በአማራ ክልል የተፈጠረው የፀጥታ ችግር በንግግር እንዲፈታ ጥሪ ቀረበ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአማራ ክልል የተፈጠረው የፀጥታ መደፍረስ በንግግር እንዲፈታ የእምነት ተቋማት እና የፖለቲካ ድርጅቶች ጥሪ አቀረቡ።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ካለፈው ጦርነት ውጤት በመማር የተፈጠረውን አለመግባባት በውይይት መፈታት አለበት ያለች ሲሆን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችም መንግሥት የተፈጠረውን ልዩነት በንግግር እንዲፈታ ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ሐሙስ ሐምሌ 27/2015 ዓ.ም. በወቅታዊ አገራዊ ጉዳይ ላይ አስቸኳይ ስብሰባ ካደረገ በኋላ በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል እየተደረጉ ባሉ ግጭቶች ተሳታፊ የሆኑ ወገኖቻችን ካለፈው ጦርነት በመማር በሰላማዊ መንገድ ተወያይተው ችግሩን እንዲፈቱ ጠይቋል።
ቤተ ክርስቲያኗ በተለያዩ ቦታዎች እየተከሰቱ ባሉት ግጭቶች እየጠፋ ባለው ውድ ሕይወት እና የንብረት ውድመት ጥልቅ ሐዘን ተስምቶኛል ያለች ሲሆን፤ ግጭት ተወግዶ ሰላም እና አንድነት እንዲሰፍን ከሁሉም በላይ እግዚአብሔርን በጾምና በጸሎት ልንማጸን ይገባል ብላለች።
ኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ምክትል ጠቅላይ ፀሐፊ ሐጂ መስዑድ አደም በተመሳሳይ በአገራችን በቅርቡ ከባድ ጦርነት ተካሂዶ ከፍተኛ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ኪሳራ ደርሶ ተመልክተናል፤ ከዚህ መማር አለብን ብለዋል።
ሐጂ መስዑድ አደም ለቢቢሲ ሲናገሩ “ጦርነት ለችግሮች መፍትሄ ያመጣል የሚል እምነት የለንም። መንግሥት በየትኛውም አግባብ ላሉ ችግሮች አስፈላጊ የሚላቸውን መልስ መስጠት አለበት። ጥያቄ ያላቸው አካላትም ጥያቄ ማቅረብ ያለባቸው በጥይት ሳይሆን በሰላማዊ ድርድር መሆን አለበት” ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ ምክትል ሰብሳቢ እና የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ዋና ፀሐፊ ዶ/ር ራሔል ባፌ ደግሞ “የወንድመማቾች የእርስ በእርስ ጦርትነት አገራችንን እጅግ ጎድቷታል፤ አስመርሯታል” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“ካለፈው መማር ይኖርብናል። ያደለው ከጎረቤት ይማራል። እኛ ከራሳችን መማር አልቻልንም። ትናንት በትግራይ የነበረውን ጦርነት እንዴት ተካሂዶ እንዴት እንደተቋጨ አይተናል። መጨረሻ ላይ በንግግር ነው የተፈታው። ይሄም በመነጋገር ሊፈታ የሚችል ነገር ነው” ብለዋል።
የትጥቅ ማስፈታት ሂደቱ በአግባቡ ባለመከናወኑ አሁን ያለንበት ችግር ውስጥ ገብተናል የሚሉ ዶ/ር ራሄል፤ መንግሥት ቀድሞ የሕዝቡን ስጋት ካስወገደ በኋላ ወቅቱን ያገናዘበ ውሳኔ ማለፈ አለበት ብለዋል።
“አሁን በሕዝብ እና በመንግሥት መካከል ልዩነት አለ። እየተነጋገሩ አይደለም። እንደ ፖለቲካ ፓርቲ የምንሰጠው ምክር መነጋገር አለባቸው። መንግሥት ለሕዝብ ጆሮ መስጠት አለበት። ባለቤቱ ነው ችግሩን የሚያውቀው። መንግሥት ችግሩን ካላደመጠ መፍትሄ ሊያመጣ አይችልም።”

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአሁኑ ወቅት በአማራ ክልል ላለው የደኅንነት ችግር አስቸኳይ መፍትሄ ካልተሰጠ ወደለየለት ጦርነት ሊገባ ይችላል የሚሉት ዶ/ር ራሄል፤ “ሕዝብ ከመጎዳቱ በፊት ወንድም ከወንድሙ ከመገዳደሉ በፊት ማስቆም ይቻላል” ብለዋል።
“ለእርስ በእርስ ችግር በንግግር እንጂ የአገር መከላከያን ተሳታፊ ማድረግ አግባብ አይደለም። መከላከያ ለዳር ድንበር ማስከበሪያ፤ አገር ጠባቂ ደጀን ነው እንጂ ለአገር ውስጥ ጦርነት መከላከያን ማሰለፍ አይገባም” ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ደግሞ የአገር መከላከያ ሠራዊት ከተቋቋመበት ዓላማ ውጭ ለፖለቲካዊ ፍላጎት ማሳኪያ የመጠቀም አባዜ እየተስተዋለ ነው ብሏል።
ፓርቲው በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በአንድ በኩል በመንግሥት ኃላፊዎች ንዝህላልነት እና ደባ፣ በሌላ በኩል ደግሞ በዘውግ ማኅበረሰብ ስም በተደራጁ ታጣቂዎች አማካይነት ጉዳት እየደረሰበት ነው ብሏል ሐምሌ 24/2015 ዓ.ም. አውጥቶት በነበረው መግለጫ።
“በየትኛውም የዘውግ ማኅበረሰብ ስም ተደራጅታችሁ በታጣቂነት የምትንቀሳቀሱ ኃይሎች በኢትዮጵያ ምድር ማዕከላዊ ዕዙ የተጠበቀ የፀጥታ መዋቅር አለመኖሩ ሁላችንንም እንደማኅበረሰብ ወደ መቀመቅ እንደሚከተን በመገንዘብ፤ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትን እረፍት መንሳት እና ቃታ መሳብ በአስቸኳይ እንድታቆሙ እንጠይቃለን” ብሏል ፓርቲው።
የአማራ ክልል መንግሥት ያጋጠመው ቀውስ ከአቅሙ በላይ መሆኑን በመግለጽ የፌደራል መንግሥቱ ጣልቃ እንዲገባ ባቀረበው ጥያቄ መሠረት፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በክልሉ ላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደንግጓል።
በዚህም የፌደራል መንግሥቱ የመከላከያ ሠራዊቱን እና የፀጥታ ኃይሎችን ወደ ክልሉ በማሰመራት ሕግ እና ሥርዓትን የማስከበር እርምጃ ይወስዳል።












