የሰብአዊ ተኩስ አቁም ስምምነትን ያፈረሰው ጦርነት

 በጦርነቱ የተፈናቀለች ግለሰብ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በኢትዮጵያ መንግሥትና በትግራይ ኃይሎች መካከከል ለወራት ጋብ ብሎ የነበረው የእርስ በእርስ ጦርነት እንደገና ተቀስቅሶ ለአምስት ወራት የቆየውን የሰብአዊ ተኩስ አቁም ስምምነት አፍርሷል።

በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ያለቁበትና ሚሊዮኖችን የመሠረታዊ አቅርቦት ጥገኛ የሆኑበት ደም አፋሳሽ ጦርነት እንዲገታና ዕርዳታ ወደ ትግራይ ክልል እንዲገባም ነው በሁለቱ አካላት መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት የተደረሰው።

ነገር ግን ከትናንት በስቲያ ጦርነቱ እንደገና የተቀሰቀሰ ሲሆን፣ በአቅራቢያው ባለ ከተማ የሚኖሩ ነዋሪዎች የከባድ መሣሪያ ተኩስ እንደሰሙና የመከላከያ ሠራዊት አባላት ሲደርሱ ማየታቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ለጦርነቱ መቀስቀስ ሁለቱም ወገኖች አንዳቸው ሌላኛውን በመግለጫቸው ተጠያቂ አድርገዋል።

ረቡዕ ጥዋት የትግራይ አመራር አማካሪ የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ፣ በአጎራባች አማራ ክልል ለሳምንት ከዘለቀ ትንኮሳ በኋላ የኢትዮጵያ ጦር በትግራይ ላይ ጦርነት ከፍቷል ብለዋል።

በኋላም የኢትዮጵያ መንግሥት፣ የትግራይ ኃይሎች የተኩስ አቁሙን ስምምነት እንዳፈረሱ እና የፌደራል እና የፀጥታ ኃይሎች ለተቃጣው ጥቃት በተሳካ ሁኔታ ምላሽ እየሰጡ ነው ብሏል።

በተጨማሪም የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ለትግራይ ጦር መሣሪያ የጫነ አውሮፕላን ተኩሰው መጣላቻውን የገለጹ ሲሆን፣ አቶ ጌታቸው ግን ሐሰት ነው ብለው አጣጥለውታል።

የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ የጦርነቱ መቀስቀስ እንዳስደነገጣቸው ገልጸው፣ ጦርነቱ በአስቸኳይ እንዲቆም ጠይቀዋል።

ጦርነቱ ሪፖርት ከተደረገባቸው አካባቢዎች 25 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ቆቦ ነዋሪ የሆኑ ግለሰብ ከማክሰኞ ምሽት ጀምሮ የተኩስ ድምጽ መስማታቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"ከሌሊቱ 5 ሰዓት አካባቢ ከሁለቱም ወገኖች የተኩስ እሩምታ እየጨመረ እና ከባድ የጦር መሣሪያዎች ሲተኮሱ እየሰማን ነበር" ብለዋል።

የትግራይ ጦርነት ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር ተቀስቅሶ በኋላም ወደ አጎራባቾቹ አማራ እና አፋር ክልሎች ተዛምቷል።

በዚህ ደም አፋሳሽ ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሞተዋል፣ ሁለት ሚሊዮን ሰዎች ቤት ንብረታቸውን ለቀው ከመሰደድ በተጨማሪ በክልሉ መሠረተ ልማት እና መሠረታዊ አገልግሎቶች ተቋርጠው ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ መንግሥት በክልሉ ላይ እገዳ በመጣል ለወሳኝ እርዳታ አቅርቦት እንቅፋት ሆኗል ተብሎ ቢወነጀልም መንግሥት በበኩሉ የትግራይ ኃይሎችን ተጠያቂ አድርጓል።

ሆኖም ከአምስት ወራት በፊት የተደረሰው የሰብአዊ ተኩስ አቁም ወደ ትግራይ የሚገባውን እርዳታ መንገድ ከማመቻቸት በተጨማሪ ጦርነቱን ጋብ በማድረግና በሰላም ይቋጫል የሚል ተስፋም ሰጥቶ ነበር።

በአሁኑ ወቅት ጦርነት እንደገና መቀስቀሱ የረድዔት ድርጅቶች እርዳታ የሚሹ ሰዎችን ለመድረስ እንቅፋት እንደሚሆንባቸውና የፖለቲካ ድርድሮችንም ወደኋላ ሊመልስ ይችላል የሚል ስጋት ፈጥሯል።