ከሐማስ እና ከሒዝቦላህ ማን ጠንካራ ጦር አለው? አሜሪካ እና ኢራንስ ወደ ግጭቱ ይገቡ ይሆን?

ሊባኖስ የሚገኘው ሒዝቦላህ ተዋጊዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ሊባኖስ የሚገኘው ሒዝቦላህ ተዋጊዎች

በጋዛ ውስጥ የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ በርካታ የቢቢሲ አንባቢያን መሠረታዊ ጥያቄዎችን ያነሳሉ።

ለእነዚህ ጥያቄዎች በመካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ የሚገኙ እና ጉዳዩን በጥልቅ የሚረዱ የቢቢሲ ዘጋቢዎች ምላሽ እንዲሰጡባቸው አድርገናል።

ወደ ሦስተኛው የዓለም ጦርነት ሊያመራ ይችላል?

ኢራን በዚህ ጦርነት በቀጥታ ከገባች እና አሜሪካ ምላሽ ለመስጠት ከተገደደች ይህ ሁኔታ ወደ ሦስተኛው የዓለም ጦርነት ሊከተን ይችላል?

የቢቢሲው የዓለም አቀፍ ፖለቲካዊ ጉዳዮች አርታኢ የሆነው ጄሬሚ ቦወን “አይመስለኝም” ይላል።

ከዚህ ቀደም የአሜሪካው ጆ ባይደን ኢራን ወይም ሒዝቦላህ በዚህ ጦርነት ውስጥ በቀጥታ ሊገቡበት ይችላሉ ብለው ያስባሉ ተብለው ተጠይቀው “አላውቅም” ብለዋል።

አሜሪካ ለማንኛውም በሚል ሁለት ግዙፍ የጦር ጄት ተሸካሚ መርከቦችን ወደ ሜዲትራኒያን ባሕር አስጠግታለች። ይህ ማለት አሜሪካ ለኢራን የማያሻማ መልዕክት እያስተላለፈች ነው።

መልዕክቱ “በዚህ ጦርነት እስራኤልን የሚነካ የአሜሪካ ኃያል ጡጫ ያርፍበታል” የሚል ነው።

መካከለኛው ምሥራቅ ኢራን እና አጋሮቿ፣ ከአሜሪካ እና አጋሮቿ ጋር ተፋጠው ያሉበት ቀጠና ነው። ሁለቱም ወገኖች እጃቸውን በቀጥታ በጦርነቱ ካስገቡ የሚከተለውን ነገር ሁለቱም ጠንቅቀው ያውቃሉ።

ስለዚህ ከቀዝቃዛ ጦርነት ወደለየለት ጦርነት ይገባሉ ተብሎ አይጠበቅም።

እስራኤል ማሳካት የፈለገችው ምንድነው ነው?

ለዚህ ጥያቄ ምላሽ የሰጠችው በደቡባዊ እስራኤል የምትገኘው እና ከፍተኛ ልምድ ያላት የቢቢሲዋ የዓለም አቀፍ ዘጋቢ ሊዝ ዱሴት ናት።

ከዚህ ቀደም በነበሩ ጦርነቶች እስራኤል ሐማስን እንደምታዳክም፣ ሮኬት የመተኮስ አቅሙን እንደምታኮላሽ ነበር የምትዝተው። አሁን ግን ሐማስን ሙሉ በሙሉ ከምድረ ገጽ የማጥፋት ዘመቻ ነው የያዘችው።

እስራኤልም ሐማስን ልክ እንደ አይኤስ ቡድን እስከ ወዲያኛው መቅበር ትፈልጋለች።

እስራኤል የሐማስን ወታደራዊ መዋቅር መደምሰስ የሚያስችል አቅም አላት። ይሁንና እስራኤል በጋዛ የምድር ጦር ዘመቻ ምን እንደሚጠብቃት በትክክል መናገር ይከብዳል።

ከአይኤስ በተለየ ሐማስ ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ መሠረት ያለው ድርጅት ነው።

በፍልስጤም ሕዝብ ዘንድ ድጋፍ አለው።

የእስራኤል ሐማስን ከምድረ ገጽ የማጥፋት ዘመቻ በከፊል ሊሳካ ይችል ይሆናል። ሐማስ የገነባውን መሸሎክሎኪያ የመሬት ለመሬት ምሽግን ማፍረስ ይቻላትም ይሆናል።

ነገር ግን በሕዝቡ ውስጥ ያለን ለዓላማ የመሞት ቁርጠኝነት ማፍረስ ግን ይከብዳታል።

የአስራኤል ወታደሮች በጋዛ ድንበር ዙሪያ እየተሰባሰቡ ነው

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, የአስራኤል ወታደሮች በጋዛ ድንበር ዙሪያ እየተሰባሰቡ ነው

ሐማስ መብረቃዊ ጥቃቱን የፈጸመው ምን ለማሳካት ነው?

