መንግሥት ትግራይ የሚገባው ዕርዳታ ለታለመለት ዓላማ ስለመዋሉ ማስተማመኛ ጠየቀ

ባለፉት በርካታ ወራት የዓለም ምግብ ፕሮግራም ነዳጅን ጨምሮ መሠረታዊ ቁሶችን ወደ ትግራይ ሲያጓጉዝ ቆይቷል።

የፎቶው ባለመብት, WFP

የምስሉ መግለጫ, ባለፉት በርካታ ወራት የዓለም ምግብ ፕሮግራም ነዳጅን ጨምሮ መሠረታዊ ቁሶችን ወደ ትግራይ ሲያጓጉዝ ቆይቷል።

የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አማካይነት ወደ ትግራይ ክልል የሚገባው ሰብዓዊ ዕርዳታ ለታለመለት ዓላማ እየዋለ ስለመሆኑ ማስተማመኛ እንዲሰጠው ጠየቀ።

መንግሥት ይህን ያለው የትግራይ ኃይሎች የዓለም ምግብ ፕሮግራም ንብረት የሆነ ከግማሽ ሚሊዮን ሊትር በላይ ነዳጅ ዘርፈዋል ከተባለ በኋላ ነው።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ዛሬ ሐሙስ ነሐሴ 19/2014 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳለው፣ የትግራይ ኃይሎች በመቀለ የነበረውን የዓለም ምግብ ድርጅት 570 ሺህ ሊትር ነዳጅ ላይ “የፈጸሙትን ዝርፊያ” መንግሥት በጽኑ ያወግዛል ብሏል።

ምንም እንኳ እስካሁን የትግራይ ኃይሎች ተዘርፏል ስለተባለው ነዳጅ ያሉት ነገር ባይኖርም፤ ከግምሽ ሚሊዮን ሊትር በላይ የሆነው ነዳጅ ከመንግሥታቱ ድርጅት መጋዘን በህወሓት ስለመወሰዱ የዓለም ምግብ ፕሮግራም አረጋግጧል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ቃል አቀፈባይ ስቴፋን ዱጃሪክም ትግራይ ኃይሎች ወደ ዓለም ምግብ ፕሮግራም መጋዘን ጥሰው በመገባት 570,000 ሊትር ነዳጅ የጫኑ 12 ቦቴዎች መዘረፋቸው ገልጸዋል።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ዴቪድ ቢዝሊ በይፋዊ የትዊተር ገጻቸው ላይ የዓለም የምግብ ፕሮግራም ለእርዳታ ሥራው የሚያውለውን 570,000 ሊትር ነዳጅ “የትግራይ ባለሥልጣናት ሰርቀዋል” ብለዋል።

ዲቪድ ቢዝሊ ነዳጁ በኃይል መወሰዱን “አስደንጋጭ እና አሳፋሪ” በማለት የገለጹት ሲሆን ነዳጁ “አሁኑኑ” ይመለስ ሲሉ በአጽንኦት ጠይቀዋል።

የ X ይዘትን ይለፉት
ይዘቱን X ይፈቅዳሉ?

ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።

ማሳሰቢያ: በሌሎች ገጾች ላይ ላሉ ይዘቶች ቢቢሲ ኃላፊነት አይወስድም።

የ X ይዘት መጨረሻ

ያለ ነዳጅ መሠረታዊ ቁሶችን ማከፋፈል አይቻልም

የህወሓት ኃይሎች ነዳጁን በኃይል መውሰዳቸውን ተከትሎ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ነሐሴ 19/2014 ዓ.ም. ከሰዓት ላይ ባወጣው መግለጫ ያለ ነዳጅ እንደ ምግብ፣ ማደበሪያ፣ መድኃኒት እና ሌሎች መሠረታዊ ቁሳቁሶችን በትግራይ ማከፋፈል አይቻለኝም ብሏል።

ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት በትግራይ የምግብ እርዳታ ጠባቂ የሆኑ 5.2 ሚሊዮን ሕዝብ መኖሩን አስታውሶ፤ የነዳጁ መዘረፍ በሚሊዮን የሚቆየሩት ሰዎችን ለከፋ ረሃብ የሚያጋልጥ ነው ብሏል።

