ኢትዮጵያ በዓለም ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር እድገት ከሚያሳዩ አገራት መካከል ተካተተች

በርካታ ሰዎች ተሰባስበው የሚታዩበት ቦታ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በመጪው 30 ዓመታት የዓለምን ግማሽ የሕዝብ ቁጥር ይይዛሉ ያላቸውን ስምንት አገራት ይፋ ያደረገ ሲሆን ኢትዮጵያ፣ ግብፅ፣ ኮንጎ፣ ናይጄሪያ እና ታንዛኒያ ከአፍሪካ አገራት በዝርዝሩ ውስጥ ተካተዋል።

እንዲሁም በሚቀጥለው ዓመት ቻይናን በመብለጥ በዓለም ብዙ ሕዝብ የሚኖርባት አገር የምትሆነው ሕንድ እንዲሁም ፓኪስታን ከስምንቱ አገራት መካከል ናቸው።

ሕንድ 1.4 ቢሊዮን ሕዝብ በመያዝ ነው በሕዝብ ብዛቷ ለዓመታት የዓለም ቁንጮ ሆና የቆየችውን ቻይናን የምትበልጠው።

በቀጣይ ዓመት ኅዳር ወር ውስጥም የዓለም ሕዝብ ቁጥር 8 ቢሊዮን የሚደርስ ቢሆንም፣ የዓለም የሕዝብ ቁጥር እድገት ቁጥር እስከ ዛሬ ከነበረው የእድገት መጠን ያነሰ እንደሆነም የመንግሥታቱ ድርጅት ይፋ አድርጓል።

በስልሳ ዓመታት ውስጥም ዝቅተኛ የተባለው የሕዝብ ቁጥር እድገት መመዝገቡን ይፋ ያደረገው የተባበሩት መንግሥታት፣ ከ40 ዓመታት በኋላ በድጋሚ ከፍተኛ እድገት ላይ ሊደርስ እንደሚችል እና ቁጥሩም 10.4 ቢሊዮን እንደሚደርስ ትንበያው ያሳያል።

እ.ኤ.አ. በ2050፣ 61 አገራት የሕዝብ ቁጥራቸው ቢያንስ በአንድ በመቶ መቀነስ ያሳያል ተብሎ ይገመታል። በአሁኑ ወቅትም በተወሰኑ ታዳጊ አገራት ውስጥ እድገቱ በአንድ ሴት 2.1 በመቶ አካባቢ ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ ይህ ምጣኔ ያለውን የሕብ ብዛት ቁጥር የመተካት እንጂ እድገት እንዳልሆነ ተመድ አስታውቋል።

ቻይና 1.15 ልጅ በአንድ ሴት በማስመዝገብ በዓለም ዝቅተኛ የሕዝብ ቁጥር እድገት ካስመዘገቡ አገራት መካከል ስትሆን፣ ከመጪው ዓመት ጀምሮ ደግሞ የሕዝብ ቁጥሯ መቀነስ እንደሚጀምር አስታውቃለች።

ቻይና ጥንዶች ከአንድ ልጅ በላይ መውለድ እንዳይችሉ የሚከለክለውን ሕጓን በማንሳት ብሎም ሁለት እና ከዚያ በላይ ለሚወልዱ ዜጎቿ ማበረታቻዎችን መስጠት ብትጀምርም እድገቱን ከመቀነስ አላስቆመውም።

ምንም እንኳን አንድ ሴት የምትወልደው ልጅ ቁጥር ቢቀንስም የሕዝብ ቁጥር እድገት በተለይም ከሕክምና ሳይንስ መሻሻል ጋር ተያይዞ የሚሞቱ ሕጻናት ቁጥር በመቀነስ፣ እንዲያድጉ በማስቻሉ ምክንያት እድገቱ ቀጥሏል።