የዝውውር መስኮቱ አምስት ትልልቅ ጉዳዮች

የዘንድሮው የክረምት ተጫዋቾች ዝውውር የተለያዩ ክብረ ወሰኖችን በማሻሻል ትላንት እኩለ ለሊት ተጠናቅቋል።
ማንቸስተር ዩናይትድ ለዝውውር መስኮቱ የመጨረሻ ቀን ክብረ ወሰን በሆነ 82 ሚሊዮን ፓውንድ አንቶኒን አስፈርሟል።
ይህን ጨምሮ የፕሪሚየር ሊጉ ክለቦች በመስኮቱ 1.9 ቢሊዮን ፓውንድ አውጥተዋል። ይህም ክብረ ወሰን ሆኖ ተመዝግቧል።
በ2017 ተመዝግቦ የነበረው 1.4 ቢሊዮን ፓውንድ ከፍተኛው የዝውውር ክፍያ የተፈጸመበት መስኮት ነበር።
ከ20ዎቹ የሊጉ ክለቦች ዘጠኙ ከ100 ሚሊዮን ፓውንድ በላይ ወጪ አድርገዋል።
በዘንድሮው የዝውውር መስኮት የፕሪሚር ሊጉ ክለቦች ከላሊጋ፣ ሴሪ አ እና ቡንደስሊጋ አጠቃላይ ድምር የሚበልጥ ወጪ ፈሰስ አድርገዋል።
ቼልሲ ከፍተኛውን ገንዘብ ለተጫዋቾች ዝውውር ወጪ ያደረገ ክለብ ሆኗል። ማንቸስተር ደግሞ የክለቡን የክረምት የዝውውር ክብረ ወሰን አሻሽሏል።
ኖቲንግሃም ፎረሰት ብዙ ተጫዋቾችን በአንድ ዝወውር ማስፈረም የቻለ እንግሊዝ ክለብ ሆኗል።
ክለቦቹ ካለፈው የዝውውር መስኮት በ1.1 ቢሊዮን (67 በመቶ) የሚበልጥ ወጪ አድርገዋል።
በአምስቱ ታላላቅ የአውሮፓ ሊጎች ለተጫዋቾች ወጪ የወጣው ገንዘብ በ52 በመቶ (3.88 ሚሊዮን ፓውንድ) ጨምሯል።
ከዚህ ውስጥ 49 በመቶው የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ነው።
የፕሪሚየር ሊጉ ክለቦች 169 ተጫዋቾችን አስፈርመዋል።
በመጨረሻ የዝውውር መስኮት ቀን የትኞቹ የተሳኩ ዝውውሮች
የፕሪሚየር ሊጉ 14 ክለቦች በመስኮቱ የመጨረሻ ቀን ቢያንስ አንድ ተጫዋች ለማስፈረም ችለዋል። ጥቂቶቹን የተሳኩ ዝውውሮች እንመልከት።
ማንቸስተር ሲቲ የተከላካይ ክፉሉ ለማጠናከር ከቦሩሲያ ዶርትሙንድ ማኑዌል አካንጂን ማስፈረም ችሏል።
ከአንቶኒ በተጨማሪ ማንቸስተር ዩናይትድ ከኒውካስል ግብ ጠባቂውን ማርቲን ደብራቭካን በውሰት አስፈርሟል።
ኤቨርተን ደግሞ ሁለት አማካዮችን ማስፈረም ችሏል። ኢድሪሳ ጌይ እና ጀመስ ጋርነር ቡድኑን ተቀላቅለዋል።
ሊቨርፑል በበኩሉ ብራዚላዊውን አማካይ አርተር ሜሎን ከጁቬንቱስ በውሰት ማስፈረም ችሏል።
ሌስተር በበኩሉ ከሬሚስ ተከላካዩ ዉት ፋዬስን በአምስት ዓመት ውል የራሱ አድርጓል።
ኖቲንግሃም ፎረሰት 21ኛውን ተጫዋች በዝውውር መስኮቱ አስፈርሟል። ሎይክ ባድን ከሬንስ በአምስት ዓመት ውል አስፈርሟል።
