የፕሬዚዳንት ባይደን 'የዕድሜ እና የአዕምሮ ብቃት' ጥያቄ ያልተገባ እንደሆነ ፓርቲያቸው ገለጸ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከዕድሜያቸው እና ከአዕምሮ ብቃታቸው ጋር ተያይዞ ጥያቄ እየተነሳባቸው ያሉትን የ81 ዓመቱ ፕሬዚዳንት ባይደን ዲሞክራቶች እየተከላከሏቸው ነው።
ፕሬዚዳንቱ ጥያቄ የተነሳባቸው ምስጢራዊ ሰነዶች አያያዛቸውን በተመለከተ ጥያቄ የሚያጭሩ ሁኔታዎች በአንድ ሪፖርት ላይ በመካተቱ ነው።
ባይደን እነዚህን ምስጢራዊ ሰነዶችን በማስቀመጣቸው ክስ ባይመሰረትባቸውም ሪፖርቱ “ ጥሩ አሳቢ፣ የማስታወስ ችሎታቸው ደካማ የሆኑ አዛውንት” ሲል ነው ፕሬዚዳንቱን የገለጻቸው።
ይህንን ገለጻ የነቀፉት ምክትል ፕሬዚዳንት ካማላ ሐሪስ “ያልተገባ፣ የተሳሳተ እና ምክንያታዊነት የጎደለው ነው ” ብለውታል።
ምክትል ፕሬዚዳንቷ አክለውም አቃቤ ሕግ “በግልጽ ፖለቲካዊ ተነሳሽነት እንዳላቸው አሳይተዋል” ብለዋል።
በቀድሞው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የተሾሙት ሮበርት ሁር የፕሬዚዳንት ባይደንን ምስጢራዊ ሰነዶች አያያዝ ምርመራን እንዲመሩ የተመረጡት ባለፈው ዓመት ነበር።
መርማሪዎች ፕሬዝዳንቱን ለአምስት ሰዓታት የዘለቀ ጥያቄዎችን ከጠየቋቸው በኋላ ባይደን ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው ያገለገሉባቸውን ዓመታት፤ እንዲሁም ልጃቸው ቦ በካንሰር ሕይወቱ ያለፈበትን ዓመት ማስታወስ ተስኗቸዋል ብለዋል።
የአሜሪካ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ሜሪክ ጋርላንድ ሮበርት ሁርን በመረጡበትም ወቅት ትራምፕ ከፍተኛ ምስጢር ያዘሉ ሰነዶችን አላግባብ ይዘዋል በሚል የፍትህ ቢሮ ልዩ አማካሪ መሾሙ ከሪፐብሊካኖች ዘንድ ከፍተኛ ትችትን አስተናግዷል።
ሮበርት ሁር በይፋ ባወጡት ሪፖርት ላይ ዋይት ሐውስ የፕሬዚዳንቱን የማስታወስ ችሎታን በተመለከተ የተጠቀሰው ነገር እንዲከለስ የጠየቀበትን ደብዳቤም አያይዘዋል።
በዚህም ደብዳቤ መሰረት ሮበርት ሁር ሁኔታውን “ዕውቀታቸው በሚፈቅድላቸው መልኩ” እንዲያዩትም ይጠይቃል።
ከዚህ ቀደም አቃቤ ሕግ ሆነው ያገለገሉት ምክትል ፕሬዚዳንቷ ካማላ ሐሪስ አርብ ዕለት በነበረ መግለጫ ላይ ይህንን ትችት አስተጋብተዋል።
“በሪፖርቱ ውስጥ የፕሬዚዳንቱ ባህርይ የተገለጸበት መንገድ በእውነታ ላይ ያልተመሰረተ፣ የተሳሳተ እና በግልጽም ፖለቲካዊ ተነሳሽነትን ያዘለ ነው” ሲሉም ተደምጠዋል።
“እንዲህ ባለ ሁኔታ ውስጥ የአቃቤ ሕግ ሚና እና ኃላፊነትን በተመለከተ ከፍተኛ የታማኝነት ደረጃ ይኖራል ብለን ጠብቀን ነበር” ብለዋል።
ዲሞክራቶቹ ሁር የሰጡት አስተያየት ከምርመራው ወሰን የዘለለ ነው ብለው እንደሚያምኑም ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የሚኒሶታዋ ተወካይ ቲና ስሚዝ የሮበርት ሁርን አስተያየት “አስጸያፊ” እና “የወረደ” ብለው የጠሩት ሲሆን በግልጽ ጉዳዩን ፖለቲካዊ አድርገዋል ሲሉም ከሰዋቸዋል።
ድጋሜ ለመመረጥ ቅስቀሳ እያደረጉ ያሉት ፕሬዚዳንት ባይደን ከዕድሜያቸው እና ከአዕምሮ አቅማቸው ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች እየተነሱባቸው ይገኛሉ።
ባይደን 81 ዓመታቸው ሲሆን በአሁኑ ወቅት የሪፐብሊካን ቀዳሚ እጩ የሆኑት ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ 77 ዓመታቸው ነው። ሪፖርቱ የመራጮችን ስጋት ለማርገብ ሚናውን አልተወጣም ተብሏል። አርብ ዕለት ቢቢሲ ያነጋገራቸው ዲሞክራቶች የፕሬዚዳንቱ የማስታወስ ችሎታ የማያሳስብ እንደሆነም ገልጸዋል።












