የትራምፕ ትሩዝ ሶሻል ከጉግል ፕሌይ ታገደ

ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ዶናልድ ትራምፕ

የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናለድ ትራምፕ የስጀመሩት 'ትሩዝ ሶሻል' የተሰኘው ማህበራዊ ሚዲያ ከጉግል ፕሌይ ታገደ።

እንደ ጉግል ከሆነ እርምጃው የተወሰደው እንደ 'ትሩዝ ሶሻል' ማስፈራራት እና ግጭት ማነሳሳት የሚሉ ፖሊሲዎቹን ስለሚጥስ ነው።

እርምጃው የአንድሮይድ ስልክ የሚጠቀሙ ሰዎች መተግበሪያውን አውርደው እንዳይጠቀሙ እንቅፋት ይሆንባቸዋል።

የትሩዝ ሶሻል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዴቪን ኑኔዝ ከዚህ ቀደም ጉግልን በአንድ ቡድን በቁጥጥር ሥር ያለ ነው ሲሉ ገልጸውታል።

ትሩዝ ሶሻል መጀመሪያ በአፕል አፕ ስቶር ላይ የተለቀቀው ባለፈው መጋቢት ቢሆንም ብዙ እንቅፋቶች አጋጥመውታል።

የትሩዝ ሶሻል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ባለፈው ሳምንት እንዳስታወቁት መተግበሪያው የመኖር አለመኖሩ ውሳኔ “የጉግል ፕሌይ ነው” ሲሉ ተደምጠዋል።

ጉግል ደግሞ ሕጉን የማክበር ውሳኔ የትሩዝ ሶሻል ነው ሲል ገልጿል።

የጉግል ቃል አቀባይ ለቢቢሲ “ነሐሴ 13/2014 ዓ.ም. ላይ ትሩዝ ሶሻል በርካታ መሠረታዊ ፖሊሲዎችን መጣሱን አሳውቀነዋል” ብለዋል።

"ይዘትን ለመቆጣጠር ውጤታማ ስርዓቶች በመኖራቸው መተግበሪያዎች በጉግል ፕሌይ ላይ እንዲሠሩ ቅድመ ሁኔታ ናቸው" ሲሉ አክለዋል።

ሶሻል ትሩዝ ችግሮቹን የሚፈታበትን አቅጣጫ መጠቆሙንም ጉግል አስታውቋል። ትሩዝ ሶሻል ከቢቢሲ ለቀረበለት ጥያቄ ምላሽ አለስጠም።

ትሩዝ ሶሻል “የመናገር ነጻነት” የሚተገበርበት ሚዲያ ተብሎ ይገለጻል።

መተግበሪያው በብዙ ተንቀሳቃሽ ስልኮች ላይ እንዲሠራ ግን በአፕል እና ጉግል ፈቃድ ሊያገኝ ይገባል።

ትሩዝ ሶሻል ገደብ የለሽ የመናገር ነጻነት ቦታ ቢባልም መናገር በሚችሉት እና በማይችሉት ጉዳዮች ዙሪያ ብዙ ሕጎች አሉት።

ሶሻል ትሩዝ ላይ በሚለጠፉ እና በማይለጠፉ ይዘቶች ዙሪያ ረዥም ዝርዝር አለው።

መድረኩ የተመሠረተው በትራምፕ ሲሆን የቀድሞው ፕሬዝዳንት ሃሳባቸውን በማህበራዊ ሚዲያው ላይ መለጠፍን ይመርጣሉ። ትራምፕ ካለፈው ዓመት የአሜሪካ ካፒቶል ሂል ግርግር በኋላ ከትዊተር እና ፌስቡክ ታግደዋል።

ትሩዝ ሶሻል ከተዛባ መረጃ እና የጥላቻ ንግግር ጋር ችግር አለበት ብለው ተቺዎች ይከራከራሉ።