ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ መንግሥት እና ህወሓት ወደ ድርድር እንዲመጡ ጫና ማሳደር ይችላል?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአየርላንድ ሪፐብሊካን አርሚ (አይአርኤ) ከብሪታኒያ አገዛዝ የመውጣት አላማ አንግቦ በፈረንጆቹ 1919 ተቋቋመ።
ከዘመናት ግጭትና የሰው ሕይወትና ንብረት ውድመት በኋላ በ1997 ‘ጉድ ፍራይደይ’ ተብሎ በሚታወቀው ቀን የብሪታኒያ መንግሥትና የአይአርኤ ተዋጊዎች ለድርድር ተቀመጡ።
የአየርላንድ ተዋጊዎችና የብሪታኒያ መንግሥት ወታደራዊ ፍጥጫ ላይ በነበሩበት ወቅት ግጭቱ ጋብ እንዲል ሲጮሁ ከነበሩት መካከል የቀድሞው የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ኔልሰን ማንዴላ ይጠቀሳሉ።
ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ስንጓዝ ኢራቅና ኢራን በፈረንጆቹ 1980 ጦርነት ውስጥ ከገቡ ከስምንት ዓመታት በኋላ ነው ወደ እርቅ መድረክ የመጡት።
ይህንን የሰላም ድርድር የመራው የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ነው።
በጎረቤት አገራት መካከል ግጭት ሲነሳ አሊያም በአንድ አገር ውስጥ የእርስ በርስ ግጭት ሲቀሰቀስ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በሚባል ቅጥያ የሚታወቁት ኃያላን አገራት ግጭት እንዲበርድ የራሳቸውን አስተዋፅዖ ያደርጋሉ።
ነገር ግን እነዚህ ኃያላን አገራት ሁሌም ተሳክቶላቸዋል ማለት አይቻልም።
ከኃያላኑ አገራት ባለፈ እንደ የተበባበሩት መንግሥታት ያሉ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና ቀጠናዊ ኅብረቶች ሰላም የማስፈን ግዴታ [ማዕቀፋቸው ላይ የሰፈረ] አለባቸው።
የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በመባል የሚታወቀው ድርጅት ወደ አፍሪካ ኅብረት ስሙን ሲቀይር አንደኛው ዓላማው የነበረው አፍሪካ ውስጥ የሚቀሰቀሱ ግጭቶችን በአፍሪካ መፍታት የሚል ነበር።
ቢሆንም ድርጅቱ ሁለት ዓመት ሊደፍን ጥቂት ወራት የቀሩትን የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ማስቆም የቻለ አይመስልም።
ከአፍሪካ ኅብረት አልፎ እነ አሜሪካ፣ አውሮፓና የተባበሩት መንግሥታት ይህን ግጭት ለማስቆም እንጥራለን ቢሉም ጋብ ብሎ የነበረው ግጭት እንደ አዲስ አገርሽቷል።
ኃያላን አገራት የራሳቸውን ጥቅም ማስከበር እንጂ ሰላም የማምጣት ፍላጎት የላቸውም የሚሉ ተንታኞችም አሉ።
በሌላ በኩል ተዋጊዎቹ ፈቃደኛ ካልሆኑ አደራዳሪዎች ያላቸው ሚና ውሱን ብሎ የሚከራከሩም አሉ።
ነገር ግን ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነት በተመለከተ መግለጫ ከማውጣት ባለፈ ምን ሊያደርግ ይችላል? ሁለቱ ወገኖች ወደ ሰላም እንዲመጡ የማድረግ ኃይልስ አለው?

