ያገረሸው ጦርነት መጨረሻ ምን ሊሆን ይችላል? የሰላም ተስፋስ ይኖር ይሆን?

የወታደራዊ መሳርያ ሲንቀሳቀስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የኢትዮጵያን መንግሥት ቀድሞ ያወጀው የተናጠል ተኩስ አቁም ስምምነት ከአምስት ወራት በኋላ ያበቃ መስሏል።

ባለፉት አምስት ወራት እምብዛም የተኩስ ድምፅ ያልተሰማበት የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት አሁን ወደ ለየለት ግጭት ሊያመራ እንደሚችል ፍንጮች ያሳያሉ።

መንግሥት የተኩስ አቁሙን ሲያውጅ ዋነኛ ምክንያቱ እርዳታ ወደ ትግራይ ክልል እንዲገባ ለማድረግ መሆኑን አሳውቆ ነበር።

ባለፉት አምስት ወራት ማዕከላዊው መንግሥት እና የህወሓት አማፂያን ወደ ጠረጴዛ ለመምጣት ቃል ገብተው ጊዜና ቦታው እስኪታወጅ ድረስ ባለው ጊዜ ነው አዲስ ግጭት የተቀሰቀሰው።

ምንም እንኳ ባለፉት ወራት ሁለቱም ወገኖች የሰላም ድርድር ለማድረግ ሲጣጣሩ ቢታዩም ወደ ከፋ ግጭት ሊገቡ እንደሚችሉ የሚያሳዩ ፍንጮች ነበሩ ይላሉ ቢቢሲ ያናገራቸው የፖለቲካ ተንታኞች።

የምሥራቅ አፍሪካ እና መካከለኛው ምሥራቅ ፖለቲካዊ ሁኔታን በመተንተን የሚታወቁት አብዱራህማን ሰዒድ ከጥቂት ሳምንታት በፊት "ሁለቱም ኃይሎች ከሁለት ዓመት ጦርነት በኋላ አረፍ አሉ እንጂ ለድርድር የሚሆን ዝግጅት አላደረጉም" ሲሉ ተናግረው ነበር።

የኹንስ ዩኒቨርሲቲው የታሪክ ፕሮፌሰር ዓወት ተወልደሚካዔልም እንዲሁ መንግሥትና ህወሓት በድርድሩ ላይ ከስምምነት አለመድረሳቸው የሚያሰጋ ነው የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ማኅበር ኃላፊ ያሬድ ኃይለማርያም ጦርነቱ ዳግም ከማገርሸቱ ጥቂት ቀናት በፊት በከፍተኛ ባለሥልጣናት መካከል ያለው የቃላት ልውውጥ አስጊ ነው የሚል ሐሳባቸውን ሰጥተው ነበር።

"ሁለቱም ወገኖች ለሰላም ያላቸው ዝግጁነት ትልቅ ጥያቄ ምልክት ውስጥ ነው" የሚሉት ተቀማጭነታቸው ለንደን የሆኑት አብዱራህማንን ጨምሮ ሌሎችም ተንታኞች፣ ሁለተኛው ዙር ጦርነት ከመጀመሪያው የከፋ ሊሆን ይችላል የሚል ግምት አላቸው።

ለመሆኑ እንደ አዲስ የተቀሰቀሰው ጦርነት ከፍተኛ ጥፋት ሊያደርስ ይችላል የሚል ስጋት የመነጨው ከየት ነው?

የዚህ ጦርነት መጨረሻ ምን ሊሆን ይችላል? አንደኛው ወገን ሊረታ ይችል ይሆን ወይስ ተመልሰው ወደ ሰላም ድርድር ይመጡ ይሆን?

ሰብዓዊ ቀውስ

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የሰሜኑ ጦርነት፣ በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች የሚታዩ ግጭቶች እና የተራዘመ ድርቅ ያስከተሏቸው መፈናቀሎች አስቸኳይ ሰብአዊ እርዳታ የሚያስፈልገው የሕዝብ ቁጥር እንዲጨምር አድርገዋል።

በዚህ ዓመት ብቻ ከ20 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ሰብዓዊ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው የተባበሩት መንግሥታት አመልክቷል።

በሰሜን ኢትዮጵያ 700 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች የረሃብ አደጋ እንደተደቀነባቸው መረጃዎች ያመላክታሉ።

ከ60 ሺህ በላይ ሰዎች ደግሞ ወደ ሱዳን ተሰደዋል፤ ሁለት ሚሊዮን ገደማ ሰዎች በትግራይ ክልል ውስጥ ተፈናቃይ ሆነዋል።

በትግራይ ክልል ብቻ ከ5.5 ሚሊዮን ሕዝብ ግማሹ "ከባድ" የምግብ እጥረት ውስጥ ይገኛል።

የመድኃኒት እና የገንዘብ እጥረት፣ የጤና ማዕከላት እና ሆስፒታሎች መውደም ሰብአዊ ቀውሱን አባብሰውታል።

በአጎራባች የአማራ እና የአፋር ክልሎችም እንዲሁ ከተኩስ አቁም በፊትና በኋላ በመቶ ሺዎች ጦርነቱን በመሸሽ ቤት ንብረታቸውን ጥለው ተሰደዋል። አሁን እየተሰደዱ እንደሚገኙ ከሰሞኑ የወጡ መረጃዎች ያሳያሉ።

ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ሁሉም የጦርነቱ ተሳታፊ የነበሩ ታጣቂ ኃይሎች ከሕግ ውጪ የሆኑ ግድያዎች፣ ማሰቃየት እና ጾታዊ ጥቃቶች መፈጸማቸው የሚያሳዩ ሪፖርቶች አሉ።

አሁን እንደ አዲስ የተቀሰቀሰው ጦርነት እነዚህ ችግሮች ሊያባብስ እንደሚችልና ከፍተኛ ውድመት ሊያደርስ እንደሚችል ተንታኞች ይገልጣሉ።

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ዋና ፀሐፊ የሆኑት ራሔል ባፌ (ዶ/ር) ድጋሚ ወደ ጦርነት መግባታችን "እንደ አገር ውድቀት ነው" ይላሉ።

"ሌላው ወደ ብሔራዊ ምክክር እየሄደ ባለበት ወቅት ወደ ጦርነት መግባት ምን ተልዕኮ ይኖው ይሆን ያስብላል።"

ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ የደኅንነት ባለሙያ በበኩላቸው "ጦርነቱ፣ ችግር ላይ በወደቀው የአገሪቷ ኢኮኖሚ ተጨማሪ ጫና በመፍጠር የሚፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር በእጥፍ እንዲጨምር ያደርጋል" ይላሉ።

የፖለቲካ ተንታኝ የሆኑት አብዱራህማን ሰዒድም እንዲሁ በማንኛውም ጊዜ ጦርነት ሰላማዊ ሰው እንደሚጎዳ በማስታወስ፣ እንደ አዲስ የተቀሰቀሰው ጦርነት ትግራይ ውስጥ ያለውን ችግር ሊያባብስ ይችላል የሚል ስጋት አላቸው።

"የመሠረተ ልማት መውደም ብቻ ሳይሆን ሕይወቱ እየጠፋና አካሉ እየጎደለ ያለውን ወጣት ትተን ከትምህርትና ከመደበኛ ኑሮው እየተስተጓጎለ ያለው ሕዝብ ላይ ትልቅ ቁስል የሚተው ይሆናል። በርካቶችም ለስደት መዳረጋቸው አይቀርም።"

ተንታኙ አክለው ለትምህርት እና ለጤና መዋል የነበረበት በጀት ለጦር መሳሪያ፣ ለሠራዊት ቀለብና የጤና አቅርቦት መዋሉ ቀውስ ያመጣል ይላሉ።

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ዋና ፀሐፊዋ ራሔል "ጦርነቱ የሚያመጣው ጉዳት ለሁለቱም ግልፅ ስለሆነ፣ በጦርነት እናሸንፋለን ብለው አምነው የጀመሩ አይመስለኝም" የሚል ግምት አላቸው።

ጦርነቱ በግልፅ የሚቃወሙት ፀሐፊዋ "በእርስ በእርስ ጦርነት መሸናነፍ የለም" ይላሉ።

የተሰቀለ ጠብመንጃ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ጦርነቱ ወዴት ሊያመራ ይችላል?

አብዱራህማን፤ ከዚህ በፊት እንደሆነው ህወሓት በወታደራዊ አቅም ሊሸነፍ ይችላል፤ ሆኖም የፌደራሉ መንግሥት ሕብረተሰቡ ውስጥ ያለውን አስተሳሰብ በቀላሉ ለማሸነፍ ሊከብደውና የግጭት ዑደቱ ሊቀጥል ይችላል ሲሉ ይገምታሉ።

"ህወሓት ድል ሊቀናው አይችልም ወይ? ብሎ መጠየቀ ተገቢ ነው። ነገር ግን ይህ ኢትዮጵያን ትልቅ አደጋ ላይ ሊጥል ስለሚችል በቀጠናው ያሉ አገራትም ሆነ አበይት መንግሥታት ይሄንን የሚፈቅዱ አይመስለኝም።"

ተንታኙ አክለው ግጭቱ በተራዘመ ቁጥር በሕዝቦች መካከል መቃቃር ሊፈጥር ይችላል የሚል ስጋት አላቸው።

"በዚህኛው ዙር [ጦርነት] በሁለቱ መካከል ግልፅ የሆነ ነገር ስለሌለ ምን ሊከሰት እንደሚችል ማወቅ ከባድ ነው" የሚሉት ራሔል መገናኛ ብዙኃን ጦርነቱን በግልፅ ስለማይዘግቡ ግራ አጋቢ እንደሆነ ይናገራሉ።

"አገራችን ላይ ምጣኔ ሃብታዊና ሰብዓዊ ቀውስ ከሚያመጡ፤ ካለ ምንም ቅደመ ሁኔታ ጦርነቱን አቁመው ውሳኔውን ለሕዝብ ቢተዉ የተሻለ ነው" ሲሉም አክለዋል።

በሌላ በኩል የደኅንነት ባለሙያው ጦርነቱ ለሳምንታት እንኳ ቢቀጥል ከኢትዮጵያ አልፎ ቀጠናውን የሚረብሽ ይሆናል ሲሉ ስጋታቸውን ይገልጻሉ።

"ይህ ጦርነት ኢትዮጵያን ይበትናታል ወይስ ይሰበስባታል የሚለው የማይታወቅበት አዲስ የጨለማ መድረክ ሊሆን ይችላል። አገሪቱ ካለችበት ሁኔታ አንጻር ደግሞ ሌሎች ተፋላሚ ኃይሎችም ሊፈጥር ይችላል።"

የባሕር በር የሌላት ኢትዮጵያ ከስድስት አገራት ጋር የምትዋሰን ሲሆን ከነዚህ መካከል ሦስቱ ማለትም ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን እና ሶማሊያ ግጭት እና ፖለቲካዊ አለመረጋጋት እያስተናገዱ ይገኛሉ።

የኤርትራ ወታደሮች ከኢትዮጵያ መንግሥት ጎን ተሰልፈው በትግራይ ጦርነት ተሳትፈዋል። ሆኖም የሁለቱ አገራት ግንኙነት አሁን ያለበት ደረጃ በውል አይታወቅም።

ከ120 ሚሊዮን በላይ የሕዝብ ቁጥር ያላት ኢትዮጵያ፣ የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ፀጥታና ደኅንነትን በማስረገጥ የምዕራባዊያን አገራት ወዳጅ ሆና ቆይታለች።

ጦርነቱ በተፋፋመበት ወቅት ለኢትዮጵያ ማንኛውም አይነት ድጋፍ አደርጋለሁ ስትል የነበረችው ቱርክ፣ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነቱ ዳግም ማገርሸቱን ተከትሎ በኢትዮጵያ ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን የትኛውም ዓይነት ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆንዋን ገልጣለች።

አንካራ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ጥቅም ላይ የዋሉ ዘመናዊ ‘ባይራክታር ቲቢ-2’ የተሰኙ ሰው አልባ አውሮፕላኖች ለኢትዮጵያ እንደሸጠች ቢነገርም የሁለቱም አገራት መንግሥታት በይፋ ያሉት ነገር የለም።

አሜሪካም እንዲሁ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ግንኙነት በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት ቢሻክርም አሁንም የገንዘብ ድጋፍ ከማድረግ አልተቆጠበችም።

አል-ሻባብ እንደ አዲስ በሶማሊያ እና ጎረቤት አገራት ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ሙከራ ማድረጉን ተከትሎ አሜሪካ በምሥራቅ አፍሪካ የኢትዮጵያን አጋርነት እንደምትሻ ተንታኞች ይገልጣሉ።

የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት እንደ አዲስ ማገርሸቱን ተከትሎ የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ኃላፊ አንተኒ ብሊንከን ሁለቱም ወገኖች ከግጭት እንዲቆጠቡ ጠይቀዋል።

የምጅራቅ አፍሪካ እና መካከለኛው ምሥራቅ ፖለቲካ ተንታኙ አብዱራህማን "አሜሪካም ሆነ አውሮፓ ከቀጠናው መረጋጋት ነው የሚጠቀሙት፤ በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ትላልቅ አገራት አደጋ ላይ መውደቅ እንደ ጅቡቲ እና ሶማልያ መውደቅ አይደለም፤ ጉዳቱ ከዚያ በላይ ነው" ይላሉ።

"ቻይናም ብትሆን በኢትዮጵያ ብዙ ኢንቨስትመንት ስላላት መረጋጋቱን ትፈልገዋለች። ቱርክም እንደዚያው። ስለዚህ ቀውሱን የሚደግፉት አይመለኝም" ሲሉ ሃሳባቸውን ያጠናክራሉ።

የሰላም ድርድር ተስፋ ይኖር ይሆን?

"የማይተማመኑ ጓደኛሞች በየወንዙ ይማማላሉ እንደሚባለው ነው የሆነው። ሁለቱም አስተሳሰባቸው አንድ ዓይነት ነው" ይላሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምክር ቤት ዋና ፀሐፊዋ ራሔል ባፌ (ዶ/ር)።

"ሰላም እንደሚፈልጉ፤ ድርድር እንደሚሹ ቢያንስ በወሬም ደረጃ ቢሆን ሲደመጥ ነበር። ግን ከልብ አለመሆኑን ነው ያየነው። እኛ ደግሞ ይህ ነገር እውነት ላይ ያልተመሠረተ ስለነበር ስጋቱ ነበረን። ቢሆንም ተስፋም ነበረን። አንድ አገር ናት ያለችን በሚል እሳቤ ብሔራዊ ምክክሩ እንዲካሄድ እንፈልግ ነበር። ነገር ግን ሁለቱም ይህንን ማድረግ አልቻሉም።"

ለአምስት ወራት ጋብ ብሎ የነበረው የኢትዮጵያ የእርስ በእርስ ጦርነት እንደገና መቀስቀሱ ያሳሰባቸው የአፍሪካ ኅብረት፣ የተባበሩት መንግሥታት፣ የአውሮፓ ኅብረት እና አሜሪካ ተፋላሚ ወገኖች ከግጭት እንዲታቀቡ ጥሪ እያቀረቡ ነው።

የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ፣ በመንግሥት እና በህወሓት መካከል የተጀመረው የሰላም ድርድር እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

ሐሳባቸውን ለቢቢሲ ያጋሩት የደኅንነት ባለሙያው ህወሓትና የፌዴራሉ መንግሥት ወደ ድርድር ይመጣሉ የሚል ተስፋ አላቸው።

ዋና ፀሐፊዋ ራሔል (ዶ/ር) ግን በዚህ ሃሳብ አይስማሙም። "ወደ ድርድር የመመለስ ልባዊ ፍላጎት አላቸው ብዬ አላስብም" ይላሉ።

"ድርድሩን ድጋሚ ቢጀምሩትም ችግራችንን አይፈታውም። እነሱ ድርድራቸው የአገር ጉዳይ ሳይሆን እንዴት በዚያም፣ በዚህም ብለን ሥልጣናችንን እናራዝም የሚል ነው። ውሳኔውን ለሕዝብ መተው ይኖርባቸዋል" ሲሉ ይመክራሉ።

"ሕዝቡ ድንበርን በተመለከት ይሁን አሊያም ሕገ-መንግሥቱን እንዲሁ አብሮ መኖርን በተለመከተ የራሱን ውሳኔ ያስተላልፍ። በሰው ሠራሽ የመጣውን ግጭትና አለመተማመን ለመፍታት ደግሞ ብሔራዊ ምክክር ይደረግ።"

የፖለቲካ ተንታኙ አብዱራህማን በበኩላቸው ከመጀመሪያው ወደ ድርድር ሲገቡ ነገሮች ግልፅ አልነበሩም ይላሉ።

"ትልቁ ችግር ህወሓት በትጥቅ ትግል የመጣ ስለሆነ፣ ግጭት በሰላማዊ መንገድ የሚፈታበት ሁኔታ ላይ ይፈተናል። ምክንያቱም በጦርነት ማሸነፍ ወይም መሸነፍ ስላለበት። ብልጽግና ደግሞ ውስጣዊ ድክመቶች ያሉት ፓርቲ ነው።"

ዋና ፀሐፊዋ በሰላም ድርድሩ ተስፋ የቆረጡ ቢመስሉም ጦርነቱ እያመጣ ያለውን ቀውስ ተከትሎ ግጭቱ መቆም አለበት ብለው ያምናሉ።

"የጦርነት የሚያስከትለው ኪሳራ ከምንም በላይ ነው። ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እያልን እናወራለን እንጂ ከዚያም በላይ ነው። ያለንን ንብረት በጦርነት እያወደሙ ልመና መውጣት እንደ አገር አሳፋሪ ነገር ነው" ይላሉ ራሔል (ዶ/ር)።