አንቶኒ ብሊንከን በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች ያለው ሁኔታ እንዳሳሰባቸው ገለጹ

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ

የፎቶው ባለመብት, Ethiopian Embassy

የምስሉ መግለጫ, የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን እና ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች ያለው ሁኔታ እንዳሳሰባቸው ገለጹ።

ብሊንከን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር አርብ፣ ሐምሌ 28/2015 ዓ.ም. በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የስልክ ውይይት ማድረጋቸውን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት አስታውቋል።

አንቶኒ ብሊንከን እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በኢትዮጵያ ስላለው ሰላም፣ መረጋጋት እና ብልጽግናን አንስተው መወያየታቸውም ተገልጿል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የተወያዩት በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች በመከላከያ ሠራዊት፣ በታጣቂ ሚሊሻዎች እና በፋኖ መካከል ሲካሄዱ የነበሩ ግጭቶች ተባብሰው መቀጠላቸውን ተከትሎ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በተደነገገበት ዕለት ነው።

“የሕዝብን ሰላም እና ደኅንነት ለማስጠበቅ የወጣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ” የሕዝብን ሰላም እና ደኅንነት ለማስጠበቅ እንዲሁም ሕግ እና ሥርዓት ለማስከበር ያለመ መሆኑ በመንግሥት ተገልጿል።

ይህንንም ተከትሎ እስራኤል ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለችው እንደሆነ የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለመደንገግ መወሰኑ በአማራ ክልል ያለው ሁኔታ አሳሳቢነትን የሚያሳይ መሆኑን እና እየተከሰቱ ያሉ ጉዳዮችን በቅርበት እየተከታተሉ መሆናቸውን የእስራኤል ሚኒስትር ተናግረዋል።

“የሁሉም ሕዝብ ደኅንንት እና ሁኔታ የሚያሳስበን ሲሆን፣ በተለይም በክልሉ ያሉ ዜጎቻችን ጉዳይ በጥብቅ የምንከታተለው ነው” ሲሉ የስደተኞችን ጉዳይ የሚከታተለው የአገሪቱ አሊያህ እና ኢንተግሬሽን ሚኒስትር ኦፊር ሱፈር መናገራቸውንም ጀሩሳሌም ፖስት ዘግቧል።

በክልሉ ያለው የፀጥታ ሁኔታ ያሳሰባቸው አሜሪካ፣ ካናዳ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና አውስትራሊያ ዜጎቻቸው ወደ አማራ ክልል እንዳይሄዱ፣ እዚያም ያሉ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ፣ ለመሄድ የሚፈልጉም ምክር እንዲጠይቁ አሳስበዋል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ ብሊንከን በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች ካለው ስጋት በተጨማሪ የፕሪቶሪያው ግጭትን በዘላቂነት የማቆም ስምምነት አፈጻጸምን በተመለከተ የታየውን መሻሻል ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ተወያይተዋል።

እንዲሁም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ እና ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ ዕርዳታ አላግባብ ከመጠቀም እና ከስርቆት ጋር ተያይዞ የቆመው የዕርዳታ አቅርቦትን በፍጥነት ለመጀመር ሥርዓት የመዘርጋቱን ሁኔታ አንስተው ተወያይተዋል።

የአፍሪካ ቀንድን በተመለከተ ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግብብ ጋር በተያያዘም በአገራቱ መካከል ላለው ውዝግብ ዲፕሎማሲያዊ እልባት ለመስጠት አሜሪካ ድጋፍ እንደምታደርግም አንቶኒ ብሊንከን መናገራቸን የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ገልጿል።

በተጨማሪም ሱዳን በጦርነት ከገባችበት ቀውስ ለመፍታት በሚደረገው ቀጣናዊ ጥረት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እያደረጉት ስላለው አስተዋጽኦም አድናቆታቸውን መቸራቸው ሰፍሯል።