የምሥራቅ አፍሪካ መሪዎች አል-ሻባብ ላይ ስለሚያካሂዱት የጋራ ዘመቻ ሞቃዲሾ ውስጥ እየመከሩ ነው

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ ፕሬዝዳንት ጊሌ፣ ፕሬዝዳንት ሐሰን እና ፕሬዝዳንት ሩቶ

የፎቶው ባለመብት, @PMEthiopia

የምስሉ መግለጫ, ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ ፕሬዝዳንት ጊሌ፣ ፕሬዝዳንት ሐሰን እና ፕሬዝዳንት ሩቶ

የምሥራቅ አፍሪካ መሪዎች በእስላማዊው ታጣቂ ቡድኑ አል-ሻባብ ላይ ስለሚወስዱት የተቀናጀ ወታደራዊ ዘመቻ ለመነጋገር በሶማሊያ መዲና ሞቃዲሾ እየመከሩ ነው።

በውይይቱ ላይ ተሳታፊ ለመሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕምድ፣ የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ እና የጂቡቲው ፕሬዝዳንት ኢስማኤል ኦማር ጌሌ ሞቃዲሾ መግባታቸውን የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሞሐሙድ ጽ/ቤት አስታውቋል።

የአል-ቃይዳ አጋር መሆኑን በይፋ በሚገልጸውን ታጣቂ ቡድን ላይ የተቀናጀ ወታደራዊ እርምጃ ለመውሰድ በሚደረገው ውይይት፣ መሪዎቹ የሶማሊያ መንግሥት ሠራዊት እያካሄደ ያለውን ዘመቻ ለማቀናጀትና ለማጠናከር ይመክራሉ ተብሏል።

እስላማዊ ታጣቂ ቡድኑ ባለፉት በርካታ ዓመታት የሶማሊያን የፌደራል መንግሥት በመቃወም ጥቃት ሲፈፅም ቆይቷል።

የአገራት መሪዎቹ ስብሰባ የሚካሄደው የሶማሊያ መንግሥት ወታደሮች በአል-ሻባብ ላይ ወሳኝ የሆነ ውጤት ማግኘታቸውን ተከትሎ ነው።

አዲሱ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ባለፈው ዓመት ግንቦት ላይ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ሠራዊታቸውን በማቀናጀት በታጣቂ ቡድኑ ላይ በወሰዷቸው ተከታታይ እርምጃዎች ድል እየቀናቸው መሆኑ ይታወቃል።

ፕሬዝዳንት ሩቶ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ ፕሬዝዳንት ጊሌ እና ፕሬዝዳንት ሐሰን

የፎቶው ባለመብት, @PMEthiopia

የምስሉ መግለጫ, ፕሬዝዳንት ሩቶ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ ፕሬዝዳንት ጊሌ እና ፕሬዝዳንት ሐሰን
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ለሁለት ቀናት በሚቆየው የመሪዎች ስብሰባ አጀንዳዎች መካከል ከእንደ አውሮፓውያኑ ከ2007 ጀምሮ በሶማሊያ ተሰማርተው የቆዩ የአፍሪካ ኅብረት ወታደሮች መውጣት ላይ ትኩረቱን እንደሚያደርግ ተገልጿል።

በሶማሊያ አልሻባብን ለመመከት በአፍሪካ ኅብረት የተሰማራው አሚሶም የተባለው ወታደራዊ ኃይል ከአገሪቱ ለመውጣት የመውጫ ዕቅዱን እየተገበረ እንደሚገኝ ቀደም ሲል መገለጹ ይታወሳል።

ታጣቂ ቡድኑ ከዚህ ቀደም በሌሎች ጎረቤት አገራት ላይ ጥቃት የፈፀመ ሲሆን በኢትዮጵያ ላይ ጥቃት ለመፈፀም ሙከራ ማድረጉ ይታወሳል።

ባለፈው ሐምሌ ወር የእስላማዊ ቡድኑ ታጣቂዎች ለቁጥጥር አስቸጋሪ በሆነው እና በረጅሙ የሶማሊያ እና የኢትዮጵያ ድንበር በኩል ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ታጣቂዎቹን በማስገባት ጥቃት ሰንዝሮ ነበር።

የአገሪቱ መከላከያ ሠራዊት እና የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል ወደ ኢትዮጵያ ዘልቀው ከገቡ የአል-ሻባብ ታጣቂዎች ጋር ውጊያ አድርገው በርካታ የአል-ሻባብ ተዋጊዎች መገደላቸው በወቅቱ ተገልጿል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ሞሐመድ “በኢትዮጵያ ላይ የተፈፀመው ጥቃት ካለው ቀጠናዊ ሁኔታ ጋር ተያይዞ ዝግጅቶች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ያሳየ ነው” ብለው ነበር።

ጂቡቲ፣ ኢትዮጵያ እና ኬንያ የታጣቂ ቡድኑን ጥቃት ለማስቆም በሶማሊያ ለተሰማራው የአፍሪካ ኅብረት ሰላም አስከባሪ ኃይል ወታደር አዋጥተዋል።

ታጣቂ ቡድኑ አል-ሻባብ የመንግሥት ኃይሎች በአሜሪካ፣ በአፍሪካ አገራት ወታደሮች መደገፍ ከጀመሩ እንዲሁም የሶማሊያ የጎሳ ሚሊሻዎች ነሐሴ ወር ላይ ከመንግሥት ወታደሮች ጋር በመተባበር ጥቃት ከፈፀሙ በኋላ በርካታ ይዞታዎቹን አጥቷል።

ሆኖም ታጣቂ ቡድኑ በዋና መዲናዋ ሞቃዲሹ፣ በማዕከላዊ እና ደቡባዊ ሶማሊያ በሚገኙ ከተሞች ጥቃት መፈፀማቸውን ቀጥለዋል።

የመሪዎቹ በአል ሻባብ ላይ የጋራ ጥቃት በሚያካሂዱበት ጉዳይ ላይ ለመምከር ስብሰባቸውን በሚጀምሩበት በዛሬው ዕለትም ቡድኑ የሞርታር ጥቃት በሞቃዲሾ ላይ መሰንዘሩ ተዘግቧል።

በጥቃቱ አራት የሞርታር ቅምቡላዎች በከፍተኛ ጥበቃ ስር በሚገኘው የፕሬዝዳንቱ ቤተ መንግሥት አቅራቢያ የወደቁ ሲሆን፣ ጉዳት ስለመድረሳቸው የተባለ ነገር የለም።