አሜሪካዊው ፍርደኛ በናይትሮጂን ጋዝ በሞት በመቀጣት የመጀመሪያው ሰው ሆነ

ኬነት ዩጂን ስሚዝ በተያዘ ጊዜ በፖሊስ የተነሳው ፎቶ

የፎቶው ባለመብት, WHNT/CBS

የምስሉ መግለጫ, ኬነት ዩጂን ስሚዝ በተያዘ ጊዜ በፖሊስ የተነሳው ፎቶ

በግድያ ወንጀል ጥፋተኛ የተባለው ኬነት ዩጂን ስሚዝ በአሜሪካ በናይትሮጂን ጋዝ የሞት ቅጣት የተፈጸመበት የመጀመሪያው ሰው ሆነ።

በአልባማ ግዛት የሞት ቅጣቱ የተፈጸመው።

የ58 ዓመቱ ኬነት አንድ ግዜ ለፌደራል ፍርድ ቤት፤ ሁለት ግዜ ደግሞ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት በናይሮጂን ጋዛ የሞት ቅጣት መፈጸም ጭካኔ የተሞላበት እና ከዚህ ቀደም ተሞክሮ የማያውቅ ነው ሲል ያቀረበው አቤቱታ ተቀባይነት አላገኘም።

እአአ በ2022 የአልባማ ግዛት ግለሰቡን በመርፌ በሞት ለመቅጣት ያደረገው ሙከራ ደም ስሩን ማግኘት ባለመቻላቸው ሳይሳካ ቀርቶ ነበር።

ግለሰቡ በ1989 በቅጥረኛ ገዳይነት ተሰማርቶ የሰባኪ ሚስት ገድሎ ነበር የተከሰሰው።

እንደ ዴዝ ፔናሊቲ ኢንፎርሜሽን ሴንተር ከሆነ ግለሰቡ በአሜሪካ ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም በናይሮጂን ጋዛ ዘዴ የተገደለ የመጀመሪያው ሰው ሆኗል።

ናይትሮጂንን ለገድያ ለመጠቀም አልባማን ጨምሮ አንድ የአሜሪካ ግዛትም ፈቅዷል።

የኬነት ግድያ ሲፈጸም አምስት ጋዜጠኞች ተገኝተዋል።

ኬነትም “ዛሬ አልባማ ሰብአዊነትን ወደኋላ የጎተተችበት ቀን ነው። ስለደገፋችሁኝ አመሰግናለሁ። ሁላችሁንም እወዳችኋላሁ” ብሏል።

ቢያንስ ከሁለት እስከ አራት ደቂቃ እንደተንፈራገጠ የዐይን እማኞች ተናግረዋል።

ናይትሮጂን ያለ ኦክስጅን ወደሰውነት ሲገባ በደም ሕዋሳት ላይ ጉዳት አድርሶ ሞት ያስከትላል።

የአልባማ አገረ ገዥ ኬይ ሌቪ ግድያው ሲፈጸም ለመገኘት አልፈቀዱም።

“ከ30 ዓመታት ሙከራ በኋላ ለአስከፊ ወንጀሉ ተቀጥቷል” ሲሉ ግን ገልጸዋል። የተገደለችው ኤልዛቤት ሴኔት ቤተሰቦች በስተመጨረሻ እረፍት እንደሚያገኙም አክለዋል።

ስሚዝ የ45 ዓመቷን ኤልዛቤት አንድ ሺህ ዶላር ተከፍሏቸው ከገደሏት ሁለት ወንጀል ፈጻሚዎች መካከል አንዱ ነው።

ተደብድባ ደረቷ እና አንገቷ ላይ በጩቤ ተወግታ ሕይወቷ አልፏል። ሕይወቷ ያለፈው በቤት ዘረፋ ወቅት እንዲመስል ተሞክሮ ነበር።

በዕዳ የተዘፈቀውና ሰባኪ የነበረው ባለቤቷ የኢንሹራንስ ገንዘብ ለማግኘት ግድያውን ማስፈጸሙ ታውቋል። መርማሪዎች ሊደርሱበት መሆኑን ሲያውቅ ራሱን አጥፍቷል።

ከኬነት ጋር በተባባሪነት ወንጀሉን የፈጸመው ጆን ፎረስት ፓርከር በ2010 በሞት ተቀጥቷል።

ኬነት ተጎጂዋ ስትገደል መገኘቱን ቢያምንም በጥቃቱ እንዳልተሳተፈ ለፍርድ ቤት ተናግሯል።

የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽነር ኬነትን በጋዝ መግደል፣ ማሰቃየት ወይም ሌላ ጭካኔ የተሞላበት ወይም ኢ-ሰብአዊ ሊሆን እንደሚችል በመግለጽ በዚህ መንገድ የሚደረገው ግድያ እንዲቆም ጠይቆ ነበር።

የኬነት ጠበቆች፣ ወንጀለኞችን በዚህ የግድያ ዘዴ መግደል ማለት "ከጨካኝ እና ያልተለመደ" ቅጣት የሚጠብቀውን የአሜሪካ ሕገ መንግሥት መጣስ ነው ብለው በጠቅላይ ፍርድ ቤት ተከራክረው ነበር።

 የተገደለችው ኤልዛቤት ሴኔት

የፎቶው ባለመብት, WHNT/CBS

የምስሉ መግለጫ, የተገደለችው ኤልዛቤት ሴኔት

የአልባማ ማረሚያ ቤት አስተዳደር ጆን ሀማ እንዳሉት በግድያው ወቅት ኬነት መንፈራገጡ የሚጠበቅ ነው። ስለ ናይትሮጂን ጋዝ ግድያ ጥናት እንዳደረጉም አክለዋል።

የተገደለችው ሴት ልጅ የሆነው ቻርልስ ሴኔት ጁንየር በመጠኑ ለኬነት ሐዘኔታ እንደሌለው ተናግሯል።

“አንዳንዶች መሰቃየት የለበትም ይላሉ። እሱ ግን እናቴ እንድትሰቃይ አድርጓል። ደጋግሞ በስለት ወግቷል” ብሏል።

የኬነት ጠበቆች ግን በግድያው ሐዘናቸውን ገልጸዋል።

“የተከሰሰበት አሰቃቂ ድርጊት ወደኋላ አይቀለበስም። የሱ ሕይወት ግን እንዲህ መሆን አልነበረበትም” ብለዋል ጠበቆቹ።

ከመገደሉ በፊት ቤተሰቦቹ፣ ጓደኞቹና የሃይማኖት አባት ጎብኝተውታል።

ለመጨረሻ ቁርሱ ሁለት ብስኩት፣ እንቁላል፣ የአፕል ስልስ ተመግቦ የብርቱካን ጭማቂ ጠጥቷል።