የትኞቹ አገራት የሞት ቅጣትን ተግባራዊ ያደርጋሉ? ምን ያህል ሰዎችስ ተገደሉ?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአሜሪካ በሞት እንዲቀጣ የተፈረደበት ግለሰብ በናይትሮጅን ታፍኖ ሕይወቱ እንዲያልፍ በመደረግ የመጀመሪያው ሰው ሆኗል።
በቀሰቀሰው እሳት አደጋ 36 ሰዎች እንዲሞቱ ያደረገው ጃፓናዊም በስቅላት እንዲገደል ተፈርዶበታል።
በርካታ የዓለም አገራት የሞት ፍርድን እያስቀሩ ቢሆንም፣ በሞት የሚቀጡ ሰዎች ቁጥር ግን እያሻቀበ መሆኑ ይነገራል።
ምን ያህል አገራት የሞት ቅጣትን ይተገብራሉ?
ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብቶች ተቆርቋሪ ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽናል በ2022 ባጠናቀረው መረጃ መሠረት በአሁኑ ወቅት፡
- በ55 አገራት የሞት ቅጣት ተግባራዊ ይደረጋል።
- ከእነዚህ አገራት መካከል ዘጠኙ በጦር ወንጀል እና በበርካታ ግድያዎች በተሳተፉ ላይ ብቻ ቅጣቱን ተግባራዊ ያደርጋሉ።
- 23 አገራት የሞት ቅጣት ቢኖራቸውም ለ10 ዓመታት ግን አልተጠቀሙበትም።
በየዓመቱ ስንት ሰዎች የሞት ቅጣት ይፈጸምባቸዋል?
የአምነስቲ ኢንተርናሽናል መረጃ ከሚመለከታቸው ምንጮች፣ ከመገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች እና ሞት ከተፈረደባቸው ግለሰቦች፣ ከቤተሰቦቻቸው እና ከተወካዮቻቸው የተገኘ ነው።
ቻይና ከሞት ቅጣት ጋር በተያያዘ መረጃ አታጋራም።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል እአአ በ2022 በዓለም አቀፍ ደረጃ 883 የሞት ቅጣት መፈጸሙን መዝግቧል። ይህ አሃዝ ቻይናን አያጠቃልልም።
በ2021 ከተገደሉት 579 ሰዎች አንጻር በ53 በመቶ ከፍ ያለ ነው። ከ2017 (እአአ) ወዲህም ከፍተኛው የሞት ቅጣት የተፈጸመበት ዓመት ነው።
ቁጥሩ በአንድ ዓመት ከአንድ ሺህ 500 በላይ ሰዎች ከተገደሉባቸው የአውሮፓውያኑ 1988፣ 1989 እና 2015 አሃዝ አንጻር በጣም አነስተኛ ነው።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል አክሎም በ2022 ቢያንስ 2 ሺህ 016 የሞት ፍርድ በ52 አገራት መተላለፉን አስታውቋል።
በ2021 ደግሞ 56 አገራት ቢያንስ 2 ሺህ 052 የሞት ፍርድ አስተላልፈዋል።
ብዙዎቹ እስረኞች ከመገደላቸው በፊት ዓመታትን ባስ ሲልም አሥርት ዓመታትን ለመጠበቅ ይገደዳሉ።
የሞት ቅጣትን በብዛት የሚፈጽሙ አገራት የትኞቹ ናቸው?
እአአ በ2022 ሃያ አገራት የሞት ቅጣትን ተግብረዋል። በ2021 በሞት የተቀጡ ሰዎች 18 ብቻ ነበሩ።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል እንደሚለው ከሆነ ቻይና ከየትኛውም አገር በበለጠ የሞት ቅጣት ትተገብራለች። በዓመት በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ይገደላሉ ተብሎ ቢታመንም ይህን ማረጋገጥ ግን አይችልም።
ከቻይና ሌላ ብዙ ሰዎችን በሞት የሚቀጡት አገራት ኢራን፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ግብፅ እና አሜሪካ ናቸው።

የተፈጸሙ የሞት ቅጣቶች አሃዝ መቀነስ
አምነስቲ ኢንተርናሽናል በየዓመቱ ያለማቋረጥ የሞት ፍርድ የሚተገብሩ 11 አገራት ላይ አጽንኦት ሰጥቷል።
እነዚህም ቻይና፣ ግብፅ፣ ኢራን፣ ኢራቅ፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ አሜሪካ፣ ቬትናም እና የመን ያካትታሉ።
ሰሜን ኮሪያ “የሞት ቅጣትን በቋሚነት ልትጠቀም እንደምትችል” ቢታመንም ይህንን ማረጋገጥ አልተቻለም።

