የአፍሪካ ኅብረት ወታደሮች ጦር ሠፈራቸውን ለሶማሊያ መንግሥት አስረከቡ

የፎቶው ባለመብት, AFP
በሶማሊያ ያለው የአፍሪካ ሕብረት ተልዕኮ ኃይል በአገሪቱ ውስጥ ካሉት ወታደራዊ የጦር ሰፈሮች መካከል ሦስቱን ለሶማሊያ መንግሥት ሠራዊት አስረከበ።
ከተለያዩ አገራት የተወጣጣው የአፍሪካ ኅብረት ኃይል ቀስ በቀስ ሶማሊያን ለቆ ለመውጣት በያዘው ዕቅድ መሠረት በእጁ የሚገኙትን ጦር ሰፈሮች ለሶማሊያ መንግሥት እያስረከበ ሲሆን፣ ከዚህ በፊትም ሌሎችን አስረክቧል።
ለበርካታ ዓመታት የሶማሊያ መንግሥትን ለማጠናከር ተሰማርቶ የቆየው የኅብረቱ ሠራዊት በሚቀጥለው የአውሮፓውያን ዓመት ማብቂያ ላይ ሙሉ ለሙሉ ሶማሊያን ለመልቀቅ ዕቅድ ይዟል።
ባለንበት የሰኔ ወር ማብቂያ ላይ የአፍሪካ ኅብረት ሁለት ሺህ የሚሆኑ ወታደሮቹን ከሶማሊያ ለማስወጣት ዕቅድ ይዞ እየሠራ ነው።
ኅብረቱ ማክሰኞ ዕለት ለሶማሊያ ሠራዊት ያስረከባቸው የጦር ሠፈሮች ሚድል ሸበሌ በሚባለው የሶማሊያ ግዛት ውስጥ ባሉ አዳሌ፣ ሚርታቅዋ እና ሃጂ አሊ በተባሉ ቦታዎች የሚገኙ ናቸው።
የጦር ሠፈሮቹ በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ስር በሶማሊያ ውስጥ ተሰማርተው የቆዩት የቡሩንዲ ወታደሮች የሚገኙባቸው እንደነበሩ ተገልጿል።
በዚህ ዓመት አስካሁን ድረስ የአፍሪካ ኅብረት ስድስት የጦር ሠፈሮችን ለሶማሊያ መንግሥት ኃይሎች ያስረከበ ሲሆን፣ አምስቱ ሚድል ሸበሌ ውስጥ የሚገኙ ናቸው።
ባለፈው ጥር ወር ላይ ለሶማሊያ መንግሥት የተሰጠው የመጀመሪያው ጦር ሠፈር በዋና ከተማዋ ሞቃዲሾ ውስጥ ሄሊዋ በሚባለው አካባቢ የሚገኝ ነው። የጦር ሠፈሩ የቡሩንዲ ወታደሮች የሰፈሩበት ነበር።
የኅብረቱ ወታደሮች የጦር ሠፈራቸውን እያስረከቡ ቢሆንም አስካሁን ምን ያህል ወታደሮች ከሶማሊያ ለቀው እንደወጡ ግን የታወቀ ነገር የለም።
የአፍሪካ ኅብረት ወታደሮች አገሪቱን መልቀቅ የሚፈጥረውን ክፍተት ለመሙላት የሶማሊያ መንግሥት በኡጋንዳ፣ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ ውስጥ አዳዲስ ወታደሮችን ሲያሰለጥን ቆይቷል።
በአሁኑ ወቅት በሶማሊያ ውስጥ 19,000 የሚሆኑ የአፍሪካ ኅብረት ወታደሮች ተሰማርተው የሚገኙ ሲሆን፣ በቀጣይ አንድ ዓመት ውስጥ ይዞታቸውን ለሶማሊያ መንግሥት ወታደሮች አስረክበው ለመውጣት ዝግጅት እያደረጉ ነው።
ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ላይ ሥልጣን የያዙት ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐመድ በታጣቂው እስላማዊ ቡድን አል ሻብብ ላይ መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻ በመክፈት ውጤታማ መሆናቸው ይነገራል።
በርካታ በታጣቂው ቡድን ተይዘው የነበሩ ቦታዎችን መቆጣጠር የቻለው የሶማሊያ ሠራዊት እየተጠናከረ ሲሆን፣ በአል ሻባብ ላይ ሁለተኛውን ዙር ዋነኛ ወታደራዊ ዘመቻ ለመክፈት በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል።
ከአልቃኢዳ ጋር ግንኙነት እንዳለው የሚነገርለት አል ሻባብ፣ ባለፉት ሳምንታት በአፍሪካ ኅብረት ኃይሎች ጦር ሠፈር ላይ ጥቃት መፈጸሙ ይታወሳል።
ባለፈው ግንቦት ወር የኡጋንዳ ወታደሮች በሚገኙበት ጦር ሠፈር ላይ ታጣቂ ቡድኑ በፈጸመው ጥቃት በርካታ ወታደሮችን መግደሉ የተነገረ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ወታደሮች ጦር ሠፈር ላይ ጥቃት ለመፈጸም ያደረገው ሙከራ ከሽፎበታል።
የሶማሊያ መንግሥት መጠነ ሰፊ ጥቃት በቡድኑ ላይ ለማካሄድ እየተዘጋጀ ባለበት በአሁኑ ጊዜ፣ አል ሻባብም በመቶዎች የሚቆጠሩ አዲስ ተዋጊዎችን አሠልጥኖ ማስመረቁን የሚያሳይ ቪዲዮ አሰራጭቷል።
