‘የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ገለልተኝነት’
የፌዴራሉ መንግሥት የአፍሪካ ኅብረት ልዩ መልዕክተኛ ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ ድርድሩን እንዲመሩት ፍላጎት አለው። ህወሓት ደግሞ ተሰናባቹ የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ እንዲያደርድሩ ይሻል።
ነገር ግን ይህ ከጫፍ ሳይደርስ፤ አደራዳሪው ሳይለይ አሊያም ድርድሩ የትና መች እንደሚካሄድ ሳይታወቅ ነው ድጋሚ ጦርነት የተቀሰቀሰው።
መንግሥት፤ አማፂው ኃይል ‘ድርድሩን ስለማይሻ’ አፈሙዝ መርጧል ሲል ይወቅሳል። ህወሓት በበኩሉ ማዕከላዊው መንግሥት ‘ጠብ ጭሯል’ የሚል ተደጋጋሚ ክስ ያቀርባል።
ጦርነቱ እንደ አዲስ ማገርሸቱን የሰሙ ምዕራባዊያን አገራት ግጭቱ እንዲበርድ ሁለቱን አካላት ከማሳሰብ አልቦዘኑም።
አገራት፣ አህጉራዊና ቀጣናዊ ድርጅ እንዲሁም የዓለም አቀፍ ተቋማት ጋብ ብሎ የነበረው ጦርነት መቀስቀሱ እናዳሳሰባቸውና ሰላም ወርዶ ድርድር እንዲጀመር ጥሪ እያቀረቡ ነው።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰላም ጥናት ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆነት ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) “ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የገለልተኝነት ጥያቄ አለበት” ይላሉ።
“የሰላም መሠረታዊ ፍልስፍና አዎንታዊ አስተሳሰብ ነው፤ ነገር ግን መሬት ላይ ያለውን እውነታ ማየትም አስፈላጊ ነው” የሚሉት ምሑሩ፤ እውን ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ገለልተኝነቱን ይጠብቃል ወይ? የሰላምን ትርጉም ይረዳል ወይ? ሲሉ ይጠይቃሉ።
በአሜሪካ ዓለም አቀፍ ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ ግኑኝነቶች ምሑሩ ፕሮፌሰር ማቻሪያ ሙኔኔ በበኩላቸው “አደራደሪዎቹ ሁለቱን ወገኖች ወደ ጠረጴዛ ለማምጣት የሚያስችል ማስተማመኛ አላቸው ወይ?” የሚል ጥያቄ ያነሳሉ።
ፕሮፌሰሩ፤ “በትግራይ በኩል ጦርነቱ ከቆመ በኋላ ምን ይፈጠራል የሚል ስጋት” አለ፤ “በመንግሥት በኩል ደግሞ፣ ህወሓት ዳግም መደራጀቱ የፈጠረው ስጋት እንዳለ ይታየኛል” ይላሉ።
ኬንያዊው ምሑር እንደሚሉት ቀውሱ ሊፈጥረው የሚችለው ቀጠናዊ ስጋት አሳሳቢ ስለሆነ የአገራቸው የኬንያ መንግሥትን ጨምሮ ሌሎች ግጭቱ እንዲቆም ይሻሉ።
ተባባሪ ፕሮፌሰር ዮናስ አዳዬም በሙኔኔ ሐሳብ ይስማማሉ።
“ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላም ጠፋ ማለት ምሥራቅ አፍሪካ ሰላም ጠፋ ማለት ነው። ለኬንያ እና ሱዳን እንዲሁም ለሌሎች አካባቢዎች መዘዝ ይኖረዋል። ሌላው ቀርቶ አሜሪካና አውሮፓ በዚህ አካባቢ ያላቸው ፍላጎት ይነካል ማለት ነው።”
