‘ተዉኝ ልኑርበት!’. . . ዜጎች መረጃ ለመስጠት ያለባቸው ስጋት እና የመገናኛ ብዙኃን ፈተና

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
‘ልጆቼን ላሳድግበት!’
‘ተውኝ ልኑርበት!’
‘ደኅንነት ናችሁ!’
‘ስልካችንን ይከታተላሉ፤ ስልካችን ተጠልፏል።’
‘ስልኬን ከማን አገኛችሁ?’
‘ድጋሚ እንዳትደውሉልኝ!’ . . .
. . . እነዚህ ምላሾች በአማራ ክልል ስላለው ግጭት እና ውጊያ ጋዜጠኞች የዐይን እማኞችን እና ነዋሪዎችን ለማነጋገር ሲሞክሩ በተደጋጋሚ የሚያገኟቸው ናቸው።
ስድስት ወራትን በደፈነው በመንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል እየተካሄደ ባለው ጦርነት ከባድ ጉዳቶች እና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እየተፈጸሙ እንደሆነ ይነገራል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) “የትጥቅ ግጭት” ሲል ጦርነቱን በገለጸበት የጥቅምቱ መግለጫው፤ ግጭቱ በከባድ መሳሪያ እና በአየር ድብደባ የታገዘ ነው ብሏል። በዚህም እየተፈጸሙ ያሉ ያለፍርድ ግድያዎችን፣ የመብት ጥሰቶችን እና ሌሎችንም ጉዳዮች በዝርዝር አቅርቦ ነበር።
የአገር ውስጥ እና የውጭ መገናኛ ብዙኃን በክልሉ ውስጥ ስላለው ሁኔታ እና በጦርነቱ ምክንያት በነዋሪዎች ላይ ስለደረሱ ጉዳቶች፣ የመብት ጥሰቶችን እና በደሎችን እንዲሁም አዳዲስ ክስተቶችን ለመዘገብ የሚያደርጉት ጥረት ፈተና ውስጥ መግባቱን ያመለክታሉ።
ግጭቱ በክልሉ ውስጥ ከተባባሰበት ጊዜ አንስቶ አንዳንድ አካባቢዎች ሙሉ በሙሉ የበይነ መረብ ግንኙነት እንዲሁም የስልክ ግንኙነቶች በከፊል በመቋረጣቸው ትክክለኛ መረጃ ለማግኘት እንቅፋት ሆኗል።
ከዚህ ባሻገርም ጋዜጠኞች መረጃ ለማግኘት የሚያናግሯቸው በክልሉ ውስጥ የሚገኙ የመንግሥት ኃላፊዎች እና ነዋሪዎች በተለያዩ ምክንያቶች የተከሰቱ እና የተመለከቷቸውን ነገሮች ለመናገር ፈቃደኛ ስለማይሆኑ፤ የሚመለከታቸው የመንግሥት ኃላፊዎችን ለማናገር ያደረጉት ሙከራ አለመሳካቱን በተደጋጋሚ ሲገልጹ ይሰማል።
ግጭቶች ወይም ጥቃቶች ካጋጠሙ በኋላ እንዲሁም አስተዳደራዊ ቅሬታዎችን በተመለከተ የፀጥታ ችግር ባለባቸው የአገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙ የዐይን እማኞች ለደኅንነታቸው በመስጋት መረጃ ከመስጠት እየተቆጠቡ ነው። ፈቃደኛ የሆኑት ምንጮች ደግሞ ማንነታቸው እንዳይገለጽ ይጠይቃሉ።