ለዚህ ጥያቄ ምላሽ የሰጠው የቢቢሲ የደኅንነት ጉዳዮች ዘጋቢ ፍራንክ ጋርድነር ነው።

በወቅቱ ሐማስ ለዚህ የሰጠው መልስ “ሁሉም ነገር ልክ አለው” የሚል ነበር።

በዋናነት እስራኤል በፍልስጥኤማውያን ላይ ታደርሰዋለች ለሚለው ግፍ እና መከራ ምላሽ የተፈጸመ ጥቃት ነበር።

ተንታኞች ግን ለሐማስ መብረቃዊ ጥቃት ሌላም ምክንያት ሊኖር እንደሚችል ይጠረጥራሉ።

ከዚህ ጥቃት ጥቂት ቀደም ብሎ እስራኤል ያላትን ግንኙነት ለማሻሻል ታሪካዊ የተባለ የስምምነት ሰነድ ከሳዑዲ አረቢያ ጋር ለመፈራረም በዝግጅት ላይ ነበረች።

ይህ ብዙ የተባለለት ስምምነት በሐማስ እና በፍልስጥኤሞች ዘንድ ክህደት ተደርጎ ነበር የተወሰደው። ኢራንም ደስተኛ አልነበረችም።

ስምምነቱ የሐማስ መብረቃዊ ጥቃትን ተከትሎ ለጊዜው እንዲዘገይ ተደርጓል።

ሌላው የሐማስ መሪዎች በእስራኤል ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ ተረድተዋል። በማኅበረሰቡ ውስጥ ያለውን መከፋፈል እና ቀኝ አክራሪ መንግሥት ሥልጣን መያዙን፣ በፍትሕ ሥርዓት መዋቅር ላይ እየተደረገ ያለው ለውጥ በሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ ተቃውሞ ማስነሳቱን ይረዳሉ።

ይህ ጥቃት በእስራኤል ያለውን ክፍፍል ይበልጥ ያብሰዋል ብለው ሳያስቡ አልቀረም።

ግብፅ ድንበሯን ለፍልስጥኤሞች የማትከፍተው ለምንድነው?

ብዙዎቹ ግብፃውያን የፍልስጥኤም ወንድሞቻቸውን ሕመም ቢጋሩ ደስተኞች ናቸው።

ነገር ግን የግብፅ መንግሥት በሰላሙ ጊዜም ቢሆን በራፋህ ድንበር ፍልስጥኤሞች እንዲገቡ አይፈቅድም።

ሐማስ በምርጫ አሸንፎ ጋዛን ማስተዳደር ከጀመረ ወዲህ ግብፅ የጋዛን ድንበር በመዝጋቱ ረገድ ከእስራኤል ጋር ተባብራለች።

አንድ ምክንያት የሚሆነው ሐማስ በግብፅ የሚገኙ የሙስሊም ወንድማማቾች የፖለቲካ እንቅስቃሴ ወዳጅ መሆኑ ነው። ያ ድርጅት ደግሞ በግብፅ ላለው መንግሥት ተቃዋሚ ነው።

አልሲሲ የመጡት የሙስሊም ወንድማማቾችን በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት ገልብጠው መሆኑ መዘንጋት የለበትም።

አሁን ያለው የግብፅ አስተዳደር ከሐማስ ጋር የተመጠነ ግንኙነት አለው። በድርድር ጊዜም ወሳኝ ሚናን ይጫወታል። ነገር ግን አሁን ያለው የግብፅ መንግሥት የፍልስጥኤሞችን ወደ ግብፅ በብዛት መግባት አይደግፍም።

በጋዛ ያሉ መጠለያ ጣቢያዎች 75 ዓመታትን አስቆጥረዋል። ከገዛ መሬታቸው በእስራኤል የተፈናቀሉ ፍልስጥኤማውያን መኖሪያዎች ናቸው።

ግብፅ ፍልስጥኤማውያንን ወደ አገሯ ማስገባት አንድም ለአገር ውስጥ ፖለቲካዋ ችግር መጋበዝ ሆኖ ነው የሚታያት፣ ሁለተኛው ደግሞ የፍልስጥኤማውያንን የአገር ባለቤትነት ጥያቄን ያጓትታል ብላ ታምናለች።

በአስራኤል ጥቃት ጋዛ ውስጥ የወደመ መኖሪያ ቤት

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, እስራኤል በጋዛ ላይ እየፈጸመችው ባለው የአየር ጥቃት ሲቪሎች እንዳይጎዱ የተባበሩት መንግሥታት ጠይቋል

የተባበሩት መንግሥታት ለምን ጣልቃ አይገባም?

