የዓለም አቀፉ የፍትሕ ፍርድ ሸንጎ ምንድነው? እስራኤል ላይ ምን መዘዝ ይዞ ይመጣል?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአውሮፓውያኑ ሐሙስ ጥር 11 እና 12 ደቡብ አፍሪካ እስራኤልን ፍርድ ቤት ታቆማታለች።
ሁለቱን አገራት የሚወክሉት ጠበቆች ሸንጎ ፊት ይቀርባሉ።
እስራኤል የዘር ፍጅት በጋዛ በፍልስጤሞች ላይ ፈጽማለች?
እንደ ደቡብ አፍሪካ ከሆነ አዎን ፈጽማለች።
ኔዘርላንድስ ሄግ የሚገኘው ሸንጎ ደቡብ አፍሪካ ክስ የመሠረተችው ታኅሣሥ 29 ነበር።
ኔታንያሁ በዚህ ጦርነት እስራኤል ያሳየችውን ሐዘኔታና የሞራል ልእልና የትም ታይቶ የማይታወቅ ሲሉ አሞካሽተውታል።
ደቡብ አፍሪካ ግን እስራኤል የዘር ፍጅት ነው የፈጸመችው ትላለች።
የደቡብ አፍሪካ ክስ ምን ይዟል?
84 ገጾችን የያዘው ዶሴ እስራኤል በጋዛ የፈጸመችው ድርጊት በባሕሪው የዘር ማጥፋት ወንጀል ነው ይላል።
ምክንያቱም ዓላማ አድርጎ የተነሳው ቀላል የማይባሉ በጋዛ የሚገኙ ፍልስጤሞችን ማውደም ነበር።
እንደ ክሱ ከሆነ የዘር ማጥፋት ድርጊት ያስባለው ፍልስጤሞችን መጨፍጨፍ፣ የአእምሮ ቀውስ መፍጠር፣ አካላቸውን ማጉደል እና ሆን ብሎ ማንነታቸውን ማጥፋት ዓላማ አድርጎ በመነሳቱ ነው።
ጁሊየት የተባሉ በደቡብ አውስትራሊያ የሕግ መምህርት፤ ደቡብ አፍሪካ ያቀረበችው የክስ ዝርዝር “በጣም የተሟላ’’ እና “በጥንቃቄ የተሰናዳ” ሲሉ አሞካሽተውታል።
ይህም በመሆኑ ይላሉ የሕግ አዋቂዋ ጁሊየት፣ “እስራኤል ለእያንዳንዱ ክስ በአጥጋቢ ሆኔታ ምላሽ መስጠት ይጠበቅባታል።”
የእስራኤል ምላሽ ምንድነው?
የእስራኤል መንግሥት ቃል አቀባይ ኤይሎን ሌቪ እስራኤል ይህን ክስ ትከላከላለች ብለዋል። ሌቪ እንደሚሉት ለዚህ ሁሉ ተጠያቂው ሐማስ ነው።
የዘር ማጥፋት ወንጀል (genocide) ምንድነው?
የ1948 የተባበሩት መንግሥታት የዘር ማጥፋት ስምምነት ድርጊቱን ሲበይነው አንድን ሕዝብ፣ ወይም ዘር ወይም ብሔር ወይም ቡድን በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ የማውደም ሙከራ ይለዋል።
ይህም
· የቡድኑን አባላት በመግደል
· የአካልና የአእምሮ ጉዳት በቡድኑ አባላት ላይ በማድረስ
· ኑሮን መሠረታዊ በሆነ ሁኔታ ማመሳቀል
· እንዳይዋለዱ በሚያደርግ ሁኔታ እክል መፍጠርን
· በግዳጅ ልጆቻቸውን ወደ ሌላ ቡድን ማዘዋወርን ሊያጠቃልል ይችላል።
የዘር ማጥፋት ወንጀል ከብዙ ዓለም አቀፍ ወንጀሎች ተከራክሮ መፈጸሙን ለማረጋገጥ ከባዱ ነው ይላሉ የሕግ አዋቂዎች።
በዘር ማጥፋት ሊከሰስ የሚችለው ማን ነው? - ግለሰብ ወይም አገር በዘር ማጥፋት ወንጀል ሊከሰስ ይችላል።

የፎቶው ባለመብት, EPA
የዓለም አቀፉ የፍትሕ ሸንጎ ሚና ምንድነው?
ይህ ሸንጎ የተባበሩት መንግሥታት ትልቁ የፍርድ ሸንጎ ነው። አገሮች ክስ መስርተው የሚረታቱበት ፍርድ ቤት ሲሆን ሁሉም የተባበረቱን መንግሥታት አባል አገራት የዚህ የፍትሕ ሸንጎ አባላት ናቸው።
አንድ አገር በዚህ ሸንጎ ክስ ሊመሠርት ይችላል። የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤና የጸጥታው ምክር ቤት 15 ዳኞችን ለዚህ ሸንጎ ይመርጣል። ዳኞቹ ለ9 ዓመታት ያገለግላሉ።
በሁለተኛው የዓለም ጦርነት 6 ሚሊዮን አይሁዳዊያን በናዚ ተጨፍጭፈዋል። ከዚያ ወዲያ ነው የዓለም መሪዎች ይህን ድርጊት እንዳይደገም ይህን ኮንቬንሽን ያሰናዱት።
እስራኤል፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ሚየንማር፣ ሩሲያ እና አሜሪካ ይህን ስምምነት ከፈረሙ ከ153 አገሮች መካከል ናቸው።
ፍርድ ቤቱ የሚሰማው ክርክር ምን ይሆናል?
ደቡብ አፍሪካ ሸንጎው ጊዜያዊ እርምጃ እንዲወስድ ትፈልጋለች። ፍርድ ቤቱ እስራኤል በጋዛ እየወሰደች ያለችውን ወታደራዊ እርምጃ እንዲያስቆም ትጠይቃለች።
ይህ ጥያቄዋ ነው መጀመርያ የሚሰማውና ቅድሚያ የሚሰጠው።
ዩክሬን በተመሳሳይ በሩሲያ ስትወረር በዚህ ሸንጎ ተመሳሳይ ጥያቄ አቅርባ ነበር። ሸንጎው የዩክሬንን ጥያቄ ተቀብሎ ሩሲያ ጥቃት እንድታቆም ጠይቆ ነበር። ሩሲያ ቸል ብላዋለች።
ጋዛ አሁን 13 በከፊል እየሠሩ ያሉ ሆስፒታሎች ብቻ ነው ያሏት። 21 የሚሆኑት ሥራ አቁመዋል። ይህም ጉዳዩን የሚያጠናክር ሊሆን ይችላል።
የሸንጎው ፍርድ በያዝነው የፈረንጆች ወር መጨረሻ ይጠበቃል።
በሸንጎው የሚሰጠው ዉሳኔ በእስራኤል ላይ ጫና ይፈጥራል ይላሉ የሕግ ባለሙያዎች። ይሁን እንጂ ሸንጎው ተፈጻሚነቱን የማስገደድ አቅም የለውም። ዉሳኔውም የመጨረሻ የሚባል አይሆንም።
ዩክሬን ባስገባችው ማመልከቻ ሸንጎው የዘር ማጥፋት ምልክቶችን አለማግኘቱን ነበር የገለጸው።
ሚስተር ቤከር የተባሉ የሕግ አዋቂ ይህ ሸንጎ እስራኤል ወታደራዊ ጥቃቱን እንድታቆም ሸንጎው ይወስናል ብለው አይጠብቁም።
ይልቅ ወታደራዊ ጥቃቱን የተመጠነ እንድታደርግ ሊጠይቅ ይችል ይሆናል።
የዓለም አቀፉ ወንጀል ፍርድ ቤት (ICC) ከሸንጎው በምን ይለያል?
የዓለም አቀፉ ወንጀል ፍርድ ቤት በፈረንጆቹ 2002 ነው የተመሠረተው። ይህ ፍርድ ቤትም እንደ ዓለም አቀፉ ሸንጎ መቀመጫው ሄግ ኔዘርላንድስ ነው።
አሜሪካ፣ ሩሲያ እና እስራኤል አባል አይደሉም።
ይህ ፍርድ ቤት ዓለም አቀፍ የጦር ወንጀሎችን ነው የሚመለከተው። አቃቢ ሕግ ግለሰቦችን በጦር ወንጀል ሊከስ ይገባል።
እነማን ተከሰው ያውቃሉ?
በዚህ ፍርድ ቤት ለመከሰስ ቀዳሚው የሩዋንዳው ሁቱ ተወላጅ ጂን ፖል አካየሱ ሲሆን ይህም በፈረንጆቹ 1998 ነበር። ክሱ በ1994ቱ የረዋንዳ የዘር ፍጅት 800 ሺህ ሰዎች ግድያን የተመለከተ ነበር።
ከዚያ በኋላ በ2017 የቀድሞው የዩጎዝላቪያን የቦስኒያ ሰርብ ኮማንደር የነበረውን ራትኮ ምላዲክ ለ8 ሺህ ሙስሊሞች ሞት ተጠያቂ አደረገ።
ይሁንና ፍርድ ቤቱ ቦስኒያ ያቀረበችውን ክስ አልተቀበለም። ክሱ ሰርቢያ ወይም የቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ በቀጥታ በሰርበርኒካ ላይ የዘር ፍጅት ፈጽማለች የሚል ነበር።
ይልቅ ፍርድ ቤቱ ሰርቢያ ጥፋቷ የዘር ፍጅቱን ማስቆም አለመቻሏና ፈጻሚ ጄኔራሎችን አሳልፎ አለመስጠቷ ነበር ሲል ወስኗል።
ሚስተር ቤሪክ እንደሚሉት ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት የዘር ማጥፋት ወንጀል ተፈጽሟል ብሎ ለማሳመን ሂደቱና ማስረጃው ቀላል አይደለም።
ዉሳኔው የሚጠበቀው መቼ ነው? ውሳኔው ዓመታትን ሊወስድ ይችላል።
ዓለም አቀፉ ሸንጎ እስራኤል የዘር ፍጅት ፈጽማለች ወደፊት በዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት አይሲሲ ክስ ሲመሰረት እንደ ማስረጃ ሊቀርብ ይችላል።
ክሱ በሸንጎው ተቀባይነት ካገኘ የእስራኤል አጋር አገራት ከቴልአቪቭ ጋር የሚኖራቸውን ግንኙነት እንዲፈትሹ ሊያደርጋቸውም ይችላል።
ይሁንና አሜሪካ ከወዲሁ ክሱን አጣጥላዋለች። የብሔራዊ ደኅንነት ካውንስል ቃል አቀባይ ጆን ከርቢ የደቡብ አፍሪካን ክስ “ፍሬ የሌለው” ሲሉ ተችተውታል።












