እስራኤል የጋዛን ጦርነት ካላቆመች ቀጠናው ከቁጥጥር ውጭ ሊወጣ እንደሚችል ኢራን አስጠነቀቀች

የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሚር አብዱላሒያን

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሚር አብዱላሒያን

የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እስራኤልን አስጠነቀቁ።

ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አሚር አብዱላሂያን እንዳሉት ኢራን ጋዛን በጦር መሣሪያ መደብደብ የማታቆም ከሆነ መካከለኛው ምሥራቅ ወደ ቀውስ ቀጠናነት ሊሸጋገር ይችላል ብለዋል።

አብዱላሒያን በዚህ አስተያየታቸው አሜሪካንን ተጠያቂ አድርገዋል።

እስራኤል በጋዛ እየወሰደች ባለችው የአየር ጥቃት በጥቂት ሳምንታት ብቻ 4600 ሰዎች በጋዛ ተገድለዋል። ከሟቾቹ ብዙዎቹ ሴቶችና ሕጻናት ናቸው።

እስራኤል ይህ ጥቃት ለወራት ሊቀጥል እንደሚችል ጠቁማለች።

ኢራን ይህ የንጹሐን እልቂት በጊዜ ካልተገታ ቀጠናው ከቁጥጥር ውጭ ሊወጣ እንደሚችል በተደጋጋሚ ስጋቷን ገልጣለች።

“አሜሪካንና እስራኤልን በጋዛ ላይ የሚያደርሱትን ይህን ኢሰብአዊ ጅምላ ግድያ ካላቆሙ ማንኛውም ነገር በማንኛውም ቅጽበት ሊሆን ይችላል። ያ ደግሞ ቀጠናውን ከቁጥጥር ውጭ እንዲሆን ያደርጋል’’ ብላለች።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት በቴህራን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነው።

‘’ነገሩ ከቁጥጥር ውጭ ከወጣ መመለሻ አይኖረመው። ‘ የከፋና መራራ’ ይሆናል። ውጤቱም ጦርነቱን ለጀመሩት ጭምር ብዙ ጣጣ ይዞባቸው ይመጣል ብለዋል።

ኢራን በጋዛ የሚፈጸመው ጥቃት የአሜሪካ ጦርነት ሆኖ እስራኤል በውክልና እየተዋጋች እንደሆነ ነው የምታምነው።

‘’አሜሪካ ወታደራዊ ቁሳቁሶችን ወደ ቀጠናው ማስጠጋቷ እስራኤል ይህን ጦርነት በውክልና ለአሜሪካ እየተዋጋች መሆኑ ማሳያ ነው’’ ብለዋል።

ከኢራን ባሻገር አሜሪካም ይህ ጦርነት ዳፋው ለአካባቢው እንዳይተርፍ ስጋት አላት።

የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ሎይድ ኦስትን ‘’በአሜሪካ ዜጎች፣ ጥቅሞች ወይም ወታደሮች ላይ ጥቃት ከደረሰ ነገሩ ሊባባስ ይችላል'' ብለዋል።

መከላከያ ሚኒስትሩ ጨምረው፣ ‘’አሁን ያለው ሁኔታ መልካም አጋጣሚ አድርጎ በመውሰድ ይህን ጦርነት ለማስፋፋት ትንኮሳ የሚፈጽም አገር ባይሞክረው ይሻላል’’ሲሉ ኢራንን በስም ሳይጠቅሱ አስጠንቀቅዋል።

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ብሊንከንም በተመሳሳይ ይህ የጋዛ ጦርነት አካባቢያዊ መልክ እንዳይዝ ስጋት እንዳላቸው አልሸሸጉም።

‘’ከሐዝቦላሕና እና ከሐማስ ጥቃቶች የሚመጡ ከሆነ እስራኤልን ለመከላከል በተጠንቀቅ አለን’’ ብለዋል።

በሰሜን እስራኤል ጉብኝት ያደረጉት ናታንያሁ ለወታደሮቻቸው ‘’ይህ ለሕይወታችን ስንል የምንዋጋው ጦርነት ነው። ይህ ማጋነን አይደለም፤ ይህ የሞት ሽረት ጉዳይ ነው። መሞት አለባቸው’’ ሲሉ ሒዝቦላህ ላይ የማያዳግም እርምጃ መውሰድ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ናታንያሁ ጨምረው ሒዝቦላህ በዚህ ጦርነት ለመሳተፍ ከወሰነ ቀይ ስህተት ይሆናል። ታይቶና ተሰምቶ የማያውቅ ኃያል ክንድ ያርፍበታል። ለሒዝቦላህ ሳይሆን ለሊባኖስም አጥፊ ነው የሚሆነው’’ ሲሉ ዝተዋል።

ሒዝቦላህ በበኩሉ ወደ ጦርነቱ ለመግባት ሙሉ ዝግጅት እንዳለው ገልጧል።

በደቡባዊ ሊባኖስ የእስራኤል ወታደሮች ከሐማስ ጋር ባደረጉት የተኩስ ልውውጥ 27 ሰዎች ተገድለዋል። በእስራኤል በኩል በትንሹ አምስት ወታደሮችና አንድ ሲቪል ተገድሏል።

እስራኤል ትናንት እሑድ ሶሪያ ላይ የአየር ጥቃት ሰንዝራለች። የደማስቆና የአሌፖ ዓለም አቀፍ አየር መንገዶችንም ከጥቅም ውጭ አድርጋቸዋለች።

በዚህ ጥቃት ሁለት የአየር መንገድ ሠራተኞች ተገድለዋል።ኢራን በሶሪያ ወታደራዊ ቀጠናዎች አሏት።