አቶ ክርስቲያን ታደለ በፀጥታ ኃይሎች መታሰራቸውን ቤተሰቦቻቸው ተናገሩ

አቶ ክርስቲያን ታደለ

የፎቶው ባለመብት, hopr/fb

የምስሉ መግለጫ, አቶ ክርስቲያን ታደለ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል እና በምክር ቤቱ የመንግሥት ወጪ፣ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ክርስቲያን ታደለ አርብ ምሽት፣ ሐምሌ 28/2015 ዓ.ም. በፀጥታ ኃይሎች ከቤታቸው ተይዘው መወሰዳቸውን ቤተሰቦቻቸው ለቢቢሲ አረጋገጡ።

አርብ ምሽት 3፡30 አካባቢ የፌደራል ፖሊስ ልብስ የለበሱ በርካታ ፖሊሶች የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ተወካይ የሆኑት አቶ ክርስቲያንን አዲስ አበባ ከሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው “በኃይል አፍነው” መውሰዳቸውን ቤተሰቦቻቸው ገልጸዋል።

በርካታ የፌደራል ፖሊስ አባላት “በአጥር ዘለው በመግባት” ወደ ቤታቸው መግባታቸውን እና አቶ ክርስቲያንን እና አንዳንድ ነገሮችን ይዘው መውሰዳቸውን የአቶ ክርስቲያን ባለቤት እናት ወ/ሮ ዛብሽወርቅ ካሳ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በወቅቱ አቶ ክርስቲያንም “እኔ ሕጋዊ ሰው ነኝ፣ ለምንድን ነው የምትፈልጉኝ? ብሎ ሲያናግራቸው ከፖሊሶቹ መካከል አንደኛው በቦክስ ደበደበው” በማለት በቦታው የነበሩት እኚሁ የቅርብ ቤተሰብ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ሌላኛዋ የፖሊስ ባልደረባ ደግሞ ወደ ቤት ውስጥ ዘልቃ በመግባት “የቤተሰቡን ፓስፖርት አንድ ላይ ሰብስባ ወስዳለች” ብለዋል።

የፖሊስ አባላቱ ከሁለቱ በስተቀር ሌሎቹ የፌደራል ፖሊስ ልብስ የለበሱ መሆናቸውን የተናገሩት የአቶ ክርስቲያን ቤተሰቦች፣ “ሁኔታውን ለማስረዳት ብንሞክርም መሣሪያ ደቅነው አስጠነቀቁን” ብለዋል።

ዛሬ [ቅዳሜ] ጠዋት 2፡30 አካባቢ ደግሞ ሌሎች ፖሊሶች አቶ ክርስቲያንን ይዘው ወደ ቤት በመመለስ ፍተሻ ማድረጋቸውንም ቤተሰቦቹ ገልጸዋል።

“የዛሬዎቹ ፖሊሶች ሥነ ሥርዓት አላቸው” ያሉት ቤተሰቦቹ፣ ጎረቤት እና የአቶ ክርስቲያን ቤተሰቦች በተገኙበት ፍተሻ አካሂደው እና አስፈርመው ከአቶ ክርስቲያን ጋር ተመልሰው መሄዳቸውን ተናግረዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

አቶ ክርስቲያ ታደለ በተመረጡበት የአማራ ክልል ውስጥ ባለፉት ቀናት በተባባሰው የፀጥታ ችግር ምክንያት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የተደነገገበት ሲሆን፣ የክልሉን ፀጥታ ለማስከበር እና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለመጠበቅ የፌደራል መንግሥቱ አስፈላጊውን እርምጃ እንደሚወስድ አስታውቋል።

አቶ ክርስቲያን በፀጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ስር ሲውሉ በምክር ቤት አባልነታቸው ያለመከሰስ መብታቸው ስለመነሳቱ እና ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር ስለመያያዙ የታወቀ ነገር የለም።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር ዶ/ር ለገሰ ቱሉ ዛሬ ቅዳሜ ሐምሌ 29/2015 ዓ.ም. ረፋድ ላይ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተያያዘ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ገልጸዋል።

ሚኒስትሩ እንዳሉት ከትናንት አርብ ጀምሮ “ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት ያላቸው፣ ስምሪት የሚሰጡ፣ በተለያየ መንገድ ችግሩን የሚያባብሱ ኃይሎችን በቁጥጥር ስር ማድረግ ተጀምሯል” ያሉ ሲሆን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አስፈጻሚ አካል የሚወሰዱ እርምጃዎችን በቀጣይ ቀናት እንደሚያሳውቅም ገልጸዋል።

አቶ ክርስቲያን በአማራ ክልል ያለው ቀውስ በተባባሰበት ጊዜ ከሁለት ቀናት በፊት “የዐቢይ አሕመድ አስተዳደር በአማራ ሕዝብ ላይ እየፈፀመ ያለውን ወረራ እና የንፁሃን ግድያ በአስቸኳይ እንዲያቆም አሳስባለሁ” በማለት ሌሎች አካላትም ድርጊቱን እንዲያወግዙ ጠይቀው ነበር።

በቅርቡ በተደረጉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጉባዔዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩን “ከሥልጣን ይልቀቁ” በሚል በመሞገት እና ገዢውን ፓርቲ የብልጽግና አስተዳደርንም ሲተቹ ይደመጣሉ። በማኅበራዊ ሚዲያም ላይ እንዲሁም መንግሥትን የሚተቹ ጽሁፎች ይጽፋሉ።

በሌላ በኩል የአዲስ አበባ ከተማ የምክር ቤት አባል የሆኑት ዶክትር ካሳ ተሻገር እኩለ ሌሊት ላይ በፌስቡክ ገፃቸው ላይ “ፓሊሶች ነን የሚሉ በሌሊት መጥተው ክፈት እየተባልኩ ነው!!” የሚል መልዕክት አስፍረው ነበር።

ቀጥሎ ስለተፈጠረው ነገር ለማወቅ ቢቢሲ ያደረገው ጥረት አልተሳካም። የዶክተር ካሳን ባለቤት ለማናገር በተደጋጋሚ ስልክ ብንደውልም ምላሽ ማግኘት አልቻልንም። ለግለሰቡ ቅርበት ያላቸው ምንጮች እሳቸውም መታሰራቸውን ቢገልጹም ቢቢሲ ማረጋገጥ አልቻለም።