በዚህም ሳቢያ የመብት ጥሰቶች እና በደሎች በአግባቡ ሳይዘገቡ እንዲቀሩ ምክንያት እየሆነ ነው። ይህ ደግሞ የሚመለከታቸው አካላት አስፈላጊውን የማስተካከያ እርምጃ እንዳይወስዱ እና አጥፊዎች በድርጊታቸው እንዳይጠየቁ ያደርጋል።
የጋዜጠኞች መረጃ የማግኘት ፈተና
በኢትዮጵያ በሚካሄዱ ግጭቶች ጋዜጠኞች መረጃ ለማግኘት የሚቸገሩ ሲሆን፤ የሚወጡ ዘገባዎችም ቢሆኑ ማንነታቸው በማይጠቀሱ ምንጮች ላይ የተንጠለጠሉ ናቸው። ይህም የመገናኛ ብዙኃኑን ተአማኒነትን ጥያቄ ውስጥ ያስገባል።
ሐምሌ 2015 ዓ/ም የተቀሰቀሰው የአማራ ክልል ጦርነት በጽንሰ ሀሳብ ደረጃ የመገናኛ ብዙኃንን ቀልብ መሳብ ነበረበት።
ግጭት ለመገናኛ ብዙኃኑ ‘ትልቅ ከበያ’ ከመሆኑ ባለፈ ለግጭቶች መፍትሄ ለማፈላለግና የሰላም አማራጮችን ለማመላከት አበርክቶ አላቸው።
ባለፉት ወራት ተባብሶ በአማራ ክልል ወደ ይፋዊ ወታደራዊ ግጭት የተሸጋገረው የፀጥታ መደፍረስን በተመለከተ ጋዜጠኞች መረጃ ለማግኘት ከባድ ፈተና እንደገጠማቸው ይናገራሉ።
በአማራ ክልል ያለውን ሁኔታ በተመለከተ ጋዜጠኞች መረጃ ለማግኘት ወደ ቦታው ሄደው ለመዘገብ የሚያደርጉት ጥረት ከተፈጠረው ስጋት አንጻር ፈታኝ ሲሆን፤ በመንግሥት በኩልም መደበኛ መረጃ የማይሰጥ ከመሆኑ ባሻገር ጦርነቱን በተመለከተ የሚያጋጥሙ ክስተቶች ላይ ማረጋገጫ ለመስጠትም ሆነ ለማስተባበል ፈጽሞ ፈቃደኝነት የለም።
ሰሎሞን [የደኅንነት ስጋት ስላለበት ስሙ የተቀየረ] በአንድ የግል መገናኛ ብዙኃን የሚሠራ ጋዜጠኛ ነው። በአማራ ክልል ያለው ጦርነት ተገቢውን የመገናኛ ብዙኃን ሽፋን አላገኘም ብሎ ያምናል።
ወደ ስፍራው ለመሄድ ያለ ፈተና፣ ነዋሪዎች በስጋት ምክንያት ያጋጠማቸውን እና ያዩትን ከመናገር መቆጠብ እና የመንግሥት ኃላፊዎች በእነሱ በኩል ያለውን መረጃ ለማጋራት ፈቃደኛ አለመሆን አስተማማኝ እና ወቅታዊ መረጃን ለማቅረብ እንቅፋት ሆነዋል ይላል።
መረጃ ለማግኘት “በሰው በሰው፤ በዘመድ” እንሄዳለን የሚለው ሌላው ጋዜጠኛ ግሩም፤ ምንጮች አደጋ እንዳይገጥማቸው ካላቸው ስጋት የተነሳ መረጃ ለማግኘት በሚያውቁት እና በሚያምኑት ሰው በኩል መቅረብ ግድ መሆኑን በመጥቀስ ያ ካልሆነ ግን “ጋዜጠኛ ነኝ” ብቻ ብሎ ማሳመን አደጋች ነው ይላል።
“መረጃውን ከሰጡን በኋላ ይደነግጡና አንዳንዶች መልሰው ይጠይቁናል፤ ‘ማናችሁ እናንተ? የምር ጋዜጠኞች ናችሁ? ከየት ነው?’ የሚለውን ይጠይቁናል። እያወቁ እንኳ የማያናግሩን ብዙ ናቸው። አትደውሉልን የሚሉ፣ ጋዜጠኞች ነን ስንል ደንግጠው ስልክ የሚዘጉ ብዙ አሉ” በማለት ውጣ ውረዱን ይገልጻል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
