በመላው ዓለም አሳሳቢ እየሆነ ስለመጣው ኩፍኝ ሊያውቋቸው የሚገቡ ነጥቦች

የዓለም ጤና ድርጅት እና የአሜሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል (ሲዲሲ) እአአ ከ2023 መጨረሻ ጀምሮ የኩፍኝ በሽታ በልጆች ላይ የደቀነው ስጋት ቀጥሏል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
የሁለቱ ተቋማት የጋራ መግለጫ የወጣው ለዓመታት በሽታውን ለመከላከል የሚውለውን ክትባት የሚወስዱ ሰዎች ማሽቆልቆሉን ተከትሎ ነው።
ሲዲሲ በድረ-ገጹ እንዳስታወቀው የኩፍኝ ወረርሽኝ በሁሉም የዓለም ክልሎች እየተከሰተ መሆኑን ነው። የመን፣ ሕንድ እና ካዛኪስታን የኩፍኝ ቫይረስ በብዛት የተሰራጨባቸው አገራት ናቸው።
የዓለም ጤና ድርጅት እና ሲዲሲ እንደሚሉት ከአውሮፓውያኑ 2021 ጋር ሲነጻጸር በ2022 የኩፍኝ በሽታ ተጠቂዎች ቁጥር በ18 በመቶ ሲጨምር፣ የሟቾች ቁጥር ደግሞ 43 በመቶ ከፍ ብሏል።
ይህም በኩፍኝ የተያዙ ሰዎችን ቁጥር ወደ 9 ሚሊዮን አሳድጎታል። ከዚህ ጋር በተያያዘ ሕይወታቸው ያለፈው ደግሞ 136 ሺህ ሲሆኑ፣ ከእነዚህ መካከል አብዛኞቹ ልጆች ናቸው።
ባለፈው ዓመት አስደንጋጭ በሆነ ሁኔታ በአውሮፓ የኩፍኝ በሽታ በ30 እጥፍ መጨመሩን የዓለም ጤና ድርጅት ተናግሯል። እአአ በ 2023 በአህጉሪቱ ከ30 ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን፣ በ2022 የነበረው ቁጥር 941 ብቻ ነው።
የኩፍኝ በሽታ ምልክቶች የትኞቹ ናቸው?
- የተለመዱ የኩፍኝ ምልክቶች የሚከተሉት ናቸው፡
- ከፍተኛ ትኩሳት
- የታመሙ፣ የቀሉ እና የውሃ የያዙ ዐይኖች
- ማሳል እና ማስነጠስ
- በአጠቃላይ መጥፎ ስሜት
- በአፍ ውስጥ ትናንሽ ነጭ ነጠብጣቦች ሊታዩ ይችላሉ
- የጆሮ ኢንፌክሽን እና ተቅማጥ ተከትሎ ሊመጣ ይችላል።
- ብዙውን ጊዜ የማያሳክክ እና ከመጀመሪያዎቹ ምልክቶች በኋላ የሚታይ ቀይ ወይም ቡናማ የቆዳ ሽፍታም ያጋጥማል።
ሽፍታው ፊት እና ከጆሮ ጀርባ ላይ ከጀመረ በኋላ ወደ ቀሪው የሰውነት ክፍል የሚሠራጭ ሲሆን፣ ቡናማ እና ጥቁር ቆዳ ያላቸው ሰዎች ላይ ለመለየት አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል።

የኩፍኝ በሽታ ከቀላል እስከ ከባድ የጤና እክልን በታማሚዎች ላይ የሚያስከትል ከመሆኑ በተጨማሪ አስከ ህልፈት ሊያደርስ ይችላል።
አንዳንድ ሰዎች እንደ ሳንባ ምች፣ የኢንሰፋላይትስ (የአንጎል እብጠት) እና ዐይነ ስውርነት ያሉ ከባድ ችግሮች ሊያጋጥሟቸው ይችላሉ።
ኩፍኝ እንዴት ይተላለፋል?
ቫይረሱ የታመመ ሰው ሲያስል ወይም ሲያስነጥስ በሚለቀቁ ትንንሽ ፍንጣቂዎች ውስጥ ይገኛል።
ጠብታዎቹ ባሉበት አካባቢ በመተንፈስ፣ ወይም እነሱን በመንካት በእጅ አማካይነት በአፍንጫ ወይም በአፍን በኩል ከሰው ወደ ሰው ሊተላለፍ ይችላል።
የኩፍኝ በሽታ ያለባቸው ሰዎች በቆዳ ላይ የሚወጣው ሽፍታ ከታየባቸው እስከ ከአራት ቀናት ድረስ ቫይረሱን ሊያስተላልፉ ይችላሉ።

