ፍልስጤማውያን በጋዛ መቆየት መቻል አለባቸው ሲሉ ብሊንከን ተናገሩ

አንቶኒ ብሊንከን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ፍልስጤማውያን ጋዛን ለቀው እንዲወጡ ጫና ሊደረግባቸው እንደማይገባ እና ሁኔታዎች በፈቀዱ ጊዜ ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ ሊፈቀድላቸው ይገባል ሲሉ የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ተናገሩ።

አንዳንድ የእስራኤል ሚኒስትሮች ፍልስጤማውያን ወደ ሌላ ቦታ እንዲሰፍሩ የሰጡትን መግለጫ ብሊንከን አውግዘዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ በተከታታይ በመካከለኛው ምስራቅ የሚያደርጉትን ጉብኝት ቀጥለው በኳታር ይገኛሉ።

የብሊንከን አስተያየት የተሰማው በሰሜን ጋዛ በሚገኝ የስደተኞች ጣቢያ በደረሰ ጥቃት በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎች መገደላቸው ከተዘገበ በኋላ ነው።

ከጃባሊያ የተገኘ ምስል በፈራረሰ ህንፃ ውስጥ አብዛኛዎቹ ሴቶች እና ህጻናት የሆኑ ሰዎች አስክሬን ታይቷል።

የእስራኤል ጦር ስለሪፖርቶቹ እስካሁን ምንም ምላሽ አልሰጠም።

ትላንት በደቡብ ዃን ዩኒስ ከተማ ከ60 በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውም ተነግሯል።

እስራኤል በሐማስ ላይ ጦርነት ከጀመረች ወዲህ በጃባሊያ ጣቢያ ላይ በርካታ ጥቃቶች ተሰንዝረዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በጋዛ እየተካሄደ በሚገኘው ጦርነት ከ22 ሺህ የሚበልጡ ሰዎች (አብዛኛዎቹ ሴቶች እና ህጻናት ) ተገድለዋል ሲል በሐማስ የሚመራው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቋል። በእስራኤል ባለፉት 24 ሰዓት በፈጸመችው ቦምብ ጥቃት ቢያንስ 113 ሰዎች መሞታቸውንም ዘግቧል።

"ፍልስጤማዊያን ሲቪሎች ሁኔታዎች ሲፈቅዱ በፍጥነት ወደ ቀዬአቸው መመለስ መቻል አለባቸው። ጋዛን ለቀው እንዲወጡ ጫና ሊደረግባቸው አይገባም" ሲሉ ብሊንከን እሑድ ዕለት ተናግረዋል።

ቀኝ አክራሪው የእስራኤል የገንዘብ ሚኒስትር ቤዛሌል ስሞትሪች ፍልስጤማውያን ጋዛን ለቀው እንዲወጡ እና “በረሃው እንዲያብብ” ለሚያደርጉት እስራኤላውያን መንገድ እንዲጠርጉ ጠይቀዋል።

የብሔራዊ ደህንነት ሚኒስትሩ ኢታማር ቤን-ጊቪር በበኩላቸው በዚህ ሳምንት ለችግሩ "መፍትሔ" ይሆን ዘንድ የጋዛ ነዋሪዎችን ቀዬአቸውን ለቀው እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል ።

የእስራኤል መንግሥት ከዚህ ቀደም ይፋ ባደረጋቸው መግለጫዎቹ የጋዛ ነዋሪዎች ወደ ቤታቸው ሊመለሱ እንደሚችሉ አቋሙን አንጸባርቋል። ይሁን እንጂ ይህ እንዴት እና መቼ ሊሆን እንደሚችል ግን ግልጽ አልተደረገም።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በጋዛ ያለው ሁኔታ ከድጡ ወደ ማጡ መሆኑን ቀጥሏል። የጤና ባለስልጣናት እንዳሉት ሆስፒታሎችን ጨምሮ የህክምና ተቋማት ጭምር ከስጋት ነጻ አይደሉም።

እስራኤል የልቀቁ ትዕዛዝ ማውጣቷን ተከትሎ ሦስት ዓለም አቀፍ የህክምና ረድኤት ቡድኖች በማዕከላዊ ጋዛ ከሚገኘውን አል-አቅሳ ሆስፒታል እየወጡ መሆናቸውን አስታወቀዋል።

የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት (ኦቻ) ተወካይ ለቢቢሲ ወርልድ ሰርቪስ ኒውስሃወር “ይህ በእጅጉ አሳሳቢ ነው” ብለዋል።

"ቀድሞውንም የተጨናነቀው እና ከአቅም በላይ የሆነ ሥራ የሚያከናውነው ሆስፒታል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የሚሄደውን የተጎጂዎች ቁጥር ለመደገፍ የሚያስችል ምንም ድጋፍ የለውም" ሲሉ ጌማ ኮኔል ተናግረዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ቴድሮስ አድሃኖም በበኩላቸው ከ600 በላይ ታማሚዎችና የጤና ባለሙያዎች ሆስፒታሉን ለቀው ለመውጣት መገደዳቸውን ተናግረዋል።

“በአሁኑ ጊዜ የት እንዳሉ አይታወቅም” ሲሉ ቴድሮስ በኤክስ ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ ገልጸዋል።

በእስራኤል ሳይገደሉ አይቀሩም የተባሉትን የሐማስ መሪን ለመቅበር በርካቶች አደባባይ ወጥተዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, በእስራኤል ሳይገደሉ አይቀሩም የተባሉትን የሐማስ መሪን ለመቅበር በርካቶች አደባባይ ወጥተዋል።

ብሊንከን ወደ መካከለኛው ምስራቅ ያደረጉት የአሁኑ ጉብኘት በጋዛ ያለው ጦርነት ሊስፋፋ ይችላል በሚል በአካባቢው ውጥረት በነገሰበት ወቅት ነው።

የሐማስ ከፍተኛ ባለስልጣን የሆኑት ሳሌህ አል-አሩሪ ማክሰኞ ዕለት በደቡባዊ ቤይሩት በእስራኤል እንደሆነ በተጠረጠረ ጥቃት ተገድለዋል።

መቀመጫውን በሊባኖስ ያደረገው እና በኢራን የሚደገፈው ሄዝቦላህ መሪ ሃሰን ናስራላህ ግድያ እስራኤልን ዋጋ ያስከፍላል ብለዋል።

ሄዝቦላህ ቅዳሜ ዕለት ሮኬቶችን ወደ እስራኤል በመተኮስ ለአሩሪ ግድያ “ምላሽ” ሰጥቷል።

"አሁን በአካባቢው ከፍተኛ ውጥረት የነገሠበት ጊዜ ነው። ይህ ግጭት በቀላሉ ሊለወጥ የሚችል፣ የበለጠ የደህንነት ስጋት አልፎ ተርፎም የበለጠ ስቃይ የሚያስከትል ግጭት ነው" ብለዋል ብሊንከን።

የኳታር ጠቅላይ ሚኒስትር ሼክ መሐመድ ቢን አብዱራህማን አል-ታኒ በበኩላቸው የአሩሪ ግድያ “ሂደቱን ውስብስብ" አድርጎታል ብለዋል።

ብሊንከን አክለውም የአልጀዚራ የጋዛ ቢሮ ኃላፊ የበኩር ልጅ የሆነው ጋዜጠኛ ሃምዛ አል ዳህዱህ በእስራኤል በደቡባዊ ጋዛ በፈጸመችው ጥቃት መገደሉን “የማይታሰብ አሳዛኝ ክስተት ነው” ብለውታል።

በጦርነቱ "እጅግ በጣም ብዙ ንፁሃን ፍልስጤማውያን ወንዶች፣ ሴቶች እና ህጻናት" ሞተዋል ብለዋል።

ብሊንከን ኳታር የደረሱት በዮርዳኖስ፣ ቱርክ እና ግሪክ ጉብኝት ማድረጋቸውን ተከትሎ ነው። እሑድ አመሻሽ ላይ ወደ አቡ ዳቢ ያቀኑ ሲሆን ሰኞ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ይጓዛሉ።