የእስራኤል ደህንነት ማስፈራሪያዎች እየሰነዘሩባቸው እንደሆነ የደቡብ አፍሪካዋ ሚኒስትር ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
እስራኤል በጋዛ በፍልስጤማውያን ላይ የዘር ፍጅት መፈጸሟ ሊቆም ይገባል በሚል ጉዳዪን ወደ አለም አቀፉ የፍትህ ፍርድ ሸንጎ የወሰደችው ደቡብ አፍሪካ ሚኒስትሯ ከእስራኤል ደህንነት ማስፈራሪያዎች እየተሰነዘሩባቸው እንደሆነ ተናገሩ።
ይህንን የተናገሩት ደቡብ አፍሪካን በዓለም አቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት ከወከሉት መካከል አንዷ የሆኑት የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ናሌዲ ፓንዶር ናቸው።
ሚኒስትሯ ናሌዲ ሐሙስ ዕለት ለሜይል እና ጋርዲያን ከተሰኘው ድረ ገጽ ጋር ባደረጉት ቆይታ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ኢላማ መደረጋቸውን ገልጸው የቤተሰቦቻቸው ደህንነትም አሳስቦኛል ብለዋል።
የማስፈራሪያዎች እና ዛቻዎች መልዕክቶች ከደረሷቸውም በኋላ በደህንነታቸው ጉዳይ ላይ ከፖሊስ ሚኒስትር ብሄኪ ሴሌ ጋር ውይይት ማድረጋቸውንም ገልጸዋል።
“የእስራኤል ወኪሎች፣ የእስራኤል የስለላ አገልግሎት ባህሪያቸው ነው። ማስፈራራት ስራቸው ነው። መቼም ቢሆንም መፍራት የለብንም። የምንታገልለት ምክንያት አለን” ሲሉም አስረድተዋል።
እስራኤል በሚኒስትሯ አስተያየት ላይ እስካሁን ምንም አስተያየት አልሰጠችም።
ደቡብ አፍሪካ ጉዳዩን ወደ አለም አቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት መውሰዷንም ተከትሎ እስራኤል በጋዛ በሚኖሩ ፍልስጥኤማውያን ላይ የሚደርሰውን የዘር ማጥፋት ለመከላከል እርምጃ እንድትወስድ ውሳኔ ተላልፏል።
እስራኤል በአንድ ወር ጊዜ ውስጥም ሪፖርት እንድታቀርብም ፍርድ ቤቱ መመሪያም ሰጥቷል።
ደቡብ አፍሪካ እስራኤል በጋዛ ፍልስጤማውያን ላይ የዘር ፍጅት እየፈጸመች ነው ስትልም ነው ጉዳዩን ወደ አለም አቀፉ የፍትሕ ፍርድ ቤት የመራችው።
84 ገጾችን የያዘው ዶሴ እስራኤል በጋዛ የፈጸመችው ድርጊት በባሕሪው የዘር ማጥፋት ወንጀል ነው ይላል።
ምክንያቱም ዓላማ አድርጎ የተነሳው ቀላል የማይባሉ በጋዛ የሚገኙ ፍልስጤሞችን ማውደም ነበር።
እንደ ክሱ ከሆነ የዘር ማጥፋት ድርጊት ያስባለው ፍልስጤሞችን መጨፍጨፍ፣ የአእምሮ ቀውስ መፍጠር፣ አካላቸውን ማጉደል እና ሆን ብሎ ማንነታቸውን ማጥፋት ዓላማ አድርጎ በመነሳቱ ነው።
ሚኒስትሯ አገራቸው የፍርድ ሂደቱን አጥብቆም እንደሚከታተተለውም ነው አጽንኦት የሰጡት።












