አወዛጋቢው የሶማሊያ ወታደሮች ጉዳይ በኤርትራ

የኤርትራ እና የሶማሊያ ፕሬዝደንት

የፎቶው ባለመብት, @hawelti

ላለፉት ሁለት ዓመታት በሶማሊያ ፖለቲካ ውስጥ አወዛጋቢ ሆኖ የቆየው ወደ ኤርትራ ተልከዋል የተባሉት በሺዎች የሚቆጠሩ ሶማሊያውያን ወታደሮች ጉዳይ ወደ መቋጫው የተቃረበ ይመስላል።

ከቅዳሜ ጀምሮ ለአራት ቀናት በኤርትራ ጉብኝት በማድረግ ላይ ያሉት አዲሱ የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐመድ በተገኙበት መመረቃቸው የተነገረው ወታደሮች፣ የት እና በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ ሳይነገር ከቆዩ በኋላ ነው።

የኤርትራ መንግሥት እሁድ ሐምሌ 03/2014 ዓ.ም. እንዳስታወቀው ለሦስት ዓመታት ወታደራዊ ሥልጠና ሲወስዱ የነበሩት የሶማሊያ ወታደሮች፣ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐመድ በተገኙበት ተመርቀዋል።

ይህ የሶማሊያ ወታደሮች ጉዳይ በተለይ ባለፈው ዓመት ኤርትራ የተሳተፈችበት ጦርነት ሰሜን ኢትዮጵያ መቀስቀሱን ተከትሎ፣ ሶማሊያ ውስጥ በፖለቲከኞችና በምልምል ወታሮቹ ቤተሰቦች መካከል ከባድ ውዝግብ አስከትሎ ነበር።

ቀድሞው ፕሬዝዳንት ፋርማጆ ተቀናቃኞች ወታደሮቹን ወዳልታወቀ ስፍራ ልከው በጦርነት ውስጥ ማግደዋቸዋል በሚል ሲወቅሷቸው፣ ይህንን ተከትሎ ቤተሰቦች ደግሞ ስለልጆቻቸው ሁኔታ በመጠየቅ መንግሥትን አስጨንቀው ነበር።

እነዚህ ሶማሊያውያን ወታደሮች ከዓመታት በፊት በምስጢር ተመልምለው ይፋ ወዳልተደረገ ቦታ ሲላኩ የተለያዩ መላ ምቶች ሲዘዋወሩ መቆየቱ ውዝግቡን የበለጠ አጠንክሮታል።

ትግራይ ውስጥ የተካሄደውን ጦርነት ተከትሎ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና የትግራይ ኃይሎች የሶማሊያ ወታደሮች በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ከፌደራል መንግሥቱ ጎን ተሰልፈው ተዋግተዋል ማለታቸው ደግሞ ሌላ ጥያቄን ፈጥሮ ቆይቷል።

ነገር ግን ይህን የሶማሊያ ወታደሮች በኤርትራ ውስጥ ስለመገኘትም ሆነ በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ውስጥ መሳተፋቸውን በተመለከተ የሞቃዲሾ መንግሥት አንዳንዴ ዝምታን ሲመርጥ ሌላ ጊዜ ደግሞ ሲያስተባብል ቆይቷል።

ነገር ግን ባለፈው ግንቦት ወር በተደረገው ምርጫ የተሸንፉት ሞሐመድ አብዱላሂ ፋርማጆ ሥልጣናቸውን ሲያስረክቡ፤ አምስት ሺህ የአገራቸው ወታደሮች ኤርትራ ውስጥ ሥልጠና እየወሰዱ እንደሚገኙ ለተተኪው ፕሬዝዳንት አረጋግጠዋል።

ሶማሊያውያን ወታደሮች በኤርትራ

የፎቶው ባለመብት, @hawelti

የምስሉ መግለጫ, ሶማሊያውያን ወታደሮች በኤርትራ

ወታደሮቹን በተመለከተ ማን ምን ብሎ ነበር?

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ከአንድ ዓመት በፊት ባወጣው ሪፖርት በኤርትራ የሰለጠኑ የሶማሊያ ወታደሮች ከፌደራሉ መንግሥት ጎን በመሰለፍ በትግራይ ጦርነት ተሳትፈዋል ብሎ ነበር።

የተመድ የሰብዓዊ ምክር ቤት በኤርትራ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ላይ ባተኮረው ሰነዱ ላይ በሥልጠና ላይ የነበሩ የሶማሊያ ወታደሮች፣ ወደ ትግራይ ጦር ግንባሮች መወሰዳቸውንና በአክሱም ከተማ እንደነበሩ የሚገልጹ መረጃዎች እንዳገኘ ገልጾ ነበር።

አብዲሰላም ጉሌድ የተባሉ የሶማሊያ ብሔራዊ የደኅንነትና መረጃ ተቋም የቀድሞ ምክትል ኃላፊ ኤርትራ ውስጥ ወታደራዊ ስልጠናቸውን ያጠናቀቁ በመቶዎች የሚቆጠሩ የሶማሊያ ወታደሮች ኢትዮጵያ ውስጥ በተካሄደው ጦርነት ውስጥ መሳተፋቸውንና በርካቶች መገደላቸውን ገልጸው ነበር።

ነገር ግን በወቅቱ የሶማሊያው የማስታወቂያ ሚኒስትር የነበሩት ኦስማን አቡከር ዱቤ የተባለውን ውድቅ በማድረግ የሶማሊያ ኃይሎች በቅርቡ በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ውስጥ በተካሄደው ውጊያ ላይ አልተሳተፉም ብለዋል።

ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ጦርነት ውስጥ የገቡት የትግራይ ኃይሎችም የጎረቤት አገር ሶማሊያ ወታደሮች በኤርትራ በኩል ወደ ትግራይ ዘልቀው በመግባት ከኤርትራ ጦር ጋር ሆነው እየወጉኝ ነው ብሎ ከሶ ነበር።

ሆኖም የሶማሊያ ወታደሮች በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ውስጥ ተሳትፈዋል የሚለውን ሪፖርት ሞቃዲሾ በተደጋጋሚ ወድቅ ስታደርግ ቆይታለች።

የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስተዳደርም የሶማሊያ ወታደሮች በትግራዩ ጦርነት ውስጥ ተሳትፈዋል የሚለውን ክስ ማስተባበሉንም በወቅቱ ብሉምበርግ ዘግቧል።

የሶማሊያ ወታደሮች ምርቃት

አዲሱ የሶማሊያ ፕሬዝደንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ ወደ ኤርትራ ካቀኑ በኋላ ትናንት ሐምሌ 03/2014 ዓ.ም. ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የወታደሮች የምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ መገኘታቸውን የሚያሳዩ ምስሎች እንዲሁም ዘገባዎች በኤርትራ መገናኛ ብዙኃን በኩል ተጋርተዋል።

የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገ/መስቀል በትዊተር ገጻቸው ላይ ከተመራቂዎቹ የሶማሊያ ወታደሮች መካከል ለሦስት ዓመታት ሥልጠና ሲወስዱ የነበሩ እንደሚገኙበት አመልክተዋል።

በትናንቱ ሥነ-ሥርዓት ላይ ምን ያህል የሶማሊያ ወታደሮች ሥልጠናቸውን እንዳጠናቀቁ፣ ምን አይነት ሥልጠናዎችን እንደወሰዱ፣ ሶማሊያውያኑ ወደ ኤርትራ መቼ እንደገቡም ሆነ መቼ ወደ ትውልድ አገራቸው እንደሚመለሱ የተገለጸ ነገር የለም።

የቀድሞው ፕሬዝዳንት ሞሐመድ አብዱላሂ ፋርማጆ ሥልጣን ባስረከቡበት ጊዜ፣ ለሥልጠና ወደ ኤርትራ ስለተላኩት 5 ሺህ ወታደሮች እንደተናገሩት፣ ሶማሊያውያኑ ወደ አገራቸው ሳይመለሱ የቆዩት ሊከሰት የሚችልን ፖለቲካዊ ቀውስ ለመከላከል ነው ሲሉ ተናግረው ነበር።

ፋርማጆ ጨምረውም አዲሱ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐመድ ወደ ሥልጣን መምጣትን ተከትሎ በኤርትራ ያሉት የሶማሊያ ወታደሮች "ወደ አገራቸው ተመልሰው ከሠራዊቱ ጋር በመቀላቀል እስላማዊውን ታጣቂ ቡድን አልሻባብን በመዋጋቱ ዘመቻ ላይ ይሳተፋሉ" ማለታቸው ተዘግቧል።

የ X ይዘትን ይለፉት
ይዘቱን X ይፈቅዳሉ?

ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።

ማሳሰቢያ: በሌሎች ገጾች ላይ ላሉ ይዘቶች ቢቢሲ ኃላፊነት አይወስድም።

የ X ይዘት መጨረሻ

“ልጆቻችን የት ናቸው?”

ሶማሊያውያን ወታደሮች በትግራይ ጦርነት ተሳትፈዋል የሚል ሪፖርት በስፋት መውጣቱን ተከትሎ ወላጆቻቸው "ልጆቻችንን የት ናቸው? ልጆቻችንን አምጡ" በሚል በሞቃዲሾ እና በሌሎች ከተሞች የተቃውሞ ሰልፎች ማካሄዳቸው በስፋት ተዘግቦ ነበር።

ወታደሮቹ በእአአ 2019 ላይ ወደ ኤርትራ የተላኩ መሆናቸውን ሪፖርቶች ያመላከቱ ሲሆን፣ ወታደሮቹ ሶማሊያን ለቀው ከመውጣታቸው በፊት ኳታር ለምታዘጋጀው የዓለም ዋንጫ በጥበቃነት እንደሚሰሩ ተነግሯቸው ነበር ተብሏል።

ሮይተርስ የዜና ወኪል ያነጋገራቸው አሊ ጂማክ ዱዲ የተባሉ አባት፤ ልጃቸው ከአገር የወጣው ኳታር ለምታስተናግደው የዓለም ዋንጫ በጥበቃ ሠራተኝነት ለመቀጠር በተነገረው መረጃ መሰረት እንደሆነ በወቅቱ አስረድተዋል።

እኚህ አባት፤ ልጃቸው በኤርትራ እንደሞተ መረዳታቸውን ተናግረዋል። በርካታ ወላጆችም ልጆቻቸው የት እንዳሉ እንደማያውቁ ለሮይተርስ ተናግረዋል።

በወቅቱ የኳታር የመንግሥት ጉዳዩን በተመለከተ ባወጣው መግለጫ "ወደ ኳታር ለሥራ ዕድል የተባለው ሐሰተኛ ምልመላን እና የውሸት ብዝበዛን" እንደሚያወግዝ ገልጾ፣ ጉዳዩ ላይ ምርመራ እንዲደረግ ጠይቆ ነበር።

አሁን አዲሱ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐመድ ወደ ኤርትራ በማምራት በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮቻቸውን ሁኔታ ተመልክተው በምረቃቸው ላይ መሳተፋቸው ተዘግቧል።

በቀጣይ እነዚህ ወታደሮች ወደ አገራቸው የሚመለሱበትን ሁኔታ ከኤርትራ መንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ያመቻቻሉ ተብሎ ይጠበቃል።