የዓድዋ በዓልን በአጼ ምኒልክ አደባባይ ለማክበር የወጡ ታዳሚዎች በአስለቃሽ ጭስ ተበተኑ

ፖሊሶች በአጼ ምኒልክ አደባባይ አካባቢ

የፎቶው ባለመብት, social media

የ127ኛው የዓድዋ ድል በዓልን በአጼ ምኒልክ አደባባይ ለማክበር የወጡ ነዋሪዎች በፀጥታ ኃይሎች በአስለቃሽ ጭስ ሲበተኑ፣ በጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ውስጥም የነበረው ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት ሳይጠናቀቅ ተቋረጠ።

በዓሉ በተለያዩ ዝግጅቶች መከበሩን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን እየዘገቡ ቢሆንም ዋናው የበዓል ሥነ ሥርዓት በተካሄደበት በአዲስ አበባ ከዚህ ቀደም ያልታዩ ሁኔታዎች እንዳጋጠሙ ባለፉት ዓመታት በዓሉን ሲታደሙ የነበሩ ነዋሪዎች ተናግረዋል።

ቀደም ባሉት ዓመታት የዓድዋ ድል በዓል በዋናነት መሃል አዲስ አበባ፣ ፒያሳ ውስጥ በሚገኘው በአጼ ምኒልክ አደባባይ በተለያዩ ዝግጅቶች በርካታ ሕዝብ ታድሞበት ይከበር ነበር።

በዘንድሮው ክብረ በዓል ግን የጸጥታ ኃይሎች አስለቃሽ ጭስ በመተኮሳቸው ፕሮግራሙ መስተጓጎሉን በዓሉን በማድመቅ እና በመታደም የሚታወቀው አርቲስት ሚካኤል ሚሊዮን ለቢቢሲ ተናግሯል።

ከዚህ በፊት በነበሩ ዓመታት ከሚኒልክ አደባባይ ወደ ዓድዋ ድልድይ ጉዞ ይደረግ እንደነበር የሚያስታውሰው ሚካኤል፣ “ዘንድሮ ሰው ወደዚያ እንዲጓዝ አልፈለጉም። ቀድሞውኑም አደባባዩ ላይ ብዙ ሰው እንዲኖርም የፈለጉ አይመስልም።

የአደባባዩ አምስቱም በሮች በመዘጋታቸውም ወደ አደባባዩ ብዙ ሰው እንዲደርስ አልተደረገም። በ6ኛው በር ብቻ ነበር የተከፈተው። አስለቃሽ ጭስ የተኮሱትም የአደባባዩን ፕሮግራም ቶሎ ለመበተን ይመስለኛል” ብሏል።

127ኛው የዓድዋ ድል በዓል “አንድነት፣ ጀግንነት እና ጽናት” በሚል መሪ ሐሳብ እንደሚከበር ከተገለጸ በኋላ፣ በአዲስ አበባ ውስጥ የተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚካሄዱ ተገልጾ ነበር።

ከእነዚህም መካከል እንደተለመደው በምኒልክ አደባባይ ሥነ ሥርዓት እንደሚኖር ቢጠበቅም ይህ ሳይሆን ቀርቷል።

ከዚህ በፊት እንደሚሆነው ጠዋት ላይ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ፕሬዝዳንት የሆኑት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ በዳግማዊ ምኒልክ አደባባይ ተገኝተው በመታሰቢያ ሐውልቱ ስር የአበባ ጉንጉን ያስቀመጡ ቢሆንም ከዚህ ያለፈ ትዕይንት በስፍራው አልነበረም።

ለበርካታ ዓመታት የዓድዋ በዓልን ከመገናኛ አካባቢ በመምጣት ሲያከብሩ እንደነበር የሚናገሩት አቶ ደረጀ ክብሩ የዛሬው ሁኔታ ግራ እንዳጋባቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“ትልቅ የበዓል ዝግጅት በመስቀል አደባባይ እንደሚካሄድ ባውቅም በምኒልክ አደባባይ የተለመደው ዝግጅት ይኖራል ብዬ ወደ ፒያሳ ባመራም። ወደ አደባባዩ ማለፍ እንደማይቻል በፖሊሶች ተነግሮኝ ተመልሻለሁ” ብለዋል።

