የኢትዮጵያ ጦር ያለበት የአፍሪካ ኅብረት ኃይል ሲወጣ ሶማሊያ አልሻባብን መቆጣጠር ትችላለች?

የፎቶው ባለመብት, AFP
ለዓመታት በጽንፈኛው እስላማዊ ቡድን አልሻባብ የምትታመሰው ሶማሊያ ደኅንነቷን ለማረጋገጥ የጎረቤት አገራት ወታደራዊ ድጋፍ አስፈልጓት ቆይቷል።
በሶማሊያ የአፍሪካ ኅብረት ሰላም አስከባሪ ኃይል (አሚሶም) ባለፉት ዓመታት በአገሪቱ ውስጥ ተሰማርቶ ጥበቃ እና ወታደራዊ ዘመቻዎችን ሲያከናውን ነበር።
ይህ ግን አሁን ማብቂያው እየተቃረበ ነው።
ታኅሣሥ 2016 ዓ.ም. በኋላ የአፍሪካ ኅብረት ሰላም አስከባሪ ኃይል ከሶማሊያ ጠቅልሎ የሚወጣበት ጊዜ እንደሚሆን ተቆርጧል።
ከዚያ በፊት ግን የውጭ ኃይሎች የአገሪቱን የደኅንነት ጉዳዮች ለሶማሊያ ጦር እና የፀጥታ ኃይሎች ማስተላለፍ ይጠበቅባቸዋል።
በዚህ ሂደትም በቅርቡ አሚሶም መጠሪያውን ወደ 'የአፍሪካ ኅብረት የሽግግር ተልዕኮ በሶማሊያ' ወደሚል ስያሜ ቀይሯል።
ይህ ኃይል በአውሮፓውያኑ 2024 ከአገሪቱ ጠቅልሎ እንዲወጣ የአፍሪካ ኅብረት፣ የመንግሥታቱ ድርጅት እና የሶማሊያ መንግሥት ከስምምነት ደርሰዋል።
የሶማሊያ መንግሥት እና የተራጁ የጎሳ የሚሊሻ አባላት ባለፉት ጥቂት ወራት ከዓለም አቀፍ የሽብር ቡድኖች ጋር ትስስር እንዳለው በሚነገርለት አልሸባብ ላይ የተጠናከረ ወታደራዊ ዘመቻ ሲያካሂዱ ቆይተዋል።
ከባድ ወታደራዊ ዘመቻ የተከፈተበት አልሸባብ መሪዎቹን እና በርካታ ተዋጊዎቹን እንዲሁም በቁጥጥሩ ስር የነበሩ ሰፊ ግዛቶችን አጥቷል።
የሚጠቀሙበት መሳሪያ ይህንን ይዘት የሚያሳይ ላይሆን ይችላል
ከቀናት በፊት በሞቃዲሾ ተሰባስበው የነበሩት የጎረቤት አገራት መሪዎች በአልሸባብ ላይ የተከፈተውን ዘመቻ እንደሚደግፉ አረጋግጠዋል።
በሶማሊያ የአፍሪካ ኅብረት ሰላም አስከባሪ ኃይል (አሚሶም) ውስጥ ወታደሮቻቸውን እያሳተፉ የሚገኙት የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ እና የጂቡቲው አቻቸው ኢስማኤል ኦማር ጉሌህ እንዲሁም ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ የሶማሊያ መንግሥት የሚያደርገውን ዘመቻ መደገፋቸውን እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።
በሶማሊያ ተሰማርቶ የሚገኘው የአፍሪካ ኅብረት ሰላም አስከባሪ ኃይል በፀጥታ ጉዳይ የሶማሊያን መንግሥት ከመርዳቱ ባሻገር አልሸባብን በመዋጋት ቀጥተኛ ተሳትፎ አድርጓል።
ፀጥታ አስከባሪው እአአ 2007 ላይ ወደ ሶማሊያ የተሰማራው አጋርነቱን ለአልቃኢዳ በይፋ ያወጀው ቡድን የማዕከላዊ መንግሥቱ ህልውናን አደጋ ላይ ጥሎ በነበረበት ወቅት ነው።
ለዓመታትም ሰላም አስከባሪው ኃይል የሶማሊያን የፀጥታ ጉዳይ በበላይነት ሲመራ ቆይቷል።
ይህም በሶማሊያውያን ዘንድ አንድ ጥያቄ አስነስቶ ነበር "የሶማሊያ ፀጥታ ኃይል፣ ኃላፊነቱን ከውጭ ኃይሎች የሚረከበው መቼ ነው?" የሚል።
በሶማሊያ ጦር ውስጥ ከፍተኛ አዛዥ የነበሩት እና አሁን በሕይወት የሌሉት ጄኔራል አብዲቃዲር አሊ ዲሪዬ በአንድ ወቅት የአገሪቱ ጦር የደኅንነት ኃላፊነቱን ሳይረከብ የቆየው ያለው የሰላም እጦት ችግር እየተበላሸ በመሄዱ ነው ሲሉ ለቢቢሲ ሶማልኛ ተናግረው ነበር።
ጄኔራሉ አገሪቱን የሚያስተዳደረው መንግሥት ቀዳሚውን ኃላፊነት መወሰድ ቢኖርበትም የጎረቤት አገራት መሪዎችም ኃላፊነት አለባቸው ብለው ብለዋል በወቅቱ።
"በሶማሊያ መንግሥት አስተዳደር ስር መሆን የነበረባቸው ኃይሎች፣ ሌሎች ፍላጎቶች ባሏቸው የውጭ መንግሥታት ቁጥጥር ሥር ይገኛል" ሲሉ ለቢቢሲ ሶማልኛ ተናግረዋል።

