የኬንያ አየር መንገድ ‘ኢትዮጵያ ገንዘቤን ትክፈለኝ’ ሲል ጠየቀ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከፍተኛ ኪሳራ ላይ የሚገኘው የኬንያ አየር መንገድ ለኢትዮጵያ መንግሥት የክፍያ ጥያቄን አቀረበ።
ክፍያው የኬንያ አየር መንገድ በኢትዮጵያ ለሰጣቸው አገልግሎትና ሽያጮች ገንዘብ ከብር ወደ ዶላር ተቀይሮ መሰጠት የነበረበት ነው።
አየር መንገዱ ተመሳሳይ ጥያቄን ለናይጄሪያ መንግሥትም አቅርቧል።
በአሠራር ደረጃ አየር መንገዶች አገልግሎታቸውን በውጭ አገራት ሲሸጡ በአገሬው ገንዘብ ከተገበያዩ በኋላ ገንዘባቸው የሚሰጣቸው በዶላር ነው።
የኬንያ አየር መንገድ በሁለቱ አገራት የሚገኘውን ገንዘቡን ማግኘት ያልቻለው በውጭ ምንዛሬ እጥረት እንደሆነ ይታመናል።
የኬንያ ባለሥልጣናት ለኬንያ አየር መንገድ የሚገባውን ክፍያ እንዲሰጡ የኢትዯጵያንና የናይጄሪያን ባለሥልጣናት በማነጋገር ላይ እንደሆኑ ተዘግቧል።
ገንዘቡ በአየር መንገዶችና በአገሮች መካከል የገቢ ክፍያ ልውውጥ በጊዜ ባለመካሄዱ የተከሰተ ችግር ነው።
የኬንያ አየር መንገድ ሁለቱ መንግሥታት ሊከፍሉት ይገባ የነበረ በሚሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ ሊያገኝ ያልቻለው ግን በዋናነት በውጭ ምንዛሬ እጥረት ምክንያት ነው።
የኬንያ አየር መንገድ በአውሮፕላን ነዳጅ ዋጋ ማሻቀብ የተነሳ፣ እንዲሁም በሌጎስና አዲስ አበባ ባጋጠመ የውጭ ምንዛሬ እጦት ገንዘቡ ስላልተከፈለው ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ 82 ሚሊዮን ዶላር ከስሬያለሁ ብሏል።
ሆኖም የኬንያ ባለሥልጣናት አየር መንገዱ ከሁለቱ አገሮች ምን ያህል ገንዘብ ማስመለስ እንዳልቻለ ትክክለኛ አሐዝ ከመግለጽ ተቆጥበዋል።
የአገሪቱ ባለሥልጣናት አሁን ይህን ለኬንያ አየር መንገድ የሚገባውን ገንዘብ ከአዲስ አበባና ከሌጎስ ለማግኘት ዲፕሎማሲን አማራጭ አድርገዋል።
በተያያዘ ዜና የዓለም አቀፉ አየር ትራንስፖርት ማኅበር ይፋ እንዳደረገው ለተለያዩ አየር መንገዶች መከፈል የነበረበት ግማሽ ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ በናይጄሪያ ቀርቷል።
የዱባዩ ኢምሬትስ ግሩፕ በተመሳሳይ በናይጄሪያ የሚገኘው ገንዘቤን ማግኘት አልቻልኩም በሚል ወደዚያ የሚያደርጋቸውን በረራዎች ማቋረጡ ይታወሳል።
ይህም የዶላር እጥረት በአቪየሽን ኢንዱስትሪው የፈጠረው ሌላ ችግር ሆኖ ተመዝግቧል።
የውጭ አየር መንገዶች አገልግሎታቸውን መሸጥ ያለባቸው በአገሬው የመገበያያ ገንዘብ ነው።
ይሁንና ገንዘባቸውን የሚወስዱት ግን ወደ አሜሪካን ዶላር ከተቀየረ በኋላ ነው።
መደበኛ አሠራሩ ይህ ይሁን እንጂ በርካታ አገሮች በውጭ ምንዛሬ እጥረት በመቸገራቸው ዕዳቸውን በዶላር ለመክፈል እየተንገታጉ ይገኛሉ።
በአፍሪካ የሕዝብ ቁጥር ቀዳሚ የሆነችው ናይጄሪያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በገጠማት የውጭ ምንዛሬ እጥረት ግዙፍ የውጭ ኩባንያዎች ላቀረቡት ምርትና አገልግሎት በሚከፈላቸው ዶላር መጠን ላይ ገደብ ለመጣል ተገዳለች።