ኤም ኤም አር ክትባት
የዓለም ጤና ድርጅት፣ የአሜሪካው ሲዲሲ፣ የዩናይትድ ኪንግደም ብሔራዊ የጤና አገልግሎት (ኤንኤችኤስ) እና ሌሎች የጤና ባለሥልጣናት እንደሚሉት ኩፍኝ በጣም ተላላፊ በሽታ ነው።
በሲዲሲ አሃዝ መሠረት ሰዎች በሽታውን በተገቢው የመከላከያ መንገዶችን ተከትለው እራሳቸውን ካልጠበቁ ለቫይረሱ ከሚጋለጡ 10 ሰዎች መካከል 9 ያህሉ ይያዛሉ።
ኩፍኝን በሁለት ጊዜ በሚሰጥ ሚዝል፣ መምፕስ ኤንደ ሩቤላ (ኤም ኤም አር) በተሰኘ በኩፍኝ ክትባት መከላከል ይቻላል። ክትባቱ እነዚህን ሦስት በሽታዎች ይከላከላል።
የዓለም ጤና ድርጅት እንደሚለው ከሆነ በሽታው በብዛት በሚገኝባቸው አገራት የሚገኙ ሕጻናት 9 ወር ሲሞላቸው የመጀመሪያውን የኤም ኤም አር ክትባትን እንዲወስዱ ይመክራል። ሁለተኛው ደግሞ ብዙውን ጊዜ ከ15 እስከ 18 ወራት ሲሆናቸው መሰጠት እንዳለበት ይገልጻል።
“በ1963 [የኩፍኝ] ክትባት ከመጀመሩ እና በስፋት ከመሰጠቱ በፊት፣ በየሁለት እና ሦስት ዓመቱ ወረርሽኞች ይከሰቱ ነበር። በዚህም በየዓመቱ ወደ 2.6 ሚሊዮን የሚገመቱ ሰዎች ሕይወታቸው ያልፋል” ብሏል።
የዓለም ጤና ድርጅት አክሎም የሟቾች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ በክትባቱ አማካይነት በጣም መቀነሱን “በ2021 በግምት 128 ሺህ ሰዎች በኩፍኝ ሞተዋል” ሲል አስታውቋል።
“አስተማማኝ እና ወጪ ቆጣቢ ክትባት ቢኖርም አብዛኛዎቹ ሟቾች ከአምስት ዓመት በታች ያሉ ሕጻናት ናቸው” ብሏል።

ስለኤም ኤም አር ክትባት የተሳሳቱ መረጃዎች
የሴራ ተንታኞች የኤም ኤም አር ክትባቱን ከኦቲዝም ጋር በማገናኘት ሐሰተኛ መረጃዎችን አቅርበዋል።
እንግሊዛዊው ተመራማሪ አንድሪው ዌክፊልድ በ1998 ሁለቱ የተገናኙ መሆናቸውን በስህተት ተናግሮ ነበር።
በኋላ ላይ ጥናቱ ውድቅ ተደርጓል። ዌክፊልድ በ2010 በዩናይትድ ኪንግደም የሕክምና ምክር ቤት እንዲወገድ ተደርጓል።
የኤም ኤም አር ክትባት ኦቲዝምን ስለማስከተሉ የሚያሳይ ምንም ማስረጃ የለም።
ለመከተብ ማመንታት
ታዳጊዎች እና ጎልማሶች የኤም ኤም አር ክትባት ቀድመው ካልወሰዱ መከተብ ይኖርባቸዋል።
ሲዲሲ እና የዓለም ጤና ድርጅት እንዳሉት ከሆነ ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ በኋላ የኩፍኝ ክትባት ሽፋን ቀስ በቀስ እየቀነሰ መምጣቱን አመልክተዋል።
“የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በክትባት እና በክትባት ጥረቶች ላይ ጥያቄን አስከትሏል። የክትባት አገልግሎት መቋረጥ እና በዓለም ዙሪያ ያለው የመከተብ ምጣኔ መቀነስ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሕጻናትን እንደ ኩፍኝ ላሉ በሽታዎች ተጋላጭ አድርጓቸዋል” ሲል የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል።
በ2021 (እአአ) ክብረ ወሰን ሆኖ የተመዘገበ ወደ 40 ሚሊዮን የሚጠጉ ሕጻናት የኩፍኝ ክትባት አምልጧቸዋል። 25 ሚሊዮን ሕጻናት የመጀመሪያውን ዙር ክትባት አላገኙም። 14 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሕጻናት ደግሞ ሁለተኛውን ክትባት አልወሰዱም።
የመጀመሪያ ክትባት ያመለጣቸው ከተባሉት ሕጻናት መካከል ግማሽ ያህሉ የሚኖሩት በ10 አገራት ነው። እነዘህም አንጎላ፣ ብራዚል፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ኢትዮጵያ፣ ሕንድ፣ ኢንዶኔዢያ፣ ማዳጋስካር፣ ናይጄሪያ፣ ፓኪስታን እና ፊሊፒንስ ናቸው።
አዋቂዎች በኩፍኝ ሊያዙ ይችላሉ?

ከዚህ ቀደም ያልተከተበ ወይም በበሽታው ያልተያዘ ማንኛውም ሰው በኩፍኝ ሊያዝ ይችላል። በታዳጊ ልጆች ዘንድም በጣም የተለመደ ነው።
እንደ ዓለም ጤና ድርጅት፣ ሲዲሲ እና ሌሎች የጤና ተቋማት ከሆነ ኩፍኝ በሁሉም የዕድሜ ክልል ውስጥ ባሉ ሰዎች ላይ ከባድ የጎንዮሽ ጉዳቶችን ሊያስከት ይችላል።
በኩፍኝ የበለጠ ሊጠቁ የሚችሉ የሚባሉት የሚከተሉት ናቸው፡
- ከ 5 ዓመት በታች የሆኑ ሕጻናት
- ከ 20 ዓመት በላይ የሆኑ አዋቂዎች
- እርጉዝ ሴቶች
- እንደ ሉኪሚያ ወይም ኤችአይቪ ባሉ ህመሞች የተፈጥሮ በበሽታን የመከላከያ ሥርዓታቸው የተዳከሙ ሰዎች።
በኩፍኝ ድጋሚ የመያዝ ዕድል አለ?
ለትርፍ ያልተቋቋመ የአሜሪካ የጥናት ማዕከል የሆነው ማዮ ክሊኒክን ጨምሮ ሲዲሲ፣ ኤንኤችኤስ እና ሌሎችም ተቋማት እንደሚሉት፣ ድጋሚ የመያዝ አጋጣሚ በእጅጉ ዝቅተኛ ቢሆንም ዕድሉ ግን አለ።
የማዮ ክሊኒክ እንዳለው ከሆነ የመጀመሪያውን ክትባት ከወሰዱት ሰዎች ከ93 በመቶ በላይ የሚሆኑት ኩፍኝን የመከላከል አቅም አላቸው። ከሁለተኛው ክትባት በኋላ ደግሞ 97 በመቶው ከበሽታው ይጠበቃሉ።
የኩፍኝ ክትባት ስለመውሰዳቸው እርግጠኛ ያልሆኑ ሰዎች በደም ምርመራ ማረጋገጥ ይችላሉ።
በአሜሪካ በሽታውን የመከላከል አቅም የሌላቸው አዋቂዎች ቢያንስ አንድ ጊዜ ክትባቱን እንዲወስዱ ይመከራሉ።
በሽታው ያልያዛቸው ወይም ክትባቶቹን ወስደው የማያውቁ ሰዎች በአንድ ወር ልዩነት ሁለት ጊዜ መከተብ ያስፈልጋቸዋል።