ፉልሃም የቀድሞውን አርሴናል እና የቼልሲ አማካይ ዊሊያንን ጨምሮ አራት ተጫዋቾችን በማስፈረም የዝውውር መስኮቱን አጠናቋል።
ቼልሲ በበኩሉ ፒየር-ኤመሪከ ኦባመያንግን እና ዴኒስ ዛካሪያን የግሉ ማድረግ ችሏል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከፍተኛ ወጪ ያደረጉ 5 ክለቦች
ቼልሲ በአዲሱ ባለቤት እጅ ከገባ በኋላ 250 ሚሊዮን ፓውንድ ወጪ በማድረግ ዝውውሩን አጠናቋል።
ሪያል ማድሪድ (292 ሚሊዮን ፓውንድ) በአንድ የዝውውር መስኮት ወጪ ካደረገ በኋላ በአንድ ክለብ የወጣ ከፍተኛ ገንዘብ ሆኗል።
ማንቸስተር ዩናይትድ የከለቡን ክብረ ወሰን በመሰባበር በሊጉ የወጪ የደረጃ ሰንጠረዥ ሁለተኛ ላይ ለመቀመጥ ችሏል።
እንደ ካስሜሮ እና አንቶኒ ያሉ ተጫዋቾችን ለማስፈረም 214 ሚሊዮን ፓውንድ ወጪ አድርገዋል።
እንደ ኤርሊንግ ሃላንድ፣ ዳርዊን ኑኔዝ፣ ጋብርኤል ጄሱስ የመሳሰሉ አጥቂዎች በብዛት የተዘዋወሩበት መስኮት ነበር።
ከፍተኛ ወጪ ያደረጉ አምስት ክለቦች
- ቼልሲ 251 ሚሊዮን ፓውንድ
- ማንቸስተር ዩናይትድ 214 ሚሊዮን ፓውንድ
- ዌስት ሃም 163 ሚሊዮን ፓውንድ
- ቶተንሃም 152 ሚሊዮን ፓውንድ
- ኖቲንግሃም ፎረስተ 145 ሚሊዮን ፓውንድ
አዲስ ቡድን የገዛው ቡድን
ኖቲንግሃም ፎረስት እአአ ከ1999 በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ተመልሷል። በሊጉ ለመቆየትም የወሰነ ይመስላል።
የስቲቭ ኩፐር ቡድን በዝውውር መስኮቱ 21 ተጫዋቾችን ማስፈርም ችሏል። 145 ሚሊዮን ፓውንድ ወጪ ሲያደርግ በአንድ መስኮት ብዙ ተጫዋቾችን ያስፈረመ የብሪታኒያ ከለብ ለመሆን በቅቷል።
እንደ ትራንስፈርማርኬት ከሆነ በ2013 ነበር ክሪስታል ፓላስ 17 ተጫዋቾችን በማስፈረም ክበረ ወሰኑን የያዘው።
ከብረ ወሰኑ ከዚህም በላይ ይሻሻል ነበር። ከቼልሲ ሚቺ ባትሹዋይን ለማስፈርም ያደረጉት ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ገንዘብ ያመጣው ጫና
ብዙዎቹ ክለቦች ገንዘብ ወጪ አድርገው ተጫዋቾችን ሲያስፈርሙ በገንዘብ እጦት እጃው የተሽመደመደም አሉ።
በሊቨርፑል 9-0 ከተሸነፉ በኀወላ የበርንማውዞቹ አለቃ የነበረው ስኮት ፓርከር የነበሩበትን ሁኔታ “የማያፈናፍን” ሲል ገልጾታል።
ከሁለት ቀን በኋላ የክለቡ አለቃ አሰልጣኙን በማሰናበት ምላሽ ሰጡ።