“ግድ ስለሆነ አለመናገርን እንመርጣለን”
ቢቢሲ ለዚህ ዘገባ የአማራ ክልል ነዋሪዎች ለመገናኛ ብዙኃን መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ የማይሆኑበትን ምክንያት ለማወቅም ፈቃደኛ ያልሆኑ በርካታ ነዋሪዎች ገጥመውታል።
ሆኖም ፈቃደኛ የሆኑ አራት ነዋሪዎች ለመገናኛ ብዙኃን መረጃ ለመስጠት ከመንግሥት በኩል ችግር ሊደርስብን ይችላል የሚል ስጋት እንዳለባቸው ተናግረዋል።
በአማራ ክልል የደቡብ ወሎ ነዋሪ የሆነ አንድ ወጣት ስለምንም ነገር ለጋዜጠኞች ከመናገርም ሆነ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ከማስፈር መቆጠቡን ይገልጻል። ሊከተል የሚችለውን “ጦስ” በመፍራት አለመናገርን እንደሚመርጥ የሚናገረው ወጣቱ፤ “ስጋቴ ተገቢ ነው” ይላል።
“ባለኝ ስጋት ምክንያት ብዙ ነገሮችን በውስጤ አምቄ ይዣለሁ። ጉዳቶችን፣ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን እና የማያቸውን ነገሮች ለመናገር አልቻልኩም። ስጋቴ ደግሞ ተገቢ ነው። ምክንያቱም መናገሬ እራሴን፣ ቤተሰቤን እና ሥራዬን ዋጋ የሚያስከፍለኝ ከሆነ ዝምታ ተመራጭ ነው” በማለት ወጣቱ ሁኔታውን ገልጿል።
ሌላው ግለሰብም ‘ስልካችን ክትትል ይደረግበታል፤ ስልካችን ተጠልፏል’ የሚል ስጋት በብዙዎች ዘንድ ስላለ እሳቸውም በማንኛውም ዓይነት መንገድ ለመገናና ብዙኃን መረጃን ከመስጠት መቆጠባቸውን ይናገራሉ።
“ስልካችን እንደሚጠለፍ እናውቃለን” በማለት መረጃን በስልክ ለመገናኛ ብዙኃን መስጠቱ ሳይቀር ችግር ላይ እንደሚጥል የሚናገረው አንድ የዩኒቨርስቲ ተማሪ፤ በጥቆማ እስር እና ጥቃት እንደሚፈጸም በአካባቢው እንደሚሰማ ይናገራል።
“ብዙ ሰዎች ካለው ወቅታዊ ሁኔታ ጋር ምንም ተሳትፎ ሳይኖራቸው ሲያዙ እና ስልካቸውን በመፈተሽ እንዲሁም አንዳንዴ በስልክ የሚለዋወጧቸውን መረጃዎችን በማዳመጥ የመንግሥት ኃይሎች እርምጃ ሲወስዱ ስላየን የደኅንነት ስጋት አለብን።”
በዚህ ወቅት መረጃ ለጋዜጠኞች መስጠት “ራስን ለጉዳት ማጋለጥ ነው፤ በጉዳት ላይ ሌላ ጉዳት መጥራት ነው” ይላል።
“ግድ ስለሆነ አለመናገርን እንመርጣለን” የሚሉት የሳይንት ወረዳ አንድ ነዋሪ፤ ማኅበረሰቡ ላይ “ቀላል በሆኑ ጉዳዮች” ምክንያት ጫናዎች መድረሳቸውን በመጥቀስ “ፍርሃት ተፈጥሯል” ብለዋል።
