ትራምፕ በስም ማጥፋት ክስ 83.3 ሚሊዮን ዶላር እንዲከፍሉ ተወሰነ

የፎቶው ባለመብት, REUTERS
ዶናልድ ትራምፕ በስም ማጥፋት ወንጀል ጥፋተኛ ተብለው 83.3 ሚሊዮን ዶላር ካሳ እንዲከፍሉ የዳኞች ስብስብ ፈረደባቸው።
ትራምፕ ፕሬዝዳንት ሳሉ እአአ በ2019 የጦማሪዋን ኢ ጄን ካሮልን ስም አጥፍተዋል በሚል ነበር የተከሰሱት።
በ1990ዎቹ ኢ ጄን ካሮል ላይ ወሲባዊ ትንኮሳ እንዳደረሱና ከዚያም ስሟን እንዳጠፏት በመግለጽ ክሱን ወደ ኒው ዮርክ ፍርድ ቤት ወስዳዋለች።
ክሱን እንዲሁም ብይኑን “ፈጽሞ የማይረባ” ሲሉ ትራምፕ አጣጥለዋል።
ትራምፕ የሰጡት አስተያየት በስሜቷ እንዲሁም በበጎ ስሟ ላይ ያደረሰውን ጉዳት ፍርድ ቤቱ ተመልክቷል።
ከዚህ በኋላ ክፉ ነገር እንዳይናገሯት ማድረጊያ መንገድም በፍርድ ቤቱ ተነስቷል።
ውሳኔው የተላለፈው ሰባት ወንድና ሁለት ሴት አባላት ባሉት ከሕዝብ በተውጣጡ ፍርድ ሰጭዎች (ጁሪ) ነው።
ውሳኔውን ተከትሎ ከሳሿ “ይሄ ለማንኛውም ጫና ለደረሰባትና አልሸነፍም ላለች ሴት ድል ነው። በጉልበት ተመክተው ሴቶችን ለመጨቆን የሚሞክሩ ደግሞ የተሸነፉበት ቀን ነው” ብላለች።
በዚህ ሂደት ላይ ተሳታፊ የነበሩ ከሕዝብ የተውጣጡ ፍርድ ሰጭዎች በክስ ሂደቱ ተሳታፊ መሆናቸውን ለሰዎች እንዳይናገሩ ተገልጾላቸው ነበር። ይህም ሊደርስባቸው የሚችለውን ጫና ከግምት በማስገባት ነው።
ከሳሿን አግተዋት እንደማያውቁና ከወንጀሉም ነጻ እንደሆኑ ትራምፕ ተከራክረዋል።
“በውሳኔው አልስማማም። ባይደን በእኔ እና በሪፐብሊካን ፓርቲ ያቀነባበሩት ነው” ብለዋል ትራምፕ።
“የሕግ ሥርዓታችን መላ ቅጡን አጥቷል። እንደ ፖለቲካዊ መሣሪያ ጥቅም ላይ እየዋለ ነው። ይሄ አሜሪካ አይደለም” ሲሉም አክለዋል።
አምና በተካሄደ የፍርድ ቤት ክርክር ወሲባዊ ትንኮሳ እንዳደረሱባት ብይን ተሰጥቷል። ይሄኛው ደግሞ የስም ማጥፋትም እንዳደረሱባት ብይን የሰጠ ነው።
ወሲባዊ ትንኮሳ እንደደረሰባት ስትገልጽ ‘ውሸት ነው’ በማለት ነው ስሟን ያጠፉት።
የትራምፕ ጠበቃ አሊና ሀባ ነበረች። በአንደኛው ቀን ፍርድ ቤቱን አቋርጠው ሊወጡ ሲሉ “እስር ቤት ልትገባ ትንሽ ነው የቀረህ። አርፈህ ተቀመጥ” ብላቸዋለች።
ዳኛውም ትራምፕ ሂደቱን እንዳያውኩ በተደጋጋሚ አስጠንቅቀዋል። ከፍርድ ቤት እንደሚያባርሯቸውም ገልጸው ነበር።
የከሳሿ ጠበቃ “ይህ ሂደት ትራምፕን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስቆም ያለመ ነው” ብለዋል።
ትራምፕ በአጠቃላይ 91 ክሶች አሉባቸው። በወንጀል በመከሰስ የመጀመሪያው የአሜሪካ ፕሬዝዳንትም ናቸው።
ክሶቹ ግን በጆ ባይደን የተቀነባበሩ ናቸው ሲሉ በተደጋጋሚ ከሰዋል።