ሳዑዲ አረቢያ በአውሮፓውያኑ 2022 የፈጸመቻቸው የሞት ቅጣቶች አሃዝ ባለፉት 30 ዓመታት ከፈጸመቻቸው ሁሉ በእጅጉ የላቀ ነው።
አምስት አገራት ማለትም ባህሬን፣ ኮሞሮስ፣ ላኦስ፣ ኒጀር እና ደቡብ ኮሪያ የሞት ቅጣትን ለበርካታ ዓመታት ጥቅም ላይ ሳያውሉ ቢቆዩም በ2022 የሞት ቅጣት ፍርድን ግን በይነዋል።
በአሜሪካ ውስጥ ደግሞ ከ1999 ወዲህ ባሉት ዓመታት የተፈጸሙ የሞት ቅጣቶች አሃዝ ቀንሷል።
አደንዛዥ እጽ እና የሞት ቅጣት
አምነስቲ ኢንተርናሽናል በ2022 በዓለም አቀፍ ደረጃ ከአደንዛዥ እጽ ወንጀሎች ጋር በተያያዘ 325 የሞት ቅጣቶች እንደነበሩ ገልጿል። ከእነዚህም ውስጥ
- 255 በኢራን
- 57 በሳዑዲ አረቢያ እና
- 11 ደግሞ በሲንጋፖር ናቸው።
ሲንጋፖር ከከሃያ ዓመታት በኋላ የመጀመሪያዋን ሴት በሞት ቀጥታለች። ሳሪዴዊ ጃማን በ2018 ሄሮይንን በማዘዋወር ወንጀል ተከሳ ነው ሞት ተፈረደባት።

የሞት ቅጣትን የሰረዙ አገራት
የሞት ቅጣት በ112 አገራት ጥቅም ላይ አልዋልም። በአውሮፓውያኑ 1991 ይህ አሃዝ 48 ነበር።
በ2022 ስድስት አገራት የሞት ቅጣትን ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ሰርዘዋል።
አራት አገራት ማለትም ካዛኪስታን፣ ፓፑዋ ኒው ጊኒ ፣ ሴራሊዮን እና መካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ ቅጣቱን ሙሉ በሙሉ ያስወገዱ አገራት ናቸው።
ኢኳቶሪያል ጊኒ እና ዛምቢያ ደግሞ በጣም ከባድ ለሆኑ ወንጀሎች ብቻ የሞት ቅጣት ተግባራዊ እንደሚያደርጉ አሳውቀዋል።
እአአ በ2023 የማሌዢያ ፓርላማ ግድያን እና ሽብርተኝነትን ጨምሮ ለ11 ከባድ ወንጀሎች አስገዳጅ የሞት ቅጣት እንዲነሳ ይንታውን ሰጥቷል።
የጋና ፓርላማ ደግሞ የሞት ቅጣትን ሙሉ ለሙሉ እንዲነሳ በ2023 ድምጽ ወስኗል።
አገሮች የሞት ቅጣትን እንዴት ይፈጽማሉ?
እአአ በ2022 አንገትን በመቅላት የሚፈጸምን የሞት ቅጣት እንደምትጠቀም የገለጸችው ብቸኛዋ አገር ሳዑዲ አረቢያ ነበረች።
ስቅላት፣ ገዳይ መርፌ እና በጥይት የሞት ቅጣትን ተግባራዊ ማድረግ ደግሞ ሌሎቹ የግድያ መፈጸሚያ ዘዴዎች ናቸው።
የዩናይትድ ስቴትሷ አላባማ ግዛት ኬኔት ስሚዝ የተባለ ነፍሰ ገዳይን ናይትሮጅን ጋዝ በመጠቀም ከቀናት በፊት በሞት ቀጥታለች።
በዚህ ዘዴ የተገደለ የመጀመሪያው ሰውም ሆኗል። የስሚዝ ጠበቆች ያልተሞከረውን ዘዴ “ጭካኔ የተሞላበት እና ያልተለመደ” ቅጣት ብለውታል።
አላባማ እና ሌሎች ሁለት የአሜሪካ ግዛቶች የሞት ፍርድን ለመፈጸም ናይትሮጅን መጠቀመን ፈቅደዋል።
ለዚህ ደግሞ ለገዳይ መርፌ በብዛት ጥቅም ላይ የሚውሉት መድኃኒቶችን ለማግኘት በጣም አስቸጋሪ መሆኑን በምክንያትነት አስቀምጠዋል።
የመድኃኒቱ እጥረት በመላው አሜሪካ የሞት ቅጣት እንዲቀንስም አስተዋጽኦ አድርጓል ተብሏል።












