አምስት ልጆቿን የገደለችው ቤልጂየማዊት እናት በፍላጎቷ እንድትሞት ተደረገ

የፎቶው ባለመብት, AFP
አምስት ልጆቿን የገደለችው ቤልጂየማዊት እናት ወንጀሉን ከፈጸመች ከ16 ዓመታት በኋላ በራሷ ፍላጎት ሕይወቷ እንዲያልፍ በጠየቀችው መሠረት ጥያቄዋ ተግባራዊ ሆነ።
ጄኔቪቭ ለኽርሚት ከሦስት አስከ 14 ዓመት እድሜ የነበራቸውን አንድ ወንድ እና አራት ሴት ልጆቿን ባሏ በሌለበት የገደለችው በአውሮፓውያኑ 2007 የካቲት ወር ላይ ነበር።
እናት ግድያውን ከፈጸመች በኋላ ራሷን ለማጥፋት ብትሞክርም ስላልተሳካለት እርዳታ እንዲደረግላት የአደጋ ጊዜ ሠራተኞችን ጠርታለች።
የ56 ዓመቷ እናት ለወንጀል ድርጊቷ የእድሜ ልክ እስራት ተፈርዶባት እስከ 2019 ድረስ በእስር ቤት ቆይታ፣ ከዚያ በኋላ ደግሞ ወደ ሥነ አእምሮ ሆስፒታል ተዘዋውራ ቆይታለች።
ቤልጂየም ውስጥ “በከባድ” እና በማይድን አካላዊ ብቻ ሳይሆን ሥነ አእምሯዊ ችግር የሚሰቃዩ ሰዎች በህክምና ድጋፍ የርህራሄ ግድያ በሚባለው መንገድ ለመሞት ከጠየቁ ሕጉ ይፈቅድላቸዋል።
ነገር ግን ይህንን ጥያቄ የሚያቀርቡ ሰዎች ውሳኔያቸው የሚኖረውን ውጤት የሚገነዘቡ እና ይህንንም በምክንያት ያለመወላወል ማስረዳት የሚችሉ መሆን አለባቸው።
“የጄኔቪቭ ውሳኔም ይህንኑ የአገሪቱን የሕግ ሂደት የተከተለ እና የተለያዩ የህክምና አስተያየቶችን ያካተተ ነበር” ሲሉ ጠበቃዋ ተናግረዋል።
የሥነ ልቦና ባለሙያ የሆኑት ኤሚሊ ማሪዮት ለአንድ የቴሌቪዥን ጣቢያ እንደተናገሩት፣ ጄኔቪቭ ለገደለቻቸው “ልጆቿ ያላትን አክብሮት ለመግለጽ” ግድያው በተፈጸመበት ዕለት ሕይወቷ እንዲያበቃ ሳትጠይቅ አትቀርም ብለዋል።
“ምናልባትም ልጆቿን ከገደለች በኋላ ራሷን ለማጥፋት ያደረገችው ሙከራን በዚህ መንገድ ለማጠናቀቅ ፈልጋ ሊሆን ይችላል” ብለዋል ባለሙያዋ።
ከ15 ዓመታት በፊት ኒቬሊስ በተባለችው የቤልጂየም ከተማ ውስጥ በአምስት ልጆቿ ላይ ግድያን የፈጸመችው እናት ጉዳይ እና የፍርድ ሂደት አገሪቱን አስደንግጦ ነበር።
በፍርድ ሂደቱ ወቅት የጄኔቪቭ ጠበቆች ተከሳሿ የአእምሮ መረበሽ የገጠማት በመሆኑ እስር ቤት መግባት የለባትም ብለው ተከራክረው ነበር። ዳኞች ግን ግድያው የታሰበበት ነው በማለት ጥፋተኝነቷን አረጋግጠው የእድሜ ልክ እስራት ፈርደውባታል።
በአውሮፓውያኑ 2010 እናት አንድ የቀድሞ የሥነ ልቦና ባለሙያ “ግድያውን እንዳልፈጽም የሚያደርግ ድጋፍ አላደረገልኝም” በሚል የሦስት ሚሊዮን ዩሮ የፍትሃ ብሔር ክስ አቅርባ ከ10 ዓመታት በኋላ ክሱን ትታዋለች።
ባለፈው የፈረንጆች ዓመት በቤልጂየም ውስጥ 2,966 የሚሆኑ ሰዎች እንደ ጄኔቪቭ የርህራሄ ግድያ በሚባለው በራስ ፈቃድ በህክምና ድጋፍ እንዲሞቱ ተደርገዋል። ይህ አሃዝም ቀደም ካለው ዓመት የ10 በመቶ ጭማሪ ኣሳይቷል።
ለዚህ የሞት ጥያቄ ከሚቀርቡት ምክንያቶች መካከል የካንሰር ህመም በስፋት የሚጠቀስ ነው። ባለሥልጣናት እንደሚሉት ከሚቀርቡት አራት ምክንያቶች ሦስቱ “በተለያየ አይነት አካላዊ እና ሥነ ልቦናዊ ችግሮች መሰቃየታቸውን” ይጠቅሳሉ።
ከአውሮፓውያኑ 2014 ጀምሮ ቤልጂየም ከአዋቂዎች በተጨማሪ ሕጻናት በማይድን እና ከባድ ስቃይን በሚያስከትል ህመም ውስጥ ከሆኑ የርህራሄ ግድያ እንዲፈጸምላቸው ፈቅዳለች። ለዚህም የወላጆች ፈቃድ ያስፈልጋል።