በአካባቢ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጫና ምክንያት ምንጮች መረጃ ለመስጠት ፈቃኛ እንደማይሆኑ የሚያነሳው ጋዜጠኛ ግሩም፤ “ለሚዲያ መረጃ እንዳትሰጡ ተብለው በግልጽ የሚከለከሉ ሰዎች እንዳሉ ይነግሩናል” በማለት በክልሉ ያለውን የነዋሪዎች ስጋት ይጋራል።
ይህን የደኅንነት ስጋት ዕለት ከዕለት እንደሚኖሩት የሚናገሩት በላሊበላ መንግሥታዊ ባልሆነ ድርጅት የሚሰሩ ነዋሪ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በዐይነ ቁራኛ ይከታተሉናል ይላሉ።
ለዚህም የስልክ ልውውጦችን ከመበርበር ጀምሮ ጠለፋም ይካሄዳል ብለው ያምናሉ። ጓደኛቸው ላይ የደረሰውን ሲያስታውሱም “ማታ ቤቱ መጡ፤ ታፍኖ ተወሰደ” ሲሉ ለእስሩ ምክንያት የስልክ ግንኙነቱ ነው ይላሉ።
“ስልካችን ይጠለፋል፤ እንደዚህ ትላልቅ ሚዲያዎች ጋር ትኩረት ተደርጎ ስለሚጠለፍ ጫናው በኋላ መታሰር እና የደረሱበት አለመታወቅ ነው።. . . ሰዉ መናገር የማይፈልገው ሳይበደል እና ሳይጨቆን ቀርቶ አይደለም” ሲሉ ቢቢሲን በሚያወሩበት ቅጽት “ሰቀቀን” ላይ ሆነው እንደሆነ ተናግረዋል።
ለመገናኛ ብዙኃን መረጃ እንዳይሰጡ ጫና ይደርስባቸው እንደሆነ በቢቢሲ የተጠየቁት ነዋሪው፤ “ቀረብ ያሉ ሰዎች ‘ስልካችሁን ተጠንቀቁ’ ይሉናል፤ ‘ለማታውቁት ሰው እንደዚህ አይነት መረጃ አትስጡ’ ይሉናል” ሲሉ በቀጥታ ከመንግሥት ሰዎች ማስጠንቀቂያ እንደማይደርሳቸው ገልጸዋል።
የነዋሪዎች የደኅንነት ስጋት የዚህን ዘገባ አዘጋጅ ጨምሮ የመገናኛ ብዙኃን ባለሞያዎችን የሞራል አጣብቂኝ ውስጥ የጣለ ነው። በአንድ ወገን ለወራት የዘለቀው አለመረጋጋት መዘገብ አለበት በሚል፣ በሌላ ጎን ደግሞ ዘገባ ለመሥራት የሰውን ሕይወት አደጋ ላይ መጣል አሊያም ለችግር ማጋለጥ መስሎ መታየቱ ነው።
ጥቅምት መጨረሻ ላይ ላሊበላ ውስጥ በመንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የተካሄደውን ውጊያ ተከትሎ “በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች” ልጃቸው እና ባለቤታቸው እንደተገደሉ የሚናገሩ እናት፣ ለእራሳቸው እንዲሁም ለቤተሰባቸው ደኅንነት በመስጋት ስለሁኔታው ለመገናኛ ብዙኃን ለመናገር ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።
“ብናገር ምን ሊፈይድልኝ” ሲሉ ከቢቢሲ የቀረበላቸውን የፈቃደኝነት ጥያቄ ውድቅ ያደረጉት እኒህ እናት፤ በአካባቢያቸው መረጃ ሰጥተዋል የተባሉ ወጣቶች ተገድለዋል በሚል በስጋት ተሸብበው መረጃ አለመስጠትን መርጠዋል።
‘የመረጃ አፈና?’
