የጦርነቱ ማገርሸትና በግጭቱ አካባቢ ያሉ ነዋሪዎች ስጋት

የፎቶው ባለመብት, AFP
ለወራት ጋብ ብሎ የነበረው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ነሐሴ 18/2014 ዓ.ም. አገርሽቶ ወደ ከፋ ደም አፋሳሽ ግጭት እንዳይገባ ስጋት ፈጥሯል።
ግጭቱን በመጀመር አንደኛው ወገን ሌላኛውን እየከሰሰ ሲሆን፣ ዓለም አቀፍ ተቋማት እና መንግሥታት የፌደራል መንግሥቱ እና የህወሓት ኃይሎች ግጭቱን አቁመው ለድርድር እንዲቀመጡ ጥሪ እያቀረቡ ነው።
በሰሜን ኢትዮጵያ የትግራይ፣ የአማራ እና የአፋር ክልሎች በሚዋሰኑባቸው አካባቢዎች የተቀሰቀሰው ግጭት ሦስተኛ ቀኑን ይዟል።
እስካሁን ግን በአካባቢው ስላለው ጦርነት ከሁለቱም ወገን የሚወጣ መረጃ የለም።
ቢቢሲ እየተካሄደ ነው ስለሚባለው ግጭት ከሁለቱም ወገኖች መረጃ ለማግኘት ያደረገው ጥረት እስካሁን ምላሽ ማግኘት አልቻለም።
ዛሬ አርብ ማለዳ በአካባቢው የስልክ ግንኙነት መቆራረጥ የነበረ ቢሆንም፣ ረፋዱ ላይ ቤተሰቦቻቸውን ደውለው ማግኘት የቻሉ ግለሰቦች ለቢቢሲ እንደገለፁት፣ ከቆቦ ራቅ ባሉ ስፍራዎች ለሊቱን የከባድ መሳርያ ተኩስ ሲሰማ ነበር ብለዋል።
የከባድ መሳርያ ተኩስ የሚሰማባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ፣ ለቅቀው ለመውጣት የሞከሩ ቢሆንም የአካባቢው አስተዳደር ማኅበረሰቡን የማረጋጋት ሥራ መስራቱን ጨምረው ተናግረዋል።
እንዲሁም በራያ ቆቦ ወረዳ ሕዝቡ አካባቢውን ነቅቶ እንዲጠብቅ እየተነገረው መሆኑን ገልፀዋል።
ጦርነቱ ከተቀሰቀሰባቸው አቅራቢያ የሚገኙ ነዋሪዎችን እስከ ሐሙስ ነሐሴ 19/2014 ዓ.ም. ምሽት ድረስ ስላለው ሁኔታ አናግሮ ነበር።
የአማራ ክልል እና የትግራይ ክልል ከሚዋሰኑበት እንዲሁም በፌደራሉ እና በትግራይ ኃይሎች መካከል ግጭት እየተካሄደባቸው እንደሆነ ከሚነገሩት አካባቢዎች 20 ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኘው ቆቦ ከተማ ያሉ ነዋሪዎች ረቡዕ ጀምሮ የከባድ መሣሪያ ተኩስ ድምፅ እንሚሰማ ሐሙስ አመሻሽ ላይ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ነዋሪዎቹ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈቀዱ ሲሆን ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ በኋላ የሚሰማው የተኩስ ድምፅ ስጋት እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል።
አንዲት ነዋሪ “የከባድ መሣሪያ ተኩስ እየሰማን ነው። አሁንም ድረስ ተኩሱ አልተቋረጠም። ጦርነቱ ተባብሷል። ተጨማሪ ኃይልም ወደ አካባቢው እየገባ ነው” ስትል ያለውን ሁኔታ ለቢቢሲ ገልጻለች።