ዮናስ (ዶ/ር) እንደሚሉት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሰላምን ትርጉም ተረድቶት ነው ወይስ ብሔራዊ ጥቅሙን አስቀድሟል የሚለው ወሳኝ ነው።
የኢትዮጵያ የእርስ በእርስ ጦርነት በሰላማዊ መንገድ መፍትሄ እንዲያገኝ ሁለቱ ተፋላሚ ኃይሎች ለማነጋገር የአፍሪካ ኅብረት፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ አሜሪካ እና አውሮፓ የተለያዩ ጥረቶች አድርገዋል።
ተፋላሚዎቹ ወገኖች ሰላም ለማምጣት የሚያስችሉ አማራጮችን እንዲያዩ፣ ያሏቸውን ስጋቶች እንዲነጋገሩ ከይፋዊ ድርድር በፊት በምስጢር ሊገናኙ እንደሚችሉ ተንታኞች ይናገራሉ።
ተባባሪ ፕሮፌሰር ዮናስ አዳዬ ግጭቱ በአፍሪካ ኅብረት አማካኝነት መፈታት አለበት ብለው ያምናሉ።
“እርግጥ ችግሩ የአፍሪካ ብቻ አይደለም። ግን በዋናነት ችግሩን ለመፍታት አፍሪካውያን መሪዎች እና አፍሪካውያን አደራዳሪዎች መኖር አለባቸው። ስለዚህ መሠረታዊው ነገር አውድ ነው። ከአውድ ውጪ የሆነ ነገር መናገር ሌላ ፍላጎት ማሳየት ነው።”
ፕሮፌሰር ሙኔኔ ደግሞ በመንግሥትም ሆነ በህወሓት በኩል ተቀባይነት ያለው ሰው ሊኖር ይገባል ይላሉ።
“ለማደራደር የተላከው ሰው በሁለቱም በኩል ተቀባይነት ከሌለው ብክነት ነው” የሚሉት ምሑሩ “የዚህ ጦርነት መጨረሻ ውድመት መሆኑን ማሳመን የሚችል ብቃት ያለው ሰው እስኪገኝ ግን ጦርነቱ ይቀጥላል” የሚል ስጋት አላቸው።
“የአፍሪካ ኅብረትም ሆነ የተባበሩት መንግሥታት ያላቸው የመተማመኛ ዋስትና የሚጠበቀውን ያህል አልሆነም። ይህ እስኪገኝ ጦርነቱ ይቀጥላል።”

የፎቶው ባለመብት, AFP
ጫና ማሳደር ይቻል ይሆን?
ኃያላን የሚባሉ አገራትን ጨምሮ ዓለም እና አህጉር አቀፍ ድርጅቶች ጫና ለማሳደር ቢጥሩም የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ዳግም ተቀስቅሷል።
ነገር ግን አሁንም የዓለም መንግሥታት እና ጎረቤት አገራት የፌደራል መንግሥቱ እና ህወሓት ለድርድር እንዲቀመጡ ጫና ማሳደር እንደሚችሉ አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ።
“ግልፅነት ካለ፣ ተዓማናኒነት ካለ፣ ገልለተኝነት ካለ ይቻላል። ሕፃናትን አታስገድሉ፣ ጦርነቱ ሁላችሁንም ይጎዳል፣ ብለው መናገር፣ ማናገር፣ ማቀራረብ ይችላሉ” ይላሉ ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር)።
ቢሆንም ይላሉ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው ምሑር፤ “አሸማጋይ ሆኖ የሚሄድ ሰው መጀመሪያ ለአንዱ የወገነ ከሆነ አስቸጋሪ ነው የሚሆነው።”
አሜሪካ የኢትዮጵያ መንግሥት የተናጠል የተኩስ አቁም ስምምነት ከማወጁ በፊት ማዕከላዊው መንግሥት ላይ በተለያዩ መንገዶች ጫና ታሳድር እንደነበር ምሑራን ይናገራሉ።
አንደኛው ማሳያ አሜሪካ፤ ኢትዮጵያ አባል ከሆነችበት የአጎዋ የንግድ ስምምነት እንድትሰረዝ ማድረጓ ነው።