በተለመደው ሁኔታ የበዓሉ ሥነ ሥርዓት ይካሄዳል ብለው የመጡ እና በስፍራው ተሰብስበው በነበሩ ታዳሚዎች ላይ ፖሊስ አስለቃሽ ጭስ በመተኮስ ከስፍራው ሲያባርር እንደነበርና የተደበደቡም እንዳሉ አቶ ደረጀ እማኝነታቸውን ገልጸዋል።

በክብረ በዓሉ ላይ ሦስት ሕጻናት ልጆቹን ይዞ የተገኘው አርቲስት ሚካኤልም፣ አስለቃሽ ጭሱ የተተኮሰው በሕጻናት ልጆች ላይ ነው ብሏል።

“ከ13 ዓመት በታች የሆኑ በርካታ ሕጻናት በፕሮግራሙ ላይ ተገኝተው ነበር። እነርሱ ላይ ነው እንደዚህ የተደረገው። ሕጻናት አደባባይ የወጡት በአገራቸው እንዲኮሩ እንጂ እንዲያፍሩ አልነበረም” ሲልም ወቅሷል።

ፖሊሶች ሰዎችን ሲያባርሩ

የፎቶው ባለመብት, social media

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ቀደም ባሉት ዓመታት የዓድዋ ድል በዓል በሚከበርበት ጊዜ ከተለያዩ የአዲስ አበባ ክፍሎች እንዲሁም ከከተማዋ ውጪ ያሉ ፈረሰኞች ጭምር በአደባባዩ በመገኘት በሥነ ሥርዓቱ ላይ ይታደሙ ነበር።

በአጼ ምኒልክ አደባባይ የተካሄደው 127ኛው የድል በዓል ግን ለአጭር ጊዜ የቆየ እና በርካታ ታዳሚዎች ወደቦታው እንዳይገቡ የተከለከሉበት እንዲሁም አስለቃሽ ጭስ የተለቀቀበት እና አንዳንዶችም በቆመጥ የተመቱበት እንደነበር በስፍራው የነበሩ የዓይን ምስክሮች ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ለበዓሉን የተለያዩ ባህላዊ እና ኪነጥበባዊ ዝግጅቶችን ለማቅረብ ተዘጋጅተው የነበሩ ስብስቦችም ወደ አደባባዩ ለመግባት መከልከላቸውን አቶ ደረጀ ጠቅሰው፣ በምኒልክ አደባባይ የነበረው የበዓሉ አከባበር “ደስ የማይል ድባብ የነበረው” ነው በማለት ተናግረዋል።

አርቲስት ሚካኤልም የተደረገው ከዓድዋ ስሜት እና ታሪክ ጋር የተጻረረ ነው ብሏል።

“ትልቅ ክብረ በዓል እንዲሆን አስበን የጀመርነው ዝግጅት ነው። በወቅቱ የነበረውን ትውፊት በሚያሳይ መልኩ የዛሬ ሰባት ዓመት ነው የጀመርነው። ሰዎች የዓድዋን ታሪክ የሚካፈሉበት እንዲሆን ነበር ስንጥር የነበረው። የሚጎበኝ ትርዒት እንዲሆን ጥረት ስናደርግ ነበር።

“ዘንድሮ በመከላከያ ሚኒስቴር ደረጃ መከበሩ ጥሩ ነው። ግን ይህ በዓል የሕዝብ ነው። የመከላከያ ብቻ አይደለም። እዚህ አክብር፣ አታክብር መባል ከዓድዋ ስሜት ጋር አይሄድም።ዓድዋ የነጻነት በዓል ነው”

በየዓመቱ የካቲት 23 የሚከበረው የዓድዋ ድል በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አማኞች ዘንድ ከሚከበረው የቅዱስ ጊዮርጊስ በዓል ጋር ተመሳሳይ ሲሆን፣ በምኒልክ አደባባይ አቅራቢያ በሚገኘው የቅዱስ ቤተክርስቲያን ውስጥም አስለቃሽ ጭስ መለቀቁን በስፍራው የነበሩ እማኞች ገልጸዋል።

ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን አገልጋይም የድል በዓሉን ለማክበር ሌሊቱን ዝግጅት ሲያደርጉ እንደነበር ገልጸው፣ ዛሬ ጠዋት በምኒሊክ አደባባይ የተለመደውን መርሃ ግብር ለማድረግ ሲወጡ አደባባዩ በአድማ በታኝ ፖሊሶች ተከቦ ማየታቸውንና በገና የያዙ እና ኃይማኖታዊ አልባሳት የለበሱ መንፈሳዊ ሰዎች ወደዚያ እንዳይሄዱ መከልከላቸውን ተናግረዋል።

“ሰው ‘ምኒልክ ዛሬም ንጉሥ ነው!’ እያለ ያጨበጭብ ፣ ያፏጭ ነበር። እኛም ወደ ቤተክርስቲያኑ ስንመለስ አድማ በታኞች አስለቃሽ ጭስ ተኮሱ። ከዚያ በኋላ የሆነውን መግለጽ አዳጋች ነው” ብለዋል።

የቤተክርስቲያኗ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾችም ከመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች “በተተኮሰ አስለቃሽ ጭስ ምክንያት በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በመናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን በርካታ ሕዝብ የታደመበት ክብረ በዓል” ሳይጠናቀቅ መቋረጡን አስፍረዋል።

የቤተክርስቲያኗ የፌስቡክ ገጽ እንዳሰፈረው ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት ከተፈጸመ በኋላ “ክብረ በዓሉ እየተከናወነ ባለበት ወቅት ከመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ወደ ቅጽረ ቤተ ክርስቲያኑ በተወረወረ አስለቃሽ ጭስ የበዓሉ ሥነ-ሥርዓት ሳይጠናቀቅ ታቦታተ ሕጉ ወደ መንበረ ክብራቸው ተመልሰዋል”።

በዚህም ሳቢያ በርካታ ምዕመናን በመጎዳታቸው ራሳቸውን ስተው ወደ ሆስፒታል እንደተወሰዱ ተነግሯል።

በዚህ በዓል ላይ ካጋጠመው ክስተት ጋር በተያያዘ መግለጫ ያወጣው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) አንድ አባሉ ከፀጥታ ኃይሎች በተተኮሰ ጥይት መገደሉን ገልጾ፣ የፀጥታ ኃይሎች በበዓሉ አክባሪዎች ላይ ፈጽመውታል ከተባለው ድርጊት ጋር በተያያዘ መንግሥት አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስድ ጠይቋል።

በፀጥታ ኃይሎች ስለተወሰደው እርምጃ ቢቢሲ ከፌደራል ፖሊስ እና ከአዲስ አበባ ፖሊስ ማብራሪያ ለማግኘት ያደረገው ሙከራ አልተሳካም።

የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ሐሙስ አመሻሽ ላይ ባወጣው መግለጫ ላይ በዓሉ በታሰበው መሠረት መከበሩን ገልጾ፣ ነገር ግን “በምኒልክ አደባባይ የሚደረገውን በዓል ለመረበሽ የፈለጉ አካላት ሁከት ለመቀስቀስ ሞክረዋል” ብሏል።

በዚህም “የአደባባዩ በዓል መረበሽ ሲያቅታቸው በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን የሚደረገውን ሃይማኖታዊ በዓል ለመረበሽ” እንደሞከሩ እና የፀጥታ ኃይሎች ሁከት ፈጣሪዎችን ለመቆጣጠር ባደረጉት “ጥረት በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ሲካሄድ የነበረው ሃይማኖታዊ በዓል መስተጓጎሉን እና ምእመናን ላይ መጠነኛ ጉዳት” መድረሱን ገልጿል።

ከዚህ በሻገር የዓድዋ ድል በዓል አዲስ አበባ ውስጥ በዓድዋ ድልድይ እና በመስቀል አደባባይ መከበሩን የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

መስቀል አደባባይ ላይ በተካሄደው ሥነ ሥርዓት ላይ የአገሪቱ ፕሬዝዳንት፣ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም፣ ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ ዲፕሎማቶች እና በርካታ ሕዝብ የታደመ ሲሆን የተለያዩ ትርኢቶች ቀርበዋል።

ከዚህ በፊት ከነበረው የዓድዋ ድል አከባበር ሁኔታ በተለየ የወታደራዊ ሰልፍ ትርኢቶች፣ የከባድ መሳሪያ ትዕይንት፣ የጦር ጄቶች እና ሄሊኮፕተሮች ትርኢቶችን በማሳየት በዓሉን አድምቀውታል።