እአአ 2017 ላይ ሰላም አስከባሪ ኃይሉ ሶማሊያ በገባ በ10ኛው ዓመት ላይ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት የሶማሊያ የፀጥታ አስተዳደር ወደ ሶማሊያ ብሔራዊ ጦር ይተላለፋል ብሎ ነበር።
ምንም እንኳ የሶማሊያ መንግሥት በአገር ውስጥ እና ከአገር ውጭ ወታደሮችን ቢያሰለጥንም፣ በፀጥታው ምክር ቤት ዕቅድ መሠረት ጦሩ ኃላፊነቱን መረከብ አልቻለም።
በቅርቡ መጠሪያውን ከአሚሶም ወደ የአፍሪካ ኅብረት የሽግግር ተልዕኮ በሶማሊያ ወደሚል ስያሜ የተቀየረበት አንዱ ዓላማም የሰላም አስከባሪ ኃይሉ ከሶማሊያ የሚወጣበትን ሂደት ለማዘጋጀት ነው።
የውጭ ኃይሎችን ከሶማሊያ የማስወጣት ሂደት አካል ከአንድ ወር በፊት በአገሪቱ የተሰማሩ የውጭ አገር ወታደሮችን ቁጥር ወደ 2ሺህ ዝቅ እንዲል ተደርጓል።
ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ላይ በምርጫ በድጋሚ ሶማሊያን ለመምራት የበቁት ሼክ ሐሰን፣ በአጭር ጊዜው ውስጥ ባካሄዷቸው ዘመቻዎች የአልሻባብ ቡድንን ለማዳከም ችለዋል።
በተጨማሪም የአሜሪካ የአየር ኃይል እና ልዩ ኃይሎች በአልሻባብ ታጣቂዎች እና መሪዎች ላይ በወሰዷቸው እርምጃዎች በርካቶችን ገድለዋል።
የሶማሊያ ብሔራዊ ጦር በአልሻባብ ላይ ድልን እየተቀዳጀ ባለበት በአሁኑ ወቅት፣ ጦሩ በሚያካሂዳቸው ዘመቻዎች ስኬታማ እንዲሆን የጎረቤት አገራት ኢትዮጵያ፣ ጂቡቲ እና ኬንያ እንዲሁም አሜሪካ ድጋፋቸውን እሰጡ ነው።

የፎቶው ባለመብት, AMISOM