እስራኤል ንጹሐንን በብዙ ቁጥር እየገደለች ለምን የተባበሩት መንግሥታት ጣልቃ አይገባም ለሚለው ጥያቄ ምላሽ የሰጠው ጄምስ ላንዳል ነው። ጄምስ የቢቢሲ የዲፕሎማቲክ ጉዳዮች ዘጋቢ ነው።

ብዙ አገሮች እስራኤልን ለመውቀስ ፈራ ተባ የሚሉት አንዱ ምክንያት በሐማስ ጥቃት ደርሶባት የአጸፋ ምላሽ እየሰጠች ስለሆነ ነው። ራሷን የመከላከል መብት አላት በሚል ነው።

ንጹሐን ላይ ስለሚደርሰው ስቃይ የበርካታ አገራት መሪዎች ለእስራኤል ማሳሰቢያ እንደሰጡ ይናገራሉ።

የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ “የንጹሐን ጉዳት በሚቀንስበት ሁኔታ ላይ ከኔታንያሁ ጋር መክረናል” ብለዋል። የተባበሩት መንገሥታትም እስራኤል በንጹሐን ላይ የምታደርሰውን ጥቃት ታቁም ሲል አሳስቧል።

እስራኤል ግን የሐማስን ይዞታዎች ነው እያጠቃሁ ያለሁት ትላለች።

እስራኤል እንዴት ስለ ሐማስ ጥቃት መረጃው ሳይኖራት ቀረ?

ከዚህ ቀደም እስራኤል የሐማስን እያንዳንዷን እንቅስቃሴ እንደምታውቅ ስትናገር ነበር። እንዴት ይህን ጥቃት አስቀድማ ማቆም አቃታት የሚለው የብዙዎች እንቆቅልሽ ነው።

ከዚህ ቀደም የእስራኤል መንግሥት አንድ የደኅንነት ቁጥጥር ማዕከልን ለጋዜጠኞች አስጎብኝቶ ነበር።

ማዕከሉ በጋዛ በእያንዷ ደቂቃ ምን እየተከናወነ እንዳለ በድሮን እና መሬት ላይ በተተከሉ ካሜራዎች መከታተል የሚያስችለው ነው።

ከዚህ ሌላ ከሕዝብ ጋር የሚኖሩ በርካታ መረጃ አቀባዮች አሉት።

ከዚህ ቀደም በነበሩ የእስራኤል እርምጃዎች የኢስላሚክ ጂሐድ መሪዎች በየትኛው ደቂቃ የት እንደሚገኙ መረጃ ስለነበረው ዒላማቸውን ያልሳቱ በርካታ እርምጃዎችን መውሰድ ችሏል።

እስራኤል በተራቀቁ መሣሪያዎች እና የስለላ አደረጃጀቶች ውስጥ ሆናም ቢሆን ሐማስ ይህን ሰብሮ ገብቶ መብረቃዊ ጥቃት ማድረሱ የመረጃ ክፍተት ነበር በሚል መግለጫ ሰጥተው አምነዋል።

ይሁንና አሁን እግረኛ ጦር ወደ ጋዛ ከገባ የሐማስን እያንዳንዱን መደበቂያ ጉድጓድ እግር በእግር ደርሶ እንደሚደመሰስ ይጠበቃል። የእስራኤል ጦር በቂ የሚባል መረጃ አለው።

ከሒዝቦላህ እና ከሐማስ ወታደራዊ አቅም የማን ይበልጣል?

ለዚህ ምላሽ የሰጠው በደቡብ ሊባኖስ የሚገኘው የቢቢሲው ዘጋቢ ሁጎ ባቼጋ ነው።

ሒዝቦላህ ከሐማስ ይልቅ ጠንካራ እንደሆነ በእስራኤሎች ዘንድ ይታመናል፤ ይነገራልም።

የሚደገፈው በኢራን ሲሆን፣ 130 ሺህ ሮኬቶች እና ሚሳኤሎች እንዳሉት ይገመታል።

ሚሳኤሎቹ ዒላማን እንዳይስቱ ዘመናዊ መሣሪያ የተገጠመላቸው ናቸው። ማዕከላዊ እስራኤል ድረስ ዘልቀው ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ ናቸው።

ሐማስ ግን ይህ ዓይነት አቅም የለውም።

ምንም እንኳ ገለልተኛ ምንጮች ይህ አሐዝ የተጋነነ ነው ቢሉም፣ የሒዝቦላህ መሪ ሐሰን ነስረላህ 100 ሺህ ሠራዊት እንዳላቸው ይናገራሉ። ሒዝቦላህ ምናልባት ከ20 ሺህ እስከ 50 ሺህ የሚገምት ታጣቂ ይኖረዋል።

ይሁንና ብዙዎቹ በደንብ የሠለጠኑ እና የጦር ሜዳ ልምድ ያላቸው ናቸው። በሶሪያ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥም ተሳትፈዋል።

እስራኤል እንደምትለው ሐማስ በድምሩ ከ30 ሺህ በላይ ወታደር የለውም።