አንድ ሌላ ነዋሪ የከባድ መሣሪያ ተኩስ መሰማቱ እንደቀጠለና ይህም በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ግራ መጋባትን እንደፈጠረ ገልጿል።
አንዳንዶችም "በአቅራቢያ ወደሚገኝ ከተማ” መሄዳቸውን ለቢቢሲ ተናግሯል።
ሮይተርስ የዜና ወኪል ያናገረው አንድ በቆቦ ያለ አርሶ አደር ደግሞ “ከረቡዕ በበለጠ ሁኔታ ሐሙስ ዕለት የከባድ መሣሪያ ተኩስ በተደጋጋሚ ሁኔታ እየሰማን ነው” በማለት በርካታ የመከላከያ እና የአማራ ክልል ኃይል ወደ ጦርነቱ ስፍራ እየገባ መሆኑን ገልጿል።
ጦርነቱ በሰሜን አማራ ክልል ውስጥ በሚገኘው አዋሳኝ የቆቦ ወረዳዎች ውስጥ የሚካሄድ ሲሆን፣ እንዲሁም በአፋር ክልል ያሉ ወረዳዎች ውስጥ የከባድ መሣሪያ ተኩስ ድምጽ እንደሚሰማ ነዋሪዎች ገልጸዋል።
ባለፉት ስድስት ወራት ጦርነቱ ጋብ ብሎ በቆየበት ጊዜ የትግራይ ኃይሎችና መንግሥት ድርድር ለማድረግ ፈቃደኛ መሆናቸውን አሳውቀው በዝግጅት ላይ እንዳሉ ነው ጦርነቱ ያገረሸው።
ዛሬ አርብ ነሐሴ 20/2014 ዓ.ም. ሦስተኛ ቀኑን የያዘውን ጦርነት በመቀስቀስ አንደኛው ወገን ሌላኛውን እየከሰሰ ሲሆን፣ ባለፉት ሁለት ቀናት ስላለው ሁኔታ የትኛውም ወገን መግለጫ አልሰጠም።
ረቡዕ ዕለት ጥቃት ተከፈተብኝ በማለት በትግራይ ቴሌቪዥን ያሳወቁት የትግራይ ኃይሎች፤ የአማራ ሚሊሻ፣ ፋኖ እና የአገር መከላከያ ሠራዊት ጥምር ኃይል በትግራይ ደቡብ አቅጣጫ መጠነ ሰፊ ጥቃት ጀምረዋል ብሎ ነበር።
ህወሓት ለጦርነት ሲዘጋጅና ከሰላም ድርድሩ ለመራቅ ሰበብ ሲፈልግ ቆይቶ ነበር ያለው መንግሥት ደግሞ፣ ረቡዕ ማለዳ ላይ ጥቃት ፈጽሟል ሲል ከሷል።
በአማራ እና በአፋር ክልል በኩል ጦርነቱ መጀመሩን ተከትሎ በአዋሳኝ አካባቢዎች ያሉ ነዋሪዎች ከዚህ ቀደም የተከሰተው ዓይነት ጦርነት ሊከሰት ይችላል የሚል ስጋት እንደተፈጠረባቸው ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ለወራት በተካሄደው ጦርነት ሳቢያ በሰሜን ኢትዮጵያ በተለይም በትግራይ ከባድ የሰብአዊ ቀውስ መከሰቱ ይታወቃል።
ጦርነቱ የእርዳታ አቅርቦትን በማስተጓጎሉ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በረሃብ አደጋ አፋፍ ላይ መቆየታቸው ሲነገር ቆይቶ፣ ሰብአዊ የተኩስ አቁም ከተደረገ በኋላ እርዳታ መቅረብ ጀምሮ ነበር።
ነገር ግን መልሶ የተጀመረው ጦርነት የእርዳታ አቅርቦቱን ሊያስተጓጉለውና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ረድኤት ጠባቂዎችን ለአደጋ ሊያጋልጥ እንደሚችል ሰግተዋል።
ምንም እንኳን በአሸማጋዮች በኩል በቅርቡ ይጀመራል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረው ድርድር እውን ከመሆኑ በፊት ጦርነቱ ቢጀመርም፣ አሁንም ሁለቱም ወገኖች ወደ ውይይት ለመመለስ ፍላጎት እንዳላቸው እየገለጹ ነው።












