በአፍሪካ ኩፍኝ እና ፖሊዮ እንደ አዲስ ማንሰራራታቸው ተገለጸ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
እንደ ኩፍኝና እና ፖሊዮ የመሳሰሉ ሕፃናትን በተለየ የሚያጠቁና በክትባት መከላከል የሚቻሉ በሽታዎች አፍሪካ ውስጥ መታየት መጀመራቸው ተገልጿል።
የዓለም ጤና ድርጅት እንደሚለው ይህ የክትባቶች ስርጭት መስተጓጎል ሊከሰት የቻለው በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ነው።
ድርጅቱ እንዳስታወቀው በያዝነው የፈረንጆቹ ዓመት ብቻ ከጥር እስከ መጋቢት ባሉት ወራት አፍሪካ ውስጥ 17 ሺህ የኩፍኝ በሽታ ታማሚዎች ሪፖርት ተደርገዋል። ካለፈው ዓመት ቁጥር ጋር ሲነጻጸር ደግሞ የዘንድሮው የ400 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።
እነዚህ በክትባት መጥፋት የሚችሉ በሽታዎች በአፍሪካ እንደ አዲስ እያንሰራሩ ለመምጣታቸው ዋነኛ ምክንያቶች ደግሞ ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች ክትባቶችን ማድረስ አለመቻሉና የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ናቸው ተብሏል።
እንደ ኢትዮጵያ፣ ዴሞክራቲክ ኮንጎ፣ ናይጄሪያ እና ሶማሊያ ባሉ ከሰሀራ በታች የሚገኙ 24 አገራት ሁለት ጊዜ መወሰድ ያለበትን የኩፍኝ ክትባት የመጀመሪያውን ዙር እንኳን ማግኘት አልቻሉም።
የኩፍኝ በሽታ በተለይም ሕፃናት ላይ ከፍተኛ ሕመምና ሞት የሚያስከትል፣ ሚዝልስ በሚባል ቫይረስ አማካይነት የሚከሰት ሲሆን በክትባት መከላከል የሚቻል በሽታ ነው።
ማላዊ ባለፈው ወር የፖሊዮ ወረርሽኝ መከሰቱን አስታውቃለች። መሰል ወረርሽኝ አፍሪካ ውስጥ ሲከሰት በአምስት ዓመታት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
ይህ ወረርሽኝ መነሻው ከፓኪስታን እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፣ እንዴትና መቼ ወደ ደቡብ አፍሪካዊቷ አገር ሊገባ እንደቻለ ግን እስካሁን ምንም የታወቀ ነገር የለም።
አሳሳቢው ነገር ሁለቱም በሽታዎች በክትባት መከላከል የሚቻሉና ተገቢው ክትትል ካልተደረገባቸው በተለይ ለበርካታ ሕፃናት የሞት ምክንያት መሆናቸው ነው።












