ባይደን የትራምፕ ደጋፊዎች ለአሜሪካ ዴሞክራሲ ‘ስጋት’ ናቸው አሉ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የቀድሞ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ‘ሜክ አሜሪካ ግሬት አጌይን’ (ማጋ) አጀንዳ ደጋፊዎች የአሜሪካ ዴሞክራሲ ስጋት ናቸው ሲሉ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ተናገሩ።
‘አሜሪካንን ዳግም ኃያል እናድርጋት’ የሚለውን አጀንዳ የሚያራምዱ ኃይሎች አገሪቱን ‘ወደ ኋላ ለመመለስ ቆርጠዋል’ ሲሉ ፕሬዝዳን ባይደን ተናግረዋል።
ባይደን ይህን ንግግር ያደረጉት ትናንት ሐሙስ ነሐሴ 26 የአሜሪካ የነጻነት አዋጅ በተፈረመባት ፊላዴልፊያ ነው።
ጆ ባይደን በንግግራቸው እአአ 2020 ተካሂዶ በነበረው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ለዶናልድ ትራምፕ ድምጻቸውን የሰጡ 70 ሚሊዮን አሜሪካውያንን በሙሉ እየተቹ እንዳልሆነ ተናግረዋል።
ባይደን የሪፓብሊካን ፓርቲ በዶናልድ ትራምፕ ተጽዕኖ ውስጥ እንደሚገኝ እና ‘የማጋ’ ጽንሰ ሃሳብ አራማጅ የሆኑ ሪፓብሊካኖች ለአገሪቱ ስጋት መሆናቸውን ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንት ባይደን ባለፈው ዓመት ወደ ካፒቶል ሂል ሕንጻ በኃይል ዘልቀው የገቡት የትራምፕ ደጋፊዎች አገር ወዳድ ሳይሆኑ አመጸኞች ናቸው ብለዋል።
ባይደን “ለረዥም ጊዜ የአሜሪካ ዴሞክራሲ የተረጋገጠ እንደሆነ ለራሳችን ስንነግር ቆይተናል። ይህ ግን አይደለም። ዴሞክራሲን ልንከላከል ይገባል። እያንዳንዳችን ዴሞክራሲን መጠበቅ አለብን” ብለዋል።
ዴሞክራቱ ባይደን ይህን ንግግራቸውን እያደረጉ ሳለ ከታዳሚዎች ከአንድም ሁለት ጊዜ የተቃውሞ ድምጽ ተሰምቶ ነበር። ባይደን ለዚህ የተቃውሞ ድምጽ ምላሽ ሲሰጡ “የመናደድ መብት አላቸው። ይህ ዴሞክራሲ ነው” ብለዋል።
ቁንጮ ከሆኑ ሪፓብሊካኖች መካከል አንዱ የሆኑት ኬቪን ማካርቲ ፕሬዝዳንት ባይደን አገሪቱን ለመከፋፈል መርጠዋል ብለዋል።
“ለምን? ምክንያቱም በፖሊሲያቸው ስለማይስማሙ። ይህ የአመራር ብቃት አይደለም” ብለዋል የካሊፎርኒያው የኮንግረስ አባል ማካርቲ።
የሪፓብሊካን ፓርቲ አባሉ ጨምረውም በባይደን አስተዳደር ወቅት በአሜሪካ ምጣኔ ሃብት የዋጋ ንረት መከሰቱን፣ በኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት ትምህርት ቤቶች መዘጋታቸው የልጆችን ትምህርትን መጉዳቱን፣ በመላ አገሪቱ ወንጀል መጨመሩን እና አሜሪካ ከአፍጋኒስታን የወጣችበትን ሁኔታ በማስታወስ የባይደን አስተዳደርን ተችተዋል።
ባለፉት ሁለት ዓመታት ባይደን በአሜሪካውያን ዘንድ ያላቸው ተቀባይነት እየቀነሰ መጥቷል። ከባይደን ንግግር በኋላ በአሜሪካዋ አነስተኛ ከተማ ኒውፋወንድላንድ ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ዴሞክራሲ ላይ ተጋርጧል ከተባለው አደጋ ይልቅ ያሳሰባቸው የነዳጅ ዋጋ ከፍ ማለት ነው።
በዚህ አነስተኛ ከተማ ያሉት ድምጽ ሰጪዎች በትራምፕ አስተዳደር እና በባይደን አስተዳደር ወቅት ያለውን የምጣኔ ሃብት ሁኔታን ማነጻጸርን ይመርጣሉ።