ሌስተርም ቀዝቀዝ ያለ የዝውውር መስኮት ነው ያሳለፈው። እንደ ካስፐር ሺማይክል እና ፎፋና ያሉ ጥሩ ስም ያላቸው ተጫዋቾችን አሳልፎ ቢሰጥም ሁለት ተጫዋቾችን ብቻ ነው ያስፈረመው።
ሜዳ ላይ ውጤት የጠመመባቸው የሚመስሉት ቀበሮዎቹ በማንቸስተር ዩናይትድ 1-0 ከተሸነፉ በኋላ ደጋፊዎቻቸው ቅሬታቸውን በጩኸት ገልጸዋል።
እንደ ፓርከር ሁሉ ብሬንዳን ሮጀርስም ቅሬታቸውን በተመሳሳይ በይፋ አሳውቀዋል።
ከዩናይትድ ሽንፈት በኋላ “የደጋፊዎችን ቅሬታ እኔም እገነዘባለሁ። ተቀናቃኞቻችን ሲጠናከሩ ምንም አላደረግንም” ብለዋል።
“እንደሌሎች ክለቦች ባለመንቀሳቀሳችን ከባድ ሆኖብናል። ልንደገፍ ይገባል። ግን አልሆነም” ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል።
“በማክበር መግለጽ የምፈልገው በዚህ ዝውውር መስኮት በሚገባው መልኩ አልተደገፍንም” ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ያልተሳኩት ዝውውሮችስ?
ከፍተኛ ወጪ ቢደረግም ያልተሳኩ የዝውውር ሙከራዎች ግን አልጠፉም።
ማንቸስተር ዩናይትድን ለመልቀቅ ፈልጎ የነበረው አጥቂው ክርስቲያኖ ሮናልዶ በኦልድትራፎርድ ለመቆየት ተገዷል።
በሌላ በኩል ማንቸስተር ዩናይትድ እና ባርሴሎና በፍራንኪ ዲ ዮንግ ዋጋ ከስምምነት መድረስ ችለው ነበር። ክረምቱን በሙሉ ሲጓተት የቆየው ዝውውር ግን ፍሬ አልባ ሆኗል።
ቼልሲ ደግሞ ከኤቨርተን የክንፍ ተጫዋቹን አንቶኒ ጎርደንን ለማስፈርም ጥረት አድርጎ ነበር። ቶፊዎቹ መሸጥ ባለመፈለጋቸው ተጫዋቹ በክለቡ ለመቆየት ችሏል።
አርሴናል ባለቀ ሰዓት ፊቱን ወደ አስቶን ቪላ በማዞር አማካዩን ዳግላስ ሉዊዝን ለማስፈረም ያደረገው ጥረት ውድቅ ተደርጎበታል።
አስገራሚው ግን የባምባ ዲዬንግ የዝውውር ጉዳይ ነው።
ሊድስ አጥቂውን ከማርሴይ እንደሚያስፈርም እርግጠኛ ሆነ። ሊቀመንበሩ አንድሪያ ራድሪዛኒም ክለባቸው ተጫዋቹን ሊቀበል መዘጋጀቱን ትዊተር ጋጻቸው ላይ አሰፈሩ።
ወደ እንግሊዝ ለመብረር እና ዝውውሩን ለማጠናቀቅ የ22 ዓመቱ ተጫዋች አየር መንገድ ተገኘ። በዚህ ወቅት ኒስ ጣልቃ በመግባት ተጫዋቹን ለማስፈርም ወሰነ።
ግን ሳይሳካ ቀረ።
የዘጠኝ ሚሊዮን ዩሮው ዝውውር ግን ተጫዋቹ የጤና ምርመራ ማለፍ ባለመቻሉ ሳይሳካ ቀረ።
ከሁለት ያጣው ተጫዋች ዝውውር በተመለከተ ራድሪዛኒ በድጋሚ ወደ ትዊተር በመመለስ “ከዝውውር መስኮቱ የመጨረሻ ቀን እብደቶች አንዱ” ሲሉ ገለጹት።












