የአማራ ክልል ምክር ቤት የአቶ ዮሐንስ ቧያለውን ያለመከሰስ መብት አነሳ

የፎቶው ባለመብት, bd com.
በአማራ ክልል ከተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር በተያያዘ በእስር ላይ የሚገኙትን አባሉን የአቶ ዮሐንስ ቧያለውን ያለመከሰስ መብት የአማራ ክልል ምክር ቤት አነሳ።
በአማራ ክልል እና በገዢው ፓርቲ ውስጥ ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታ ላይ የነበሩት አቶ ዮሐንስ ቧያለው በአማራ ክልል የተከሰተውን አለመረጋጋት ተከትሎ በተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተይዘው ለወራት በእስር ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል።
የአማራ ክልል ምክር ቤት ከትናት ረቡዕ ጀምሮ እያካሄደ ባለው መደበኛ ጉባኤው ላይ የምክር ቤቱ አባል የሆኑትን የአቶ ዮሐንስ ቧያለውን ያለመከሰስ መብት እንዲነሳ መወሰኑን የክልሉ መገናኛ ብዙኃን አስታውቋል።
አቶ ዮሐንስ ከምክር ቤት አባልነታቸው በተጨማሪ በክልሉ ገዢ ፓርቲ ውስጥ ከምክትል ሊቀመንበር አንስቶ በከፍተኛ ኃላፊነት ላይ ነበሩ።
በተጨማሪም በፌደራል መንግሥቱ ውስጥ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የመለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ ፕሬዝዳንትነት ተሹመው የነበረ ቢሆንም ሹመቱን እንደማይቀበሉት በይፋ ማሳወቃቸው ይታወቃል። ከዚያ በኋላም የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ስትራቴጂክ ጥናት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ነበሩ።
አቶ ዮሐንስ በአማራ ክልል ውስጥ ግጭት ተፈጥሮ የአስቸኳይ ጊዜ ከመታወጁ በፊት በምክር ቤቱ ውስጥ በተደረገ ስብሰባ ላይ የክልሉን መስተዳደር አጥብቀው የተቹ ሲሆን፣ ጠንከር ባለ ንግግራቸውም ይታወቃሉ።
የክልሎችን ልዩ ኃይሎች በማፍረስ ከሌሎች የፀጥታ ክፍሎች ጋር መልሶ ለማወቀር የወጣውን የመንግሥት ዕቅድ እና ታጣቂዎችን ትጥቅ ለማስፈታት የተጀመረውን እንቅስቃሴ ተከትሎ ካለፈው ዓመት አጋማሽ ጀምሮ የአማራ ክልል ውስጥ የተቀሰቀሰው አለመረጋጋት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲደነገግ ምክንያት መሆኗል።
በዚህም ሳቢያ የፌደራል እና የክልል ምክር ቤት እንደራሴዎችን ጨምሮ በርካታ ሰዎች በእስር ላይ እንደሚገኙ የመብት ተቋማት ያወጧቸው ሪፖርቶች ያመለክታሉ።
ከእነዚህም መካከል ዛሬ የካቲት 14/2016 ዓ.ም. ያለመከሰስ መብታቸው የተነሳው የአማራ ምክር ቤት አባሉ አቶ ዮሐንስ ቧ ያለው አንዱ ናቸው። ከእሳቸው በተጨማሪም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላቱ አቶ ክርስቲያን ታደለ እና ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) እንዲሁም የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባሉ ካሳ ተሻገር (ዶ/ር) በእስር ላይ ይገኛሉ።
እነዚህ በተለያዩ ደረጃዎች ባሉ ምክር ቤቶች ውስጥ አባል የሆኑት ግለሰቦች ያለመከሰስ መብታቸው ሳይነሳ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ስር ተይዘው ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ለወራት በእስር ላይ ቆይተዋል።
ምንም እንኳን በተለየ ሁኔታ ቢሆንም የኦሮሚያ ምክር ቤት አባል እና የሰላም ሚኒስትር ዲኤታው አቶ ታዬ ደንደአም ከሁለት ወራት በፊት በቁጥጥር ስር ውለው በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ያለመከስ መብታቸው መነሳቱ ይታወሳል።