በኢትዮጵያ የመረጃ ነጻነትና መረጃ የማግኘት መብት በወረቀትና በተግባር ለየቅል እንደሆነ ይነሳል። መረጃ ለመስጠት የተቋቋሙ የመንግስት ተቋማትም ግዴታቸውንና ኃላፊነታቸውን ዘንግተዋል በሚል ይወቀሳሉ።
ዶ/ር አየለ አዲስ የመገናኛ ብዙኃን እና ተግባቦት ባለሞያ እና በእንጅባራ ዩኒቨርስቲ መምህር ናቸው። በአጠቃላይ “የመረጃ ንፉግነት” ባህል አለ የሚሉ ሲሆን፤ ከመንግሥት መዋቅር ጀምሮ እስከ ማኅበረሰቡ ድረስ “መንግሥትን በመፍራት” የመረጃ እቀባ ይደረጋል ይላሉ።
ይህም ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና ሚዛናዊ መረጃ እንዳይሰራጭ ያደርጋል ሲሉ ሐሰተኛ፣ የተበከሉ እና የተዛቡ መረጃዎች ሥርጭት ከፍተኛ እንዲሆኑ በማድረግ ተጽዕኖውን ይገልጻሉ።
“መረጃ የዲሞክራሲ ሥርዓት አመላካች ነው” የሚሉት ዶ/ር አየለ፤ “መረጃ መከልከል የሌለበት ሀብት ነው” በማለት፣ “በአማራ ክልል እየተካሄደ ባለው ጦርነት ከባድ የመረጃን አፈና እየተፈጸመ ነው” ይላሉ።
አክለውም አፈናው የአገሪቱ የሕጎች ሁሉ የበላይ ከሆነው ሕገ-መንግሥት ጀምሮ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌን እንዲሁም የመገናኛ ብዙኃን የነጻነት እና መረጃ የማግኘት መብት አዋጅን የጣሰ እንደሆነ ዶ/ር አየለ አዲስ ተናግረዋል።
“መረጃ ኃይል ነው በሚባልበት ዘመን መገናኛ ብዙኃን መረጃ አላገኙም ማለት ሕዝቡም መረጃ የማግኘትም ሆነ የማወቅ መብቱ ተከልክሏል ማለት ነው።”
ጋዜጠኞች ራሳቸውን ሳንሱር እንደሚያደርጉ የሚጠቅሱት ዶ/ር አየለ እና ጋዜጠኞቹ እየተካሄዱ ያሉት ግጭቶች እና እየደረሱ ያሉ ጉዳቶች ተገቢውን የመገናኛ ብዙኃን ሽፋን አለማግኘታቸው “እየተፈጸሙ ያሉ ጥሰቶች እና በደሎች እንዳልተፈጸሙም ሊያስቆጥር ይችላል” በማለት ተጠያቂነትን እንደሚያጠፋ ይናጋራሉ።
በደሎች እና የመብት ጥሰቶች አለመዘገባቸው መነገር ያለባቸው ታሪኮች እንዲዳፈኑ ያደርጋል የሚሉት ዶ/ር አየለ፤ ተጽዕኖው “የሰብዓዊ መብት ረገጣዎች” እንዲስፋፉ ያደርጋል በማለት ስጋታቸውን ይገልጻሉ።
“የመረጃ ምንጮች መረጃ ሲደብቁ እና መረጃን ሲነፍጉ፣ ጭቆና እና በደሎች እንዲስፋፉ በር ይከፈታሉ ነው። ነገር ግን ይህንን ለማድረግ ያስገደዳቸው ስጋታቸው ይገባኛል፤ ምንም ጥያቄ የለውም። በሞባይል መቅረጽ፤ ድምጽ መቅረጽ በጣም ከባድ ሰዓት ነው” ይላሉ።
ዶ/ር አየለ የመረጃ ድበቃው የተጎጂዎችን ድምጽ ያፍናል በማለት፣ ጦርነቱ እና ተጽዕኖው በአግባቡ በመገናኛ ብዙኃን አለመሰነዱ ለጥናትም ሆነ ለታሪክ ማስረጃን ለማስቀረት የሚኖር ዕድልን ያሳጣል።
በተጨማሪም በሕዝቡም ሆነ በመንግሥት ኃላፊዎች በኩል የሚፈጸሙ የመረጃ አፈናዎች መገናኛ ብዙኃን መወጣት ያለባቸውን “የአቀራራቢነት” ሚና እንዳይወጡ እንቅፋት እንደሚሆንባቸው ያነሳሉ።
“ችግሩ ዞሮ ዞሮ ሕዝቡ ነው የሚጎዳው። ይህን ችግር ተቀራርቦ፣ ተነጋግሮ፣ ተወያይቶ በመፍታት ረገድ ሚዲያዎች ሊያደርጉት የሚገባው በጎ አስተዋጽኦ መረጃ ባለመበገኘቱ ምክንያት ኃላፊነታቸውን እንዳይወጡ አድርጓል” ይላሉ ዶ/ር አየለ።












