደረግ እና "እገታን መዳኘት እንዲያቆም" ያቀረቡትን ጥያቄ "ቸል በማለት እገታን ሕጋዊ አድርጓል" ሲሉ ወቅሰዋል።

ከዚህ በተጨማሪም በዋስትና የመከራከር መብታቸውን "ያለ በቂ ምክንያት ሙሉ በሙሉ በመገደብ" ተከሳሾችን "በተራዘመ እገታ በማቆየት የከሳሽን ጥቅም ብቻ አረጋግጧል" የሚል ቅሬታቸውን አቅርበዋል።

ተከሳሾቹ ፍርድ ቤቱ "የደረሰብንን እና በገለልተኛ አካል የተረጋገጠ ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት እንዳላየ አልፎታል" ሲሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰትን የተመለከተ አቤቱታም አቅርበዋል።

በፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ መሠረት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የሰብዓዊ መብት ጥሰትን በተመለከተ ያቀረበውን ሪፖርት ከዘጠኝ ወራት በፊት ለፍርድ ቤቱ ማቅረቡ ይታወሳል።

ኮሚሽኑ በሪፖርቱ ተከሳሾቹ "ለተለያዩ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች መጋለጣቸውን ለማመን በቂ ምክንያታዊ መሠረት መኖሩን" ገልጾ ነበር።

ኢሰመኮ በ21 ገጾች ባዘጋጀው በዚህ ሪፖርት "የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት በፈጸሙ የፀጥታ አካላት ላይ በሙሉ የተሟላ የወንጀል ምርመራ በማድረግ ሕጋዊ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ" ምክረ ሃሳብ አቅርቦ ነበር።

ተከሳሾች ፍርድ ቤቱ ይህን የኮሚሽኑን ሪፖርት "አፍኖ በመያዝ ውሳኔ ሳይሰጥበት ቀርቷል" የሚል ቅሬታቸውን በአቤቱታቸው ላይ አቅርበዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ተከሳሾች በማረሚያ ቤት በፌደራል ፖሊስ እና በደኅንነት አካላት የሚደርሱባቸውን "ተደጋጋሚ ጥቃት እና የሰብዓዊ መብት ጥሰት" ለፍርድ ቤቱ ቢገልጹም ችሎቱ "ምንም ምላሽ ሳይሰጠን አቤቱታውን አዳፍኖታል" ሲሉ ወቅሰዋል።

ተከሳሾቹ "ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዐቃቤ ሕግ ያቀረበው ክስ ትክክል አለመሆኑን አይቶ አሻሽሎ እንዲያቀርብ በይግባኝ የሰጠውን ብያኔ የስር ፍርድ ቤቱ ቀባብቶ አልፎታል" ሲሉ ከቀረበባቸው ክስ ጋር የተያያዘ ቅሬታቸውን ገልጸዋል።

አቤቱታ የቀረበበት ሌላኛው ጉዳይ የዐቃቤ ሕግ ምስክሮችን የተመለከተ ነው።

ፍርድ ቤቱ "የተከሳሾች መብት በመተላለፍ" የክስ መዝገቡ ላይ የቀረቡ የዐቃቤ ሕግ ምስክሮች "ዝርዝር እና ማንነት እንዳይገለጽ ዐቃቤ ሕግ ያቀረበውን ጥያቄ በመቀበል የተከሳሾችን መብት አጣቧል" የሚል ወቀሳ በተከሳሾች በኩል ቀርቦበታል።

በተጨማሪም ምስክሮቹ "ጥበቃ የሚያስፈልጋቸው" መሆናቸው በዐቃቤ ሕግ ቢገለጽም እስካሁን ችሎት ፊት የቀረቡት ምስክሮች "የመከላከያ እና የፌዴራል ፖሊስ አባላት የሆኑ እና ልዩ ጥበቃ የሚያስፈልጋቸው አለመሆናቸውን" እንደታዘቡ ተከሳሾቹ በአቤቱታቸው ጠቁመዋል።

በአቤቱታቸው መደምደሚያ ላይ "ፍርድ ቤቱ ትክክለኛ ፍትሕ ለመስጠት አለመቻሉን እንረዳለን" ያሉት ተከሳሾቹ፤ "በሂደትም የመሻሻል ጭላንጭል ቢኖር ዕድል ለመስጠት" እስከ አሁን የፍርድ ሂደቱን ሲከታተሉ መቆየታቸውን ገልጸዋል።

አክወለውም "የጠቀስናቸው ችግሮች እስካልተቀረፉ ድረስ በዚህ ችሎት ቀርበን ለመዳኘት ዝግጁ አለመሆናችንን እንገልጻለች" ሲሉ አቋማቸውን በአቤቱታቸው አስታውቀዋል።

ጠበቃ ሰለሞን የችሎቱ ዳኞች አቤቱታውን ካነበቡ በኋላ "ይሄ [አቤቱታ] ችሎት አንቀርብም የሚል ነው፤ ስለዚህ ይሄንን አንቀበልም፤ በዳኞች ላይ ተቃውሞ ካላችሁ ዳኞች ይነሱልን ማለት ትችላላችሁ ብለው አቤቱታውን መለሱት" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ይህን ጊዜ አቶ ዮሐንስ ቧያለው "አቤቱታችን ቅሬታችንን አይታችሁ እንድትፈቱልን ነው። ከዚህ በኋላ ችሎት አንቅርብም ያልነው ቅሬታችንን የማይፈታ ከሆነ ነው" ማለታቸውን ጠበቃው ገልጸዋል።

ሦስተኛ ተከሳሽ ሆነው የቀረቡት የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አባሉ ዶ/ር ካሳ ተሻገር በበኩላቸው "ችሎት አንቅርብም የሚለው አቋም የመጨረሻ ድምዳሜ ሳይሆን ቅድመ ሁኔታ ነው። እዚያ ላይ የተቀመጡት ነገሮች መቀረፍ አለባቸው" ማለታቸውን አክለዋል።

የተከሳሾቹ ጠበቃ አቶ ሰለሞን "ከዚህ በኋላ ችሎቱ አቤቱታውን ተቀብሎታል። እንግዲህ በቀረበው ቅሬታ ላይ ብይን ይስጥ አይስጥ የሚቀጥለው ችሎት ላይ ነው የምናየው" ሲሉ ለቢቢሲ ተናገረዋል።

ዐቃቤ ሕግ በእነ አቶ ዮሐንስ ቧያለው ላይ የመሠረተው ክስ የወንጀል ሕጉን እንዲሁም የሽብር ወንጀልን ለመቆጣጣር እና ለመከላከል የወጣውን አዋጅ በመተላለፍ የተፈጸመ "ወንጀልን" የሚመለከት ነው።

የዐቃቤ ሕግ የክስ ሰነድ ተከሳሾቹ "የፖለቲካ ርዕዮተን በኃይል ለማስፈጸም በማሰብ" ተሰብስበው ተደራጅተዋል ሲል ይከስሳል።