ባይደን የግብፁን አል ሲሲ የሜክሲኮ ፕሬዝዳንት ማለታቸው መነጋገሪያ ሆነ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የግብፁን ፕሬዝዳንት አብደል ፋታህ አል ሲሲን በስህተት የሜክሲኮ መሪ ብለው በመጥራታቸው በግብፃውያን ዘንድ መነጋገሪያ ሆኑ።
ፕሬዝዳንት ባይደን ትናንት ሐሙስ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እስራኤል በጋዛ ላይ እያካሄደች ያለውን ዘመቻ በተመለከተ በተናገሩበት ጊዜ ነው አል ሲሲን የሜክሲኮ ፕሬዝዳንት ብለው የጠቀሷቸው።
“እንደምታውቁት መጀመሪያ ላይ የሜክሲኮው ፕሬዝዳንት ሲሲ፣ ወደ ጋዛ ሰብአዊ እርዳታ ለማስገባት በራቸውን መክፈት አልፈለጉም ነበር” በማለት ነበር ባይደን ስህተት የፈጸሙት።
ባይደን ፕሬዝዳንትነታቸውን ለአል ሲሲ በስህተት የሰጡባቸው አሜሪካንን በስተደቡብ የምታዋስነው ሜክሲኮ ፕሬዝዳንት አንድሬያስ ማኑኤል ሎፔዝ ኦብራዶር ናቸው።
ግብፃውያን ፕሬዝዳንት አል ሲሲን በተመለከተ ትችት በሚጽፉበት ጊዜ ሳንሱር እንዳይደረጉ አል ሲሲን ከሚለው ድምጽ ጋር በሚዛመደው “ኤል ሜክሲኪ” በማለት ይገልጿቸዋል።
ይህም በአረብኛ “ሜክሲኳዊው” ማለት ሲሆን በበርካታ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ ግብፃውያን ዘንድ የሚታወቅ የፕሬዝዳንቱ ቅጽል ስም ነው።
የባይደን ስህተትም የተከሰተው ከዚሁ ቅጽል ስማቸው ጋር በተያያዘ ነው በማለት በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ የመነጋገሪያ እና የመቀለጃ ርዕስ ሆኗል።
“ፕሬዝዳንቱን በነጻነት መተቸት ስለማይቻል አል ሲሲ የሚለው ድምጽ ከ‘አል ሜክሲኪ’ ጋር ስለሚመሳሰል ቁጥጥርን ለማምለጥ እና በነጻነት ለመተቸት ሲሉ ግብፃውያን በዚያ ስም ይጠሯቸዋል” ሲል አንድ የኤክስ (የቀድሞው ትዊተር) ተጠቃሚ ጽፏል።
ሌላኛው ግብፃዊ ደግሞ “ፕሬዝዳንቱን ስንተች በመንግሥት እንዳንታወቅ ‘ኤል ሜክሲኪ’ ብለን እንጠራዋለን፤ የፕሬዝዳንት ባይደን ስህተትም የበለጠ አስቂኝ የሚሆነው በዚህ ምክንያት ነው” ብሏል።
በሚመጣው ዓመት ለሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የዲሞክራቶች ዕጩ በመሆን ለሁለተኛ ዙር የሚወዳደሩት ጆ ባይደን የጤና እና የማስታወስ ሁኔታ በአሜሪካ ውስጥ መነጋገሪያ በሆነበት በአሁኑ ጊዜ አል ሲሲን የሜክሲኮ ፕሬዝዳንት አድርገው መናገራቸው የበለጠ ትኩረት ስቧል።
የ81 ዓመቱ ጆ ባይደን ከዕድሜ ጋር በተያያዘ የማስታወስ ችግር አለባቸው እየተባለ ቢወራም እሳቸው ግን አሜሪካንን ለመምራት የአዕምሮ ብቃት እንዳላቸው በመግለጽ የሚቀርብባቸውን ትችት አጣጥለውታል።
በሚቀጥለው ዓመት ኅዳር ላይ በሚደረገው ምርጫ ፕሬዝዳንት ባይደንን ይፎካከሯቸዋል ተብለው የሚጠበቁት በርካታ ክሶች የቀረቡባቸው የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ናቸው።












