ፍልስጤምን የሚደግፉ የአሜሪካ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ያነሱት የረሃብ አድማ ሳምንት አለፈው

የፎቶው ባለመብት, Sabine Jimenez Williams
በአሜሪካ የሚገኘው ብራውን ዩኒቨርስቲ ፍልስጤምን የሚደግፉ ተማሪዎች ያነሱት የረሃብ አድማ ስምንተኛውን ቀን ያዘ።
እስራኤል በወረራ ከያዘቻቸው የፍልስጤም ግዛቶች ላይ ዩኒቨርስቲው ተጠቃሚ ሆኗል በሚልም ነው ተማሪዎቹ ተቃውሟቸውን ለማሰማት የረሃብ አድማ የመቱት።
እስራኤል በጋዛ ላይ የምታደርገውን ጭፍጨፋ እያገዙ ነው ካሏቸው ኩባንያዎችም ጋር የንግድ ሽርክናውን ዩኒቨርስቲው እንዲያቆም ጫና ለማድረግ የረሃብ አድማ እያደረጉ መሆኑንም ገልጸዋል።
በረሃብ አድማው 19 ተማሪዎች ተሳታፊ ሆነዋል።
የብራውን ዩኒቨርስቲ ባለስልጣናት እስራኤልን ይደግፋሉ ካሏቸው ኩባንያዎች ጋር ያላቸውን የንግድ ሽርክና ወይም ኢንቨስት ማድረግ እስኪያስቡበት ድረስ እንደሚቀጥሉም ገልጸዋል።
የእስራኤል- የጋዛ ጦርነት ከጀመረ ወዲህ በአሜሪካ ውስጥ ረጅሙ የረሃብ አድማ ሳይሆን እንዳልቀረም ተነግሯል።
በሮድ አይላንድ በሚገኘው በዚህ ስመ ጥር ዩኒቨርስቲ የተነሳው የረሃብ አድማ የፍልስጤም ድጋፍ ካውከስ እና የተኩስ አቁም እንዲካሄድ በሚጠይቁ አይሁዳውያን ተማሪዎች የተዘጋጀ ነው።
እስራኤል በከበባ ውስጥ ባስገባቻት ጋዛ ውስጥ የጀመረችውን የተቀናጀ ጥቃት ተከትሎ ከ27 ሺህ 900 በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን ከጋዛ የጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያስረዳል።
በተጨማሪም ቢያንስ 67 ሺህ ፍልስጤማውያን መቁሰላቸውንም በሐማስ አስተዳደር ስር ያለው የጤና ሚኒስቴር ገልጿል።
ሐማስ መስከረም መጨረሻ ላይ በደቡብ እስራኤል በፈጸመው ጥቃት 1 ሺህ 200 ሰዎች መገደላቸውን የእስራኤል ባለስልጣናት ማስታወቃቸው ይታወሳል።
የ22 ዓመቷ ተማሪ ሮዝንዝዌይግ እንደተናገረችው በዩኒቨርስቲው ውስጥ ደቡብ አፍሪካ ከጨቋኙ አፓርታይድ ለመላቀቅ የምታደርገው ትግልን ለመደገፍ ተመሳሳይ የ11 ቀን የረሃብ አድማ በአውሮፓውያኑ 1986 መደረጉን አስታውሳለች። የረሃብ አድማውም የአፓርታይድ ስርዓትን ከሚደግፉ ኩባንያዎች ጋር ያሉ የንግድ ሽርክናዎች እንዲቆሙ የሚጠይቅ ነበር።
“የረሃብ አድማችን ተማሪዎች የሚደራጁበት እና ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ የትግል መስመር አድርጌ ነው የማየው” ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች። 61 ተማሪዎች የታሰሩበትን የኅዳር ወር በቤት ውስጥ መቀመጥን ጨምሮ በዩኒቨርስቲው ለወራት የቆየ ተቃውሞ እየተካሄደ ይገኛል።
“የእኛን ድምጽ ብቻ ሳይሆን በጋዛ የተገደሉትን በሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውንን ድምጽ እንዲሰማ ዩኒቨርስቲውን እየለመንን ነው” ብላለች።
ተማሪዎቹ ምንም ምግብ ያልተመገቡ ሲሆን ለስምንት ቀናትም ውሃ እና ፔዲያላይት የተሰኘ ንጥረ ነገሮችን የያዘ ውሃ መሳይ ፈሳሽ ብቻ ወስደዋል።












