ፕሬዝዳንት ባይደን ለቀረበባቸው ትችት “የማስታወስ ችሎታዬ ምንም አልሆነም” ሲሉ መለሱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የማስታወስ ችሎታቸው ‘በጉልህ’ ቀንሷል መባሉን ተከትሎ በብስጭት “የማስታወስ ችሎታዬ ምንም አልሆነም” ሲሉ መለሱ።
ባይደን ከዓመታት በፊት ምክትል ፕሬዝዳንት ሳሉ ከወታደራዊ እና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ጋር የተያያዙ ምስጢራዊ ሠነዶች አያያዛቸውን በተመለከተ የወጣ የምርመራ ሪፖርት ላይ የ81 ዓመቱ ፕሬዝዳንት ቁልፍ የሚባሉ ቀናትን ዘንግተዋል ብሏል።
የፍትሕ ቢሮ አማካሪ የሆኑት ሮበርት ሁር ፕሬዝዳንቱን ለአምስት ሰዓታት የዘለቀ ጥያቄዎችን ከጠየቋቸው በኋላ ባይደን ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው ያገለገሉባቸውን ዓመታት፤ እንዲሁም ልጃቸው ሕይወቱ ያለፈበትን ዓመት ማስታወስ ተስኗቸዋል ብለዋል።
መርማሪው ይህን ካሉ በኋላ ባይደን ብስጩ ሆነው ለጋዜጠኞች ሲናገሩ፤ “የማስታወስ ችሎታዬ ደህና ነው” ካሉ በኋላ ልጃቸው ሕይወቱ ያለፈበትን ቀን አያስታውሱም መባላቸው “በምን ድፍረቱ ነው ስለዚህ ጉዳይ የሚያወራው” ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ በመርማሪው የግል ሕይወታቸውን የተመለከቱ ጥያቄዎችን ሲጠየቁ፤ “ምን አግብቶት ነው ይህን የሚጠይቀኝ እያልኩ እራሴን ስጠይቅ ነበር” ካሉ በኋላ “ልጄ ሕይወቱ ያለፈበትን ጊዜ ማንም እንዲያስታውሰኝ አልፈልግም” ብለዋል።
የፕሬዝዳንቱ የመጀመሪያ ልጅ የሆነው ቢዩ ባይደን በ45 ዓመቱ እአአ 2015 በጭንቅላት ካንሰር ሕይወቱ አልፏል።
ባለ 345 ገጹ ሪፖርት ፕሬዝዳንቱ የምስጢራዊ ሠነድ አያያዛቸው ከሕግ አግባብ ውጪ ቢሆንም ክስ ግን አያስመሰርትባቸውም ተብሏል።
ጆ ባይደን አምስት ሰዓታት የሚረዝመው ቃለ መጠይቅ የተደረገላቸው ሐማስ በእስራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቃት ከሰነዘረ በኋላ ባሉት ሁለት ተከታታይ ቀናት መሆኑን አስታውሰው “ትኩረቴ በሙሉ በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ነበረ” ብለዋል።
ባይደን ሕዳር 2017 ዓ.ም. በሚደረገው ምርጫ ዴሞክራቶችን ወክለው እንደሚወዳደሩ ይፋ ከሆነ በኋላ የፕሬዝዳንቱን ዕድሜ የተመለከቱ ጥያቄዎች ሲነሱ ቆይተዋል።
ፕሬዝዳንቱ ግን ትንናት ሐሙስ ምሽት ላይ ለሪፖርተሮች መግለጫ ሲሰጡ አገሪቱን ለሁለተኛ ዙር ለመምራት አቅሙ አለኝ ብለዋል።
“የምሰራውን አውቃለሁ። በዕድሜ የገፋሁ አዛውንት ነኝ፤ ነገር ግን የማደርገውን አውቃለሁ። ይህን አገር መልሼ በሁለት እግሩ እንዲቆም አደርጊያለሁ። የእርሱ ምክር አያስፈልገኝም” ብለዋል።
ባይደን የፍትሕ ቢሮ አማካሪ በሆኑት ሮበርት ሁር ምርመራ የተደገባቸው ምስጢራዊ ሰነዶች ዴልዌር በሚገኘው መኖሪያ ቤት መገኘታቸውን ተከትሎ ነው።
ባይደን ሠነዶቹ በቤታቸው የተገኙት በአንድ ሠራተኛ ምክንያት መሆኑን ተናግረው ሠነዶቹ በመኖሪያ ቤታቸው እንደነበሩ እንደማያውቁ ተናግረዋል።