በወቅቱ የኢትዮጵያ መንግሥት በዚህ ውሳኔ ምክንያት ከ200 ሺህ በላይ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ቤተሰቦች እንደተጎዱ ጠቅሶ፣ በተለይም ከግጭቱ ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸው ሴቶች ላይ ጉዳቱ ይበረታል በማለት ተቃውሞት ነበር።
የአሜሪካ መንግሥት ባለፈው ዓመት በጦርነቱ ሳብያ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ ባለሥልጣናት፣ ወታደራዊና የደኅንነት አባላት፣ እንዲሁም በአማራ ክልል ኃይሎች እና በህወሓት አባላት ላይ የቪዛ ዕቀባ መጣሉ የሚታወስ ነው።
በወቅቱ ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የወጣው መግለጫ፤ ይህ ውሳኔ ግጭቱ እንዲቆምና የኤርትራ ወታደሮች ከክልሉ እንዲወጡ፣ የሰብአዊ ዕርዳታ አቅርቦት እንዲሻሻል እንዲሁም በግጭቱ ተሳታፊ የሆኑት ኃይሎች ወደ ድርድር እንዲመጡ የተደረገው ጥረት ባለመሳካቱ ነው ብሎ ነበር።
ተባባሪ ፕሮፌሰር ዮናስ፤ “ገለልተኛ በሆነ መንገድ በመሣሪያ ማዕቀብም ይሁን በተለያዩ መንገዶች ጫና ማሳደር ይችላሉ” ይላሉ።
ነገር ግን “ጫና ማሳደር ያለባቸው ትንኮሳ እያደረገ ያለው አካል ላይ መሆን አለበት” የሚል እምነት አላቸው።
ፐሮፌሰር ሙኔኔ በበኩላቸው ጫናው ምን ያህል ነው? የሚለው እንዳለ ሆኖ “ዕቀባ መጣል ግን ተጨባጭ ለውጥ እንደማያመጣ ከዚህ በፊት ታይቷል” ሲሉ ይከራከራሉ።
“ኤርትራ የተለያየ ማዕቀብ ቢጣልባትም የቀየረው ነገር የለም” ሲሉ የሚጠቅሱት ኬንያዊው ፕሮፌሰር “ኢትዮጵያ ላይ እንደ አገር ማዕቀብ መጣል ብዙም ለውጥ አያመጣም፤ ምክንያቱም ጉዳዩ መንግሥት ጋር ነው ያለው። መንግሥትና ሕዝብ ደግሞ የማዕቀቡ ጫና እኩል አይሰማቸውም” ባይ ናቸው።
የሰላም ጥናት ተመራማሪው ዮናስ አሁንም ቢሆንም በአፍሪካ ኅብረት የሚመራ ከሆነ የሰላም ድርድር ተስፋ አለ ብለው ያምናሉ።
“እኛ ስናስተምር የምንለው ምንድነው፡ there’s no way to peace; peace is the way [ወደ ሰላም የሚወስድ መንገድ የለም። ሰላም በራሱ መንገድ ነው) ነው የምንለው። አደራዳሪዎቹ ይህንን በሚገባ ተረድተው ግጭቱ እንዲበርድ የሚፈልጉ ናቸው? ወይስ የራሳቸውን ጥቅም ለማስከበር የአገዛዝ ለውጥ እንዲመጣ የሚሹ ናቸው?”
ምሑሩ በዚህ ረገድ እንደ ቻይና፣ ሩሲያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ኖርዌይና ዴንማርክ ያላቸውን አቋም ያደንቃሉ።
በአብዛኛው “ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ከሰላም ይልቅ አለመግባባትን ነው የሚፈጥረው” ብለው የሚከራከሩት ዮናስ፤ “ሊቢያ፣ ኢራን፣ ኢራቅ፣ አፍጋኒስታን ከ20 ዓመታት በኋላ የተፈጠረውን አይተናል” ብለው፤ “ነገር ግን ቅንነቱ ካለ መፍትሔ አይጠፋም” ሲሉ ያሰምራሉ።
“ለምሳሌ የአፍሪካ ኅብረት ፓነል ኦፍ ዘ ዋይዝ የሚባል አለ። በየቦታው እየተዟዟረ የሚያስታርቅ ነው። ቡሩንዲ ውስጥ ያለው ግጭት እንዲበርድ አስተዋፅዖ አድርጓል። ለዚህ ነው ቅንነት ካለ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሰላም ማምጣት ይቻላል የምለው።”












