በዓለም የመጀመሪያው የወባ መከላከያ ክትባት በካሜሩን መሰጠት ተጀመረ

በቀኝ በኩል ያለችው የስምንት ወር ዕድሜ ያላት ዳንዜላ በካሜሩን ክትባቱን በመውሰድ የመጀመሪያዋ ሆናላች

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, በቀኝ በኩል ያለችው የስምንት ወር ዕድሜ ያላት ዳንዜላ በካሜሩን የወባ መከላከያ ክትባቱን በመውሰድ የመጀመሪያዋ ሆናላች

በዓለም የመጀመሪያው የወባ መከላከያ ክትባት በካሜሩን ተጀመረ። በመላው አፍሪካ በሺዎች የሚቆጠሩ ልጆችን ሕይወት ያድናል ተብሏል።

የመጀመሪያው ክትባት ዛሬ የተሰጠው ዳንኤላ ለተባለች ልጅ በካሜሩን ዋና ከተማ ያውንዴ ውስጥ ነው።

በአፍሪካ በየዓመቱ 600,000 ሰዎች በወባ ምክንያት እንደሚሞቱ የዓለም ጤና ድርጅት ገልጿል።

ከሟቾች መካከል ከአምስት ዓመት በታች ያሉ ሕጻናት 80% ይይዛሉ።

አርቲኤስኤስ የተባለውን ክትባት ከስድስት ወር በታች ላሉ ጨቅላ ሕጻናት ካሜሩን በነጻ ነው እየሰጠች ያለው።

ይህ የወባ መከላከያ ክትባት የሚሠጣቸው ሕጻናት በአጠቃላይ አራት ጠብታ መውሰድ ያስፈልጋቸዋል።

ክትባቱ በ36% ለበሽታው ተጋላጭ በሆኑ ሰዎች ላይ ውጤታማ መሆኑን የአሜሪካ ጥናት ተቋም አሳውቋል። ይህም ከሦስት ሰዎች የአንድ ሰው ሕይወት ይታደጋል ማለት ነው።

ክትባቱ መጀመሩ ነፍስ አድን እና እፎይታ የሚሰጥ ቢሆንም የውጤታማነት መጠኑ ውስን መሆን የታቀደውን ግብ እንዳልመታ በኬንያ የወባ መከላከያ ማኅበር ባለሙያ ዊልስ አክዌል ይናገራሉ።

ሐኪሞች ህመሙን መከላከል የሚችሉበት ተጨማሪ ግብዓት መሆኑን ክትባቱ በካሜሩን እንዲጀመር ያስቻሉት የካሜሩን ሐኪም ዶ/ር ሻሎም ኖዱላ ይናገራሉ።

“በበሽታው የሚያዙ እና የሚሞቱ ሰዎችን ቁጥር በከፍተኛ መጠን መቀነስ እንችላለን። በሽታውን ለማጥፋት የሚደረገውን ትግልም ያፋጥናል” ብለዋል።

ክትባቱን ለመሥራት 30 ዓመታት ወስዷል። ጥናት ያደረገው የዩናይትድ ኪንግደሙ መድኃኒት አምራች ጂኤስኬ ነው።

የዓለም ጤና ድርጅት ክትባቱን ፈቃድ ሰጥቶታል። ክትባቱን በካሜሩን ሲያስጀምር በሽታውን በመከላከል ረገድ ከፍተኛ ደረጃ መደረሱን ገልጿል።

ክትባቱ በኬንያ፣ በጋና እና በማላዊ ከተሞከረ በኋላ ነው በካሜሩን የተጀመረው።

ሌሎች 20 አገራት ክትባቱን በዚህ ዓመት ለመጀመር እየተጠባበቁ እንደሚገኙ ዓለም አቀፍ የክትባት ተቋም ጋቪ ገልጿል።

ከእነዚህም ውስጥ ቡርኪና ፋሶ፣ ላይቤሪያ፣ ኒጀር እና ሴራ ሊዮን ይገኙበታል።

የዓለም ጤና ድርጅት እንዳለው፣ በየዓመቱ በካሜሩን ስድስት ሚሊዮን ሰዎች በበሽታው የሚያዙ ሲሆን፣ አብላጫውን ቁጥር የሚይዙት ከአምስት ዓመት በታች ያሉ ሕጻናት ሆነው 4,000 ሰዎች ይሞታሉ።

በ42 ቀጠናዎች ስድስት ወራት የሞላቸው ጨቅላዎች ሁለት ዓመት እስኪሆናቸው አራት ጠብታ ይወስዳሉ።

ክትባቱን በተመለከተ ካሜሩን ውስጥ ፍርሃት እና ጥርጣሬዎች ነበሩ።

ሆኖም የአገሪቱ የክትባት ኃላፊ ዳንኤሊ ኤኮቶ “ክትባቱ አስተማማኝና ነጻ ነው” ብለዋል።

አንድ ልጇን ያስከተበች እናት ‘ልጄን ለማስከተብ የወሰንኩት ከወባ ለመከላከል ነው። ልጆች በበሽታው ሲያዙ በቀላሉ ይሞታሉ” ብላለች።

እአአ በ2021 በወባ ምክንያት ከተከሰተ ሞት 95% በአፍሪካ ነው የተመዘገበው። ከወባ ጋር በተያያዘ በተከሰቱ ሞቶች ደግሞ 96% ተመዝግቧል።