ነሐሴ 18/2014 ንጋት ላይ ታጣቂዎች መቀለ ውስጥ ወደሚገኘው የዓለም ምግብ ፕሮግራም ቅጥር ግቢ ከገቡ በኋላ በኃይል ከግማሽ ሚሊዮን ሊትር በላይ ነዳጅ መወሰዳቸውን በመግለጫው ተመልክቷል።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም ዳግም ነዳጁ በአስቸኳይ ተመላሽ እንዲሆንለትም ጠይቋል።

“ዝርፊያው የጦር ወንጀል ነው”

የፌደራሉ መንግሥት የትግራይ ኃይሎች ለሰብዓዊ ተግባር ተብሎ ትግራይ የገባውን ነዳጅ መዝረፋቸው “ግልጽ የጦር ወንጀል እና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ሕግጋቶችን የጣሰ ደርጊት ነው” ብሎታል።

የትግራይ ኃይሎች ነዳጁን መውሰድ ያስፈለጋቸው በቆቦና በአካባቢው ላይ ለተከፈተው ጥቃት ማስፈጸሚያ ለማዋል ነው ያለ ሲሆን፤ ረቡዕ የተፈጸመው ዝርፊያ ቡድኑ በእርዳታ የሚገባ ነዳጅ እና የምግብ ድጋፍ ለጦርነት ዓላማ ሲጠቀም የመቆየቱን ሃቅ ለመላው ዓለም በግልጽ ያሳየ ነው ብሏል።

“. . . ቡድኑ ከፈጸመው ዝርፊያ ባሻገር ድርጊቱን ለማስቆም የሞከሩ የሰብዓዊ እርዳታ ባለሙያዎችንም አስሯል።” ብሏል።

በዚህ የፌደራሉ መንግሥት የተዘረፈው ነዳጅ እንዲመለስ፣ በትግራይ ኃይሎች ላይ ተጠያቂነት እንዲሰፍን እና ትግራይ የሚገባው ዕርዳታ ለታለመለት ዓላማ መዋሉን ማስተማማኛ እንዲሰጠው ጠይቋል።

ሰብአዊ ዕርዳታ

በህወሓት ኃይሎችና በኢትዮጵያ መንግሥት ሠራዊት መካከል ትግራይ ውስጥ ተቀስቅሶ ሁለት ዓመት ሊሞላው የተቃረበው ጦርነት ወደ አማራና አፋር ክልሎች ተስፋፍቶ ከባድ ሰብአዊ ቀውስ አስከትሏል።

በርካታ ሺዎች በጦርነቱ ምክንያት ሳይሞቱ እንዳልቀሩ ሲገመት፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ በረሃብ አፋፍ ላይ መሆናቸውና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ደግሞ ለመፈናቀልና ለችግር መዳረጋቸውን የተባበሩት መንግሥታት አመልክቷል።

የጦርነቱ ጋብ ማለትን ተከትሎ ባለፈው መጋቢት ወር ላይ መንግሥት የሰብአዊ ዕርዳታ አቅርቦት የተኩስ አቁም ማወጁን ተከትሎ፣ ህወሓትም ተኩስ ለማቆም በመስማማቱ አልፎ አልፎ ከሚያጋጥሙ ግጭቶች ባሻገር ለወራት ጦርነት ቆሞ ነበር።

በዚህም ዓለም አቀፍ ተቋማት የዕርዳታ አቅርቦቶችን ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ በተለይም ወደ ትግራይ ለማስገባት ተከታታይ ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል።

የጦርነቱ ማዕከል በሆነችው ትግራይ ውስጥ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የሰብአዊ ዕርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው የረድኤት ድርጅቶች የሚናገሩ ሲሆን፣ ከጦርነቱ መባባስ በኋላ ተቋርጦ የነበረው አቅርቦት ከወራት በፊት መልሶ ተጀምሮ ነበር።

ረቡዕ ነሐሴ 18/2014 ዓ.ም. መልሶ ባገረሸው ግጭት ሳቢያ ወደ ትግራይ ሲደረግ የነበረው የዕርዳታ አቅርቦት ሊቋረጥ ይችላል የሚል ስጋት ተፈጥሯል።

ድጋሚ የተቀሰቀሰውን ጦርነት ሁለቱም ወገኖች አንዳቸውን ሌላኛውን ጥቃት በመሰንዘር እየተካሰሱ ሲሆን፣ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ግጭቱ በአስቸኳይ ቆሞ ድርድር እንዲጀምር ጥሪ እያቀረቡ